Thursday, January 26, 2012

ኪዳነ ምህረት



እግዝእትነ ማርያም
 ኪዳነ ምህረት ማለት የምህረት መሐላ ማለት ነው፡፡ 33 በዓላተ እግዝእትነ ድንግል ማርያም አንዱ ነው፡፡ እመቤታችንም ከጌታችን መቃብር እየሄደች በምትለምንበት ጊዜ አይሁድ ለምቀኝነት አያርፉምና ምን ልታመጣብን ነው በማለት ሊጣሏት ሲመጡ ጌታችንም ከዓይናቸው ሰውሯታል አይሁድም ጠባቂ ቢያቆሙ እመቤታችን ዕለት ዕለት መሄዷን አላቋረጠችን እመቤታችንም እንዲህ ብላ ስትጸልይ ልጄ ወዳጄ ሆይ ከስጋዬ ስጋ ከነፍሴ ነፍስ ነስተህ ሰው በመሆንህ ዘጠኝ ወር 5 ቀን በቻለችህ ማሕጸኔ ከአንተ ጋር ሀገር ለሀገር ስለ መሰደዴ መትተህ ልምናዬን ትሰማኝ ዘንድ እለምንሃለሁ አለች በዚህ ጊዜ ንውጽውጽውታ ሆነ መቃብራት ተሰነጣጠቀ ጌታችንም እልፍ ከእልፍ መላዕክቱ ጋር መጥቶ ሰላም ለኪ ማርያም ምን እንዳደርግልሽ ትለሚኚኛለሽ አላት፡፡ እርሷም መታሰቢያዬን ያደረገውን ስለ ስሜ ለችግረኛ የሚራራውን በስሜ ቤተ ክርስቲያን ያነጻውን መባዕ የሰጠውን ከሃይማኖት ከፍቅር ጽናት ልጁን በስሜ የጠራውን ሁሉ ማርልኝ ከሞተ ስጋ ከሞተ ነፍስ አድንልኝ አለችው፡፡ ጌታችንም ይህን ሁለ እንዳደርግልሽ መሐልኩ ለኪ በርእስየ ወበ አቡየ ሕያው ወበመንፈስ ቅዱስ ብሎ ቃል ገብቶላት አርጓል፡፡ 

'ኪዳን' የሚባለው ቃል «ቃል» ከሚለው ጋር እየተቀናጀ በብሉይ ኪዳን 280 ጊዜ ያህል ሲጠቀስ በአዲስ ኪዳን ደግሞ 33 ጊዜ በላይ ተጠቅሷል፡፡ «ኪዳን» ቃሉ «ተካየደ» ተማማለ፣ ቃል ተገባባ ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ነው፡፡
«ምሕረት» የሚለው ቃል ደግሞ ማብራሪያ ሳያሻው ምሥጢሩ ከነዘይቤው ከግእዝ የተወረሰ ነው፡፡ ስለዚህ ኪዳነ ምሕረት ማለት የምሕረት፣ የይቅርታ ውል፣ ስምምነት፣ መሐላ ማለት ነው፡፡ ኪዳን ከተራ ውሎችና ስምምነቶች የበለጠ ጽኑና ቀዋሚ ነው፡፡ ከፍ ያለ ክብደትም አለው፡፡

«ከመረጥኳቸው ጋር ቃል ኪዳኔን አደርጋለሁ» ተብሎ በዳዊት መዝሙር እንደተጻፈ እግዚአብሔር ከመረጣቸው ቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ቃል ኪዳን አድርጓል፡፡ ወደ ፊትም ያደርጋል፡፡ /መዝ. 88÷3/ ቃል ኪዳኑም የምሕረት ቃል ኪዳን ነው፡፡ በቅዱሳን አበውና በቅዱሳት እማት/እናቶች/ ታሪክ፣ ገድልና ድርሳን እንደምናነበው እግዚአብሔር ለቅዱሳን ከመሞታቸው አስቀድሞ ይገለጥላቸዋል፤ የምሕረት ቃል ኪዳንም ይሰጣቸዋል፡፡ የእግዚአብሔር የምሕረት ቃል ኪዳን በቅዱሳኑ ሕይወት ዙሪያ ብቻ የሚያተኩር አይደለም፡፡ ለስማቸው፣ ለመስቀላቸው፣ ለልብሳቸው ገድላቸውን ለያዘ መጽሐፍ፣ አልፎ ተርፎም ለረገጡት አፈርና ለተጋደሉበት ቦታ ሁሉ ተርፎላቸዋል፡፡ ስለዚህ ልዩ ልዩ ቃል ኪዳን የተገባላቸው ቅዱሳት መካናት ሞልተዉናል፡፡

 ለቅዱሳን ከሞት አስቀድሞ የእግዚአብሔር መገለጥ ወይም የሚሞቱበትን ጊዜና የአሟሟታቸውን መንገድ ገልጦ መንገር በቅዱሳት መጻሕፍት የተለመደ ነው እንጂ እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ ጌታ ለቅዱስ ጴጥሮስ እንዴት ባለ አሟማት እንደሚሞት ነግሮታል፡፡ /ዮሐ.21÷39 2 ጴጥ.1÷14/ ለቅዱስ ጳዉሎስ ስለሚሞትበት ጊዜ ተነግሮታል፡፡ /የሐዋ.20÷25 21÷10-13/ «ከሞቱ አስቀድሜ እገለጥለታለሁ» እንዲል፡፡ /ሰኔ ጎልጎታ/፡፡

እግዚአብሔር ከሞታቸው አስቀድሞ በመገለጥ ለቅዱሳን የምሕረት ቃል ኪዳን የሚሰጣቸው በእነርሱ በጎ ሥራ ከእነርሱ በኋላ ያሉ የሰው ልጆችን ለመጥቀም ፈልጎ ነው፡፡ ተጠቃሚዎቹ ራሳቸው ናቸው እንዳይባል ወደ ሞት አፋፍ የተጠጉ ከመሆናቸውም ባሻገር ለቃል ኪዳን የበቁት የሚጠቀሙበት በጎ ሥራ በመሥራታቸው ነው፡፡ የሰው ልጆች ያለፉ ቅዱሳንን በመዘከር የቃል ኪዳናቸው ተጠቃሚ ሲሆኑ ቅዱሳኑ ግን ከመታሰብ በቀር በሰው በኩል የሚጨመርላቸው የለም፡፡ ቅዱሳን የምሕረት ቃል ኪዳን ሲቀበሉ ለወገናቸው መትረፋቸውን እንረዳለን፡፡

የምሕረት ቃል ኪዳን ለምን ያስፈልጋል ቢባል ሕግ መተላለፍ ካለ ሁልጊዜ ተጠያቂነት ወይም ቅጣት ይኖራል፡፡ ይህም በአዳም ይታወቃል፡፡ የሰው ልጆች ደግሞ ከተጠያቂነት ነጻ የሚያደርግ አኗኗር ይዘው አይገኙም፡፡ በዚህ ምክንያት ቅጣት እንዳያገኛቸው የሚድኑበትን በርካታ መንገዶች እግዚአብሔር አዘጋጀ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ የምሕረት ቃል ኪዳን ነው፡፡
የምሕረት ቃል ኪዳን ሁሉ በጎ እንድንሠራ የሚያበረታታ ነው፡፡ ይህም ዘወትር ከቃል ኪዳኑ ጋር ተያይዘው በሚቀመጡ ግዴታዎች ይታወቃል፡፡ ለበጎ ሥራ ምክንያት የማይሆን ባዶ የምሕረት ቃል ኪዳን የለም፡፡ «ስምሸን /ስምህን/ የጠራውን፣ ዝክር ያዘከረውን፣ የተራበ ያበላውን፣ የተጠማ ያጠጣውን፣ የታረዘ ያለበሰውን፣ እንግዳ በስምህ /በስምሽ/ የተቀበለውን፣ ገድልህን ያነበበውን፣ የሰማውን፣ የተረጎመውን ወዘተ ኃጢአቱን ይቅር እለዋለሁ፣ እምረዋለሁ» የሚሉ ቃል ኪዳናት በሙሉ ከባዱን መልካም ሥራ መፈጸም ባይቻለን እንኳን ቀላሉን መሥራት እንዳለብን ግዴታ የሚጥሉ ናቸው እንጂ አንዳንዶች እንደሚያስቡት መልካም እንዳንሠራ የሚያሳንፉ አይደሉም፡፡ ከዚህ ይልቅ ለበጎ ሥራ የሚያነሣሡና የታዘዙትን መሥራት ያልተቻላቸውን ሰዎች ተስፋ ሳይቆርጡ እስከ መጨረሻው ሰዓት የሚድኑበት መንገድ እንዳለ አውቀው የተቻላቸውን እንዲያደርጉ የሚጠቁሙ ናቸው፡፡

የእግዚአብሔር ቸርነት ከአእምሮ በላይ ነው፡፡ ይህም ሰዎች በእግዚአብሔር ቸርነት ላይ በሚያነሡት ጥያቄ ይታወቃል፡፡ ለምሳሌ በየዜና ገድላቸው እንደምናነበው እግዚአብሔር ለብዙ ቅዱሳን «እስከ አሥር፣ ሠላሳ፣ ሃምሳ አምስት ወዘተ ትውልድ ድረስ እምርልሃለሁ» እያለ የምሕረት ቃል ኪዳን ሰጥቷቸዋል፡፡ ይህን በማንበብ እምነት የጎደላቸው አንዳንዶች «ይህ እንዴት ይሆናልእያሉ ይጠይቃሉ፡፡ ይህ ብቻ በራሱ የፈጣሪ ቸርነት ከሕሊና በላይ መሆኑን አያስረዳምን ?

ፈጣሪ ስለ ፈራጅነቱና ስለ መሐሪነቱ ሲናገር «በሚጠሉኝ እስከ ሦስተኛና አራተኛ ትውልድ ድረስ የአባቶችን ኃጢአት በልጆች ላይ የማመጣ ለሚወዱኝ ትእዛዜን ለሚጠብቁ እስከ ሺሕ ትውልድ ድረስ ምሕረትን የማደርግ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝ፡፡» ይላል፡፡ /ዘጸ.20÷2-6/ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እስከ ሺሕ ትውልድ የሚደርስ የእግዚአብሔርን ምሕረት መናገሩ በአዋልድ መጻሕፍት ላይ ያለው የሠላሳና የሃምሳ ትውልድን ምሕረት የሚያወሳው ኃይለ ቃል ሊስተባበል አለመቻሉን ያሳያል፡፡ ያን ማክፋፋት ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እንደመቃወም ይቆጠራል፡፡

ዓለም ከተፈጠረች ሰባት ሺሕ አምስት መቶ ዓመት ገደማ ሊሆናት ነው፡፡ የሰው ልጅን አማካይ እድሜ እጅግ አሳንሰን በመቁጠር የአንድ ትውልድ ዘመን ሠላሳ ዓመት ነው ብንል እንኳን ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ያለው ትውልድ ከሁለት መቶ ሃምሳ አይበልጥም፡፡ ነገር ግን ፈጣሪ የሚወደውና ትእዛዙን የሚጠብቅ እውነተኛ ሰው ከተገኘ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ያን ያህል ትውልድ እስከዓለም ፍፃሜ የሚኖር ከሆነም «እስከ ሺሕ ትውልድ» ድረስ እንኳን ይቅር ሊል ቃል ኪዳን ገብቷል፡፡ ይህ የሚያሳየው የእግዚአብሔርን የቸርነት ስፋት ነው፡፡ ሺሕ ትውልድ ባይኖር እንኳን ሺሕ ትውልድ ስለሌለ እግዚአብሔር ሺሕ ትውልድ ሊምር አይችልም አይባልም፡፡ ስለዚህ የፈጣሪን ቃል ኪዳን ከመሐሪነቱ አንጻር እንጂ ከዓመታቱ መብዛት አንጻር ሊመለከቱት አይገባም፡፡

ፈጣሪ ለቅዱሳኑ በየዕለቱ ብዙ ነፍሳትን ከሲዖል እንዲያወጡ የምሕረት ቃል ኪዳን ሊሰጣቸው ይችላል፡፡ የተሰጣቸውም ቅዱሳን አሉ፡፡ ነገር ግን ተፈጻሚነቱን ስንመለከት በቀን የተባለውን ያህል ነፍሳት ከሲዖል ሊወጡ ወይም አንድም ነፍስ ከሲዖል ላትወጣ ትችላለች፡፡ ይህ ግን በተገባላቸው ቃል ኪዳን ላይ ምንም ዓይነት አሉታ የለውም፡፡ ምክንያቱም ለቅዱሳኑ ይህ ቃል ኪዳን ሲሰጥ ሲዖል ካለችው ነፍስ ደግሞ የሚጠበቅ ነገር ይኖራልና፡፡ ያን የምታሟላ ነፍስ ካልተገኘች ኪዳኑ ተፈጻሚ አይሆንም፡፡ ይህም በመሆኑ ቃል ኪዳኑ ከንቱ ነው አይባልም፡፡ ከላይ እንዳየነው ተፈጻሚ ሊሆን ባለመቻሉ ብቻ ለሺሕ ትውልድ የተገባው ቃል ኪዳን ከንቱ ነው ሊባል አይቻልምና፡፡

ስለዚህ ምእመናን ቅዱሳን የተገባላቸው ቃል ኪዳን ለሰው ልጆች የተሰጠ የመዳን ጸጋ መሆኑን መረዳት ይገባቸዋል፡፡ በኃጢአት ወድቀን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ፍርድ ፊት የሚያፍር ነፍስ እንዳለን ስንረዳ ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ ለወዳጆቹ ስለገባው ቃልኪዳን ብሎ እንዲምረን መማጸን ይገባል፡፡«ከመረጥኳቸው ጋር ቃል ኪዳኔን አደርጋለሁ» ባለው መሠረት ጌታ ከእመቤታችን ጋር ብዙ ቃል ኪዳን አድርጓል፡፡ እርሷ የተመረጠች ብቻ ሳትሆን ከተመረጡትም ሁሉ የተመረጠች ናትና፡፡ ከቅዱሳን ሁሉ እመቤታችን ድንግል ማርያም በሁሉም ረገድ ስለምትበልጥ ከተሰጣቸውም የምሕረት ቃል ኪዳን ለሷ የተሰጣት ኪዳን ኪዳነ ምሕረት ተብሎ ተለይቶ ይታወቃል፤ ማለትም ትጠራበታለች፤ ኪዳነ ምሕረት ትባላለች፡፡ ስለዚህ የኃጥአን ሁሉ ዓይን የእርሷን የምሕረት ቃል ኪዳን ተስፋ ያደርጋል፡፡ የሚገባቸውን ሁሉ አድርገው ላወቁትና ላላወቁት ጉድለቶቻቸው ሁሉ ስሟን ለሚጠሩ ቃል ኪዳንን ለመቀበል ያበቃትን ለሰው ልጆች ነጻነት ልጇ ለሰጠው ፍፁም መድኃኒት ምክንያት የሆነችበት ጸጋዋ ሁሉ በሥላሴ ፊት ይታሰብላቸዋል፡፡

አመአምላክ ቅድስት ድንግል ማርያም በቃል ኪዳኗ አትለየን!

ስብሐት ለአበ፣ስብሐት ወወልድ፣ስብሐት ወመንፈስቅዱስ።አሜን

No comments:

Post a Comment