Monday, July 16, 2012

ቤተክርስቲያን እንዴት ተመሠረተች ? ክፍል ፪


ርዕሰ አድባራት አክሱም ጺዮን

 ሕዝቡ በጠቅላላ ገበሬውም ሆነ ነጋዴው የመንግሥትም ባለሥልጣን በሚሠራው ሥራ ሁሉ ባለጸጋ ስለነበር የሮም ግዛት ተወዳዳሪ የሌላት ታላቅ አገር ነበረች፤ ታዲያ ምን ያደርጋል እነዚህ ሁሉ ሀብታት ለሕዝቡ ደስታና ውስጣዊ ዕረፍትን ሊያገኙለት አልቻሉም፡፡ ሁልጊዜ በአካባቢው ከሚሰማው የሽብርና የሁከት ድምጽ የተነሳ ባልታሰበ ቀን እንደመስሳለን በሚል ቀቢጸተስፋ ገዝቶት ነበር፤ ያመልኳቸው ከነበሩ ጣዖታትም አንዳችም የተስፋ ድምጽ አልነበረም፡፡ በቀቢጸ ተስፋ ባሕር ውስጥ ገብቶ የሚማቅቀውና መውጣትም የተሳነው አማኛቸውን ሊያረጋጉት አልቻሉም፡፡ ዳዊት እንደተናገረው ዓይን እያላቸው የማያዩ፤ ጆሮ እያላቸው የማይሰሙ፤ እጅ እያላቸው የማይዳስሱ አፍ እያላቸው የማይናገሩ፤ እግር እያላቸው የማይሄዱ ግዑዛን ናቸውና፡፡ ከዚህም የተነሣ ማለት የሚያመልኳቸው ጣዖታት ሊያረጋጓቸውና ሊረዷቸው ስላልቻሉ ሕዝቡአማልክቶቻችን የዋሃንና ግድ የለሾች ናቸውእያሉ በጣዖታቱ ይዘብት ነበር፡፡ የሰው ልጅ ሥልጣኔም በክፋትና በደግነት መካከል የለውን ልዩነት ለማመልከት አልቻለም፡፡ በዚህም አኳኻን ስለ ሰው ልጅ የወደፊት ዕድል ምንም የተስፋ ጭላንጭል አልነበረም፡፡


ሰው በተፈጥሮው ከወዴት መጣሁ? ወዴትስ ነው የምሔደው? ብሎ ራሱን በራሱ የመጠየቅና የመመርመር ስጦታ ያለው ባለአእምሮ ፍጡር ስለሆነ እነዚህ ጥያቄዎች ሁልጊዜ በፊቱ ይደቀኑበታል፡፡ ነገርግን ለነዚህ ጥያቄዎች ከውስጥ ከራሱም ሆነ ከውጭ ከሌላ አጥጋቢ መልስ ስላላገኘ ከላይ እንደገለጥነው የደስታና የኑሮ ጣእሙንና ምሥጢሩን ሊያውቀው አልቻለም፡፡ በሮም ቅኝ ግዛት ውስጥ የሚኖር ሁሉ በዚህ ሁኔታ በቀቢጸ ተስፋ ስለተሞሉ እነሱም ሆነ ሥርዓተ ማኅበራቸው ጠባቂ እንደሌለው መርከብ አቅጣጫው የማይታወቅ ሆነ፡፡ ሕዝቡን ለማስደሰት በሮም የቴያትር ሰገነት ላይ የሚቀርበው የጨዋታ ዓይነትም እንኳ ደም መፍሰስና መደባደብ ስለነበር በጨለማ ላይ የዛፍና የገደል ጥላ ሲጨመር ጨለማው እንደሚጸና ሰቀቀኑን አባብሶት ነበር፡፡ ሀብታም በሀብቱ ደስታን ለመሸመት አልሆንለት ብሎ ሲጨነቅ ሲጠበብ በዝቅተኛው ሕዝብ ዘንድ ደግሞ ዕጓለማውታንና መበለታትን ወዴት ወደቃችሁ የሚላቸው አልነበረም፡፡ በሽተኞችና ረሀብተኞች ጥርኝ ጥሬ ኩባያ ውኃ የሚላቸው አጥተው በረሀብ ይተላለቁ ነበር፡፡ ሲሞቱም የአውሬ ራት እንጂ የሚቀብራቸው አልነበረም፡፡ በአጠቃላይ ፍርድ ጎደለ፣ ድሃ ተበደለ የሚል ታዛቢ ተመልካች የሌለበት የአስረሽ ምችውና የብላ ተበላ ዘመን ነበር፡፡

የሰው አውሬው ሰው ነው የሚባለው የሮማውያን ተረት የተፈጸመው በዚህ ጊዜ ነበር፡፡ እነ አውግስጦስ ቄሣር የሰላም እመቤት ብለው የሰየሟት ወይም ራሷን ሰላም ብለው የጠሯት ፖክስ ሮማና ፍቅርና ሰላምን አላስገኝላቸውምና ይህ ሁሉ ሁከትና የሽብር ጥላ ባንዣበበት ወራት የቤተክርስቲየን መሠረት የአሕዛብ ብርሃን የእሥራኤል ዘነፍስ ክብር መድኃኒዓለም በሮም ቅኝ ግዛት ሥር በነበረች በፍልስጥኤም ልዩ ስሟ ቤተልሔም በምትባል በይሁዳ ክፍል ተወለደ፡፡ በተወለደም ጊዜ ትንቢት ያልተነገረላቸው ሱባኤ ያልተቆጠረላቸው ከአሕዛብ ወገን የሆኑ ሰብአ ሰገል መድኅን መወለዱን አውቀው ከምድረ አሕዛብ እጅ መንሻውን ወርቅ፣ ዕጣን ከርቤ ይዘውለት መጡ፡፡ ገበሩለትም፡፡ በመድኅን መወለድ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ መላእክትም ተደስተዋል፡፡በሰማይ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይገባዋል፤ በምድርም ሰላምእያሉ ዘምረዋል፡፡

ይህ ሁሉ ባንድ ወገን የነበረው የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ሲሆን በሌላ በኩል የነበረው የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ደግሞ የሚያሳዝን ነበር፡፡ ለምሳሌ ሥርዓተ ኦሪትን ትንቢተ ነቢያትን በሚገባ እንከታተላለን ይሉ የነበሩ ፈሪሳውያን ክንዱ የሚያደቅ ግርማው የሚያንቀጠቅጥ ሮማውያንን አባሮ አገራቸው ፍልስጥኤምን ነጻ የሚያወጣ ኃይለኛ መሲሕ ሲጠባበቁት ሁኖ አልመጣም እንዲያውም ከላይ እንደተገለጠው ዘመኑ የሁከትና የሽብር ዘመን ስለነበር አውግስጦስ ቄሣር ለጸጥታ አጠባበቅ እንዲያመች በየጊዜው ዜጎቹን ሲያስቆጥር ነበርና ድንግል ማርያም ለመመዝገብ ለመቆጠር አገር ጥላ ስንቋን ቋጥራ በሔደችበት ቦታ መጠጊያ እንኳ በሌለበት በተጨናነቀ አካባቢ ከብቶች በሚያድሩበት ቦታ መሲሕ ተወለደ፡፡ በዚያም የሀብታሞች የነገሥታት ልጆች ሲወለዱ በሚነጠፍላቸው ወርቀ ዘቦ ሳይሆን ሉቃስ እንደነገረን እናቱ በጨርቅ ጠቀለለችው፡፡ በዚህ ምክንያት ማለት እነሱ እንዳሰቡትና እንደተጠባበቁት ሆኖ ስላላገኙት ፈሪሳውያንም ሆኑ ሰዱቃውያን መሲሕነቱን አልተቀበሉትም፡፡ በተንኮል እየተመሣጠሩም በማስተማር ጊዜው ብዙ የንቀትና የተላልቆ ከቄሣርም ጋር የሚያጋጭ የፖለቲካ ጥያቄ ይጠይቁት ነበር፡፡

ፈረሳውያን ሙሴን እንወደዋለን ስለሚሉ በነቢያትም ተአምራት ስለሚኮሩ የሙሴንና የነቢያትን አምላክእንደ ሙሴ መና አውርዶ ደመና ጋርዶ እንደ ኤልያስ ዝናም አቁሞ እሳት አዝንሞእንዲያሳያቸው መላልሰው የፈተና ጥያቄ ጠየቁት እሱም ለጠየቁት ሁሉ በቃሉ ትምህርት በእጂ ተአምራት የሚገባ መልስ ሰጥቷል፡፡ በተለይም ሰዱቃውያን በምድር ብቻ እንጂ ከሞት በኋላ ስላለው ሕይወት ስለማያምኑ ስለ ትንሣኤ ሙታን የሚያደናግር ጥያቄ መስሎ የታያቸውን ጠየቁት፡፡ ለዚህም የማያዳግም መልስ ሰጥቷቸዋል፡፡ በፖለቲካም ከሮም መንግሥት ባለሥልጣኖች ጋር ነገሩን ለማያያዝ ስለ ግብር አከፋፈል ማለት ለሮማ ቅኝ ገዥ ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም ሲሉ እነዚሁ ሰዱቃውያን የተንኮል ጥያቄ አቅርበውለት ነበር፡፡ ተንኮላቸውን ስለሚያውቅ፡የቄሳርን ለቄሣር መስጠት ይገባል፤ የእግዚብሔርን ለእግዚአብሔር ስጡአላቸው፡፡ መድኃኒታችን በዚህ በማስተማር ጊዜው የፈሪሳውያንም ኾነ የሰዱቃውያን ሁኔታ ግብዝነታቸውም ከልክ ያለፈ ስለነበር ለጥያቄያቸው መልስ ከመስጠት ጋር ይገሥጻቸው ነበር፡፡ እነሱም በበኩላቸው እሱን ለማጥፋት አድማ ይጎነጉኑበት ጀመር፡፡ የክርስቶስ መወለድና ትምህርቱም ያላስደሰታቸው የቤተ እሥራኤል ተመጻዳቂዎች ብቻ አልነበሩም፡፡ የሮም መንግሥትም በበኩሉ ክርስቶስን በጥላቻ ዓይን ይመለከተው ነበር፡፡ የሮማ ቄሣር ወዳጅ በመሆኑ በገሊላ የነገሠ ሄሮድስ መሲሕክርስቶስበቤተልሔም መወለዱን ከሰብአ ሰገል እንደሰማ የራሱንና መላዋንም የቄሣር ግዛት የሚቀናቀን ንጉሥ የተወለደ መስሎት ደነገጠ፡፡

የመሲሕ መወለድ ስላስደነገጠው ሕፃኑን መሲህ ለመግደል ሙከራ አደረገ፡፡ ነገርግን ሕፃኑ መሲህ የነቢያትን ትንቢት ለመፈጸም ከእናቱ ጋር ወደ ግብጽ ተሰደደ፡፡ የሄሮድስ ሰይፍ በአንገቱ ላይ አልወደቀችም፡፡ ነገር ግን በሄሮድስ ተንኮል ብዙ የገሊላ ሕፃናት በሰይፍ አለቁ፡፡ ደማቸውም እንደ ውኃ ፈሰሰ፡፡ የብዙ እናቶች እንባ በግፍ ፈሰሰ፡፡ ኋላም መሲሕ በማስተማር ጉዞው እንደ ፈሪሳውያንና እንደ ሰዱቃውያን የሄሮድስን ባለ ሥልጣኖችና ራሱንም ሄሮድስን በግብዝነቱ በይፋ ስለሚገሥጸውየጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነውእንደሚባለው በክርስቶስ ላይ ለማደም አመች ሆነ፡፡ ጌታ ግን የሮማ ቅኝ ገዥዎችና የቤተ እሥራኤል የኃይማኖት ሰዎች መሲሕነቱን ባያውቁለትም ለበቀል ሳይሆን ለምሕረት ለመዳን የመጣ እውነተኛ መሲህ እንደመሆኑ መጠን በነቢያት ስለ እሱ የተነገረውን ለመፈጸም ድውያነ ሥጋን በተአምራት ድውያነ ነፍስን በትምህርት እየፈወሰ የማስተማር ሥራውን ቀጠለ፡፡ የቃሉን ትምህርት ሰምተው የእጁን ተአምራት አይተው የአመኑበትን የእግዚአብሔር የጸጋ ልጅ ለመሆን አበቃቸው፡፡ እነሱ ግን ጥላቻቸውን ወደ ግቡ ለማድረስ የተነሱና በሰይጣን የሚገፋፉ ስለሆኑ የርሱ ትሕትናና ፍቅር ቅንዓታቸውን አባባሰው እንጂ አልቀነሰውም፡፡ ስለዚህም በፈሪሳውያንና በሰዱቃውያን ከሳሽነት በሮማውያን ዳኝነት ክስ ተመሠረተበት፡፡ ክሱም ኃይማኖትንና ፖለቲካን የሚመለከቱ ጣምራ ነገሮችን የያዘ ነበር፡፡
የሮማ መንግሥት የዜጎችን እኩልነት ያከብራል እንዲባል በቅኝ ግዛት ውስጥ ለሚገኙ ሕዝቦች ሁሉ የሃይማኖትና የባህል ነጻነት ሰጥቷቸው ነበር፤ አንዱ የሌላውን ሃይማኖት ቢነቅፍና ቢያዋርድ ወይም ከዚያም ከአንዱ ሃይማኖት ውስጥ አንዱ አዲስ ሐሳብ ቢጨምር ወይም ቢቀንስ ራሳቸው እንዲቀጡት ቅጣቱ በሕይወት ላይ የሆነ እንደሆነ ግን ወደ መንግሥት ባለ ሥልጣን አቅርበው እንዲያስፈርዱበት ሕግ ተሠርቶ ነበር፡፡ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያንም በክርስቶስ ላይ ክስ የመሠረቱበት ይህ መብታችን ተነክቷል፤ በቀላል ቅጣት የሚታለፍ ስላልሆነ በሞት ይቀጣልን ብለው ነው፡፡በፖለቲካመንፈስ የተመሠረተበት ሁለተኛ ክስ ደግሞእኛ ያለ ቄሣር ንጉሥ የለንም፡፡ እሱ ንጉሠ አይሁድ ነኝ እያለ ያስተምራል ሕዝቡ ለቄሣር እንዳይገብር ያሳድማልየሚል ነበር፡፡ እንዲህ ማለታቸው በእውነት ፊሪሳውያንና ሰዱቃውየን ለሮማ መንግሥት አስበው አይደለም፡፡ የሮማ ባለሥልጣኖች ነገሩን ይዋል ይደር ሳይሉ እንዲያፋጥኑትና ጉዳዩ ሃይማኖት ብቻ ሳይሆን የሮማንም የአገዛዝ አውታር የሚነቀንቅ ሰለሆነ መንግሥት ለራሱመ ጭምር ሲል ባስቸኳይ ርምጃ እንዲወስድ ለዘዴ ነው፡፡ እነሱ ሰው ሰውኛውን ይህን ያህል ደከሙ እንጂ መሲሕ እንደሆነ በሃይማኖት የሙሴን ሕግ ይሽራል የሚለው ክስ ሳይመሠረትበት በፊትየሙሴን ሕግ ለመፈጸም እንጂ ለመሻር አልመጣሁምእያለ ሲያስተምር እንደነበር በጆሮዋቸው ሰምተዋል፡፡
ክፍል 3 ይቀጥላል ይቆየን

No comments:

Post a Comment