Thursday, November 1, 2012

ጾመ ጽጌ ክፍል 2

የማኅሌተ ጽጌና የጾመ ጽጌ አጀማመር
  የእመቤታችን የስደቷ መታሰቢያ ወር በቤተ ክርስቲያናችን የሚከበረው በማኅሌት፣ በቅዳሴና በዝክር ነው፡፡ በወርኃ ጽጌ ባሉት ሳምንታት ከቅዳሜ ማታ እስከ እሑድ ጠዋት አበው ካህናት የሚያቀርቡት ዝማሬ ከቅዱስ ያሬድ ድጓ፣ ከማኅሌት ጽጌና ከሰቆቃው ድንግል የተውጣጣና ሦስት ወገን ያለው ነው፡፡ ዝክሩም፣ በአሁኑ ወቅት በከተሞች አካባቢ እየተረሳ ቢመጣም፣ ዘወትር እሑድ የአንድ አካባቢ ሰዎች ማዕከላዊ በሆነ ቦታ ተሰባስበው በእመቤታችን ስም የሚዘክሩት ነው፡፡ ዐቅመ ደካሞች፣ ድሆችና መንገደኞች ተጠርተው በእመቤታችን ስም እንዲበሉና እንዲጠጡ ይደረጋል፡፡ ይህም ትውፊት እመቤታችን ወደ ኢትዮጵያ በመጣች ጊዜ ኢትዮጵያውያን  አባቶችና እናቶች ያደረጉላትን መስተንግዶ ለማሰብ ነው፡፡

ጾመ ጽጌ ክፍል 1

የጾም ትርጓሜ
የቤተ ክርስቲያናችን የሥርዓት መድብል የሆነው ፍትሐ ነገሥት ጾምን እንዲህ ይተረጉመዋል፡- ጾምሰ ተከልአተ ብእሲ እመብልዕ በጊዜ ዕውቅ በውስተ ሕግ - ጾምስ በታወቀው ዕለት፣ በታወቀው ሰዓት ሰው ከምግብ የሚከለከለው መከልከል ነው፡፡ አንድም ጾም ሰውን ከምግብ መከልከል ነው፡፡ ይህም ኃጢአቱን ለማስተሰረይ፣ ዋጋውን ለማብዛት እርሱ ወዶ ሕግን ለሠራለት እየታዘዘ የፈቲውን ኃይል ያደክም ዘንድ ሥራም ለነባቢት ነፍስ ትታዘዝ ዘንድ ነው፡፡ ፍት.ነገ.ፍት. መ. አንቀጽ 15564፡፡ በዚህ መሠረት ጾም ማለት ከጥሉላተ መባልዕት /ሥጋ ፣ ቅቤ፣ ወተት፣ እንቁላል እንዲሁም የአልኮል መጠጦች/ መታቀብ ነው፡፡