Tuesday, August 21, 2012

††† የማኅበረ በዓለ ወልድ መልዕክት †††


                                             
በጎርፍ ምክንያት የሚሸረሸር መሬት፦ ዝም ካልነው መሬቱ ተሸርሽሮ፦ የመሬቱ ገጽታ ተቀይሮ ፤ ከጥቅም ውጪ ሆኖ ይቀይራል። የመሬቱን መሸርሸር ለማቆም ግድብ መሥራት የግ ይላል። እኛ አሁን መነጋገርና መሥራት ያለብንም መገደብ ያልቻልነው ለምንድን ነው? የት እና እንዴት ነው የምንገድበው? በሚሉት ጉዳዮች ላይ ነው። ከዚያም በኋላ በሌሎች ቦታዎች ላይ ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር በዕቅድ መሥራት እንችላለን። የአጭርና ረዥም ጊዜ ዕቅድ ንድፍ ይዘን የምንጓዝ ከሆነ እንደየአካባቢውና እንደየሁኔታው ለሚፈጠሩ ችግሮች መሠረታዊና ለቦታው የሚስማማ የአሠራር ዘዴዎችን መዘርጋት ቀላል ይሆናል።
እንግዲህ በዚህ ዘመን ያለነው ክርስቲያኖች ከዚህ የምንማረው ምንድን ነው? ከእኛስ የሚጠበቀው እስከምን ድረስ ነው? እስከሞት ድረስ መታመን እንችላለን ወይ? ቤተክርስቲያን እየደረሰባት ያለው ፈተና  እንዴት ሊበዛ ቻለ? መፍትሔውስ ምንድን ነው? በኢትዮጵያ፦ በሰሜን አሜሪካ እና በሌሎች ክፍላተ ዓለማት ብዙ ማኅበራት አሉ፦ በኅብረት መሥራት አይቻልም ወይ? ቤተክርስቲያንን በየጊዜው እየከበባት ያለውን የጥፋት ዘመቻ መግታት የሚቻለው እንዴት ነው? ከሃይማኖታችን ኃላፊነት ግዴታ አንጻር ብዙ ያልሠራነው እኛ ወይስ የሃይማኖት መሪዎች? ዛሬ በየገዳማቱ ላይ በተደጋጋሚ እየደረሱ ላሉት ጥቃቶች ተጠያቂው ማን ነው? መፍትሔዎቻቸውስ? ቤተክርስቲያንን አብዝቶ እየጎዳት ያለው የውስት ወይስ ከውጪ የሚመጣ ፈተና? የቤተክርስቲያን ጠላቶች ዓላማ ግልፅና  የታወቀ ሲሆን መግታት ያልቻልንበት በምን ምክንያት ነው? በሰከነ  ልብ፦ በበሰለ አዕምሮ ፦ በለዘበ አንደበት፦ የቤተክርስቲያንን ጥቅም ባማከለ ሁኔታ እስኪ እንነጋገር፦ እንመካከር፦ እንጸልይ። በነገር ሁሉ እግዚአብሔር ማስተዋሉን ይስጠን! አሜን! ፪ ጢሞ ፪፡፯


ስለቤተክርስቲያን ስናስብ፦ ስለሃይማኖታችን ጉዳይ ስንነጋገር ወደ ሰላም መንገድ የሚያቀናውን፦ እርስ በርሳችን የምታንጽበትን፦ ወደ ክብሩ ሙላት ሊያደርሰን የሚችለውን የአንድነትን መንገድ ብቻ ማሰብ እንዳለብን ልንገነዘብ ያስፈልጋል። የቤተክርስቲያንን ወይም የሃይማኖታችንን ጉዳይ መመዘን ያለብን ከእኛ ፍላጎትና የግል ጥቅም አንጻር ሳይሆን የእግዚአብሐር ቃል ከሚነግረን ሐሳብና ዓላማ፦ የቤተክርስቲያንን ሥርዓትና ትውፊት በሚጠብቅ ሁኔታ ሊሆን ይገባል። በቤተክርስቲያንና ማኅበራት መካከል መለያየትን መፍጠር ራሳችንን ጎድተን የጠላት መሳለቂያ ከመሆን ያለፈ ሌላ ጥቅም ሊኖረው አይችልም። በእግዚአብሔር ዘንድም የተወደደ አይደለም። መጽሐፈ ምሳሌ፮፡፲፮ -፲፱
መመላለሳችን እግዚአብሔርን በመፍራትና ለእግዚአብሔር በመገዛት እንጂ ለከንቱ ውዳሴና ለታይታ፦ ሰዎችንም በመፍራት አይሁን። ዛሬ የጨለማ ሠራዊት በሙሉ ትጥቅን ኃይል የቤተክርስቲያንን ሕልውና ሲፈታተን፦ የብርሃን ልጆች በዝምታና በቸልተኝነት ልንቀመጥ የተገባ አይደለም። የጥቃት ስልቱን በማጥናት ተገቢ የሆነ መከላከል ማድረግና ቤተክርስቲያንን ከዘመናዊ የጠላት ወረራ መታደግ አማራጭ የሌለው የዚህ ዘመን “ትውልድ” ኃላፊነትና ግዴታ ነው። “ትውልድ” የተባለውም የቤተክርስቲያንን ጥሪ ተቀብሎ ለትድግናዋ የሚቆምና የሚሠለፍ የእውነት ሠራዊት ማለት ነው። ይህ “ትውልድ” እግዚአብሔር በአንድም በሌላም መንገድ ቤተክርስቲያንን እንደሚታደጋት የሚያምን፦ አሁን በቤተክርስቲያን የሚያንዣብበው የፈተና ጭጋግና ውሽንፍር በሚታዩትና በማይታዩት የእግዚአብሔር ሠራዊት ድል ሆኖ፤ ቤተክርስቲያን ፍፁ ም ትንሣኤን እንደምታገኝ፦ ሥርዓቷና ትውፊቷ እንደተጠበቀ “ለትውልዶች” እንደሚተላለፉ የሚታመን፤ ለዚህም መሳካት ወገቡን በወንጌል ዝናር ታጥቆ ፦ የወንጌልን ጋሻ ይዞ፦ የሚንበለበለውን የጠላት ፍላፃ ለመመከት ሁሌም ዝግጁ የሆነ፦ በጉልበቱ፦ በጊዜው በሐብቱና ባለው ነገር ሁሉ የክርስቶስን ቤተክርስቲያን የሚያገለግል “ትውልድ” ነው፡፡
በመሆኑም ይህን እንላለን፦ ዝምታው ይብቃ! የተኛ ይንቃ። ማኅበራት በአንድነት ለመሥራት ይነጋገሩ። የትኩረት አቅጣጫችን በመስቀል ዓላማ ላይ የተመሠረተ  ይሁን። ጽኑና የማይነቃነቅ እምነት፦ የማይጠወልግ ተስፋ፦ ጨለማ የ ሚያሸንፈው ራዕይ ይኑረን፤ የሕይወትና የትንሣኤ ጌታ ድካማችንንና መቃተታችንን ይመለከታል፦ ሊረዳንም የታመነ ነው። በሊቀ ነቢያት ሙሴ መንፈስና ኃይል፦ ፈርዖናውያንን ድል እናደርጋለን የማይቻል መስሎ የሚታየውን ፊት ለፊታችን የተንጣለለውን የቤተክርስቲያን ችግር - ባሕረ ኤርትራን ከፍለን እንሻገራለን፤ በእልልታም እንዘምራለን። በነቢዩ ኤልያስ መንፈስና ኃይል ከታመንን የምሕረት ዝናብ ይወርድልናል፤ በቤተክርስቲያን ጉዳይ ተሟጦ የነበረው የምዕመናን የተስፋ ማጣት - ረሐብ ጋብ ይላል፦ የበአል በቢያት ይወድቃሉና! ይህንን ማመንና መቀበል ይጠበቅብናል።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
እግዚአብሔር ሐገራችንን እና ቤተክርስቲያናችንን ይጠብቅልን! አሜን!
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ማኅበረ በዓለ ወልድ ትምህርት ክፍል
ሰሜን አሜሪካ አህጉረ ስብከት ሐምሌ ፳፩ ፳፻፬ ዓ.ም.
አትላንታ  

No comments:

Post a Comment