Monday, October 22, 2012

ዘመነ ጽጌ - ክፍል አንድ

[ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 6]

"ልጄን ከግብፅ ጠራሁት"   (.ሆሴዕ 111 )

ከመምህር ዮሐንስ  ለማ

እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ  ቤተክርስቲያን  ሕግና ስርአት መሰረት ከመስከረም 26 ቀን  እስከ ሕዳር 6 ቀን  ያለው 40 ቀን  የእመቤታችንን እና የልጇን ስደት በማሰብ ወርኃ ጽጌን (ዘመነ ጽጌን) ታከብራለች፡፡ ይህ 40 ቀን የእመቤታችንና የጌታችን ስደት የሚታሰብበት ዘመን ነው፡፡ ወቅቱ የአበባና የፍሬ ወቅት በመሆኑ እመቤታችን በአበባ ጌታችን በፍሬ እየተመሰሉ ጌታችን በአምልኮት እመቤታችን በፈጣሪ እናትነቷ በተለየ ምስጋና ይመሰገናሉ ፡፡

 በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሳው ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ አምሥቱን ጸዋትወ ዜማ ሲደርስ 14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሳው አባ ጊዮርጊስ ደግሞ ሰዓታትን ደርሷል፡፡ በዚሁ ዘመን ከአባ ጊዮርጊስ ጋር ጥልቅ መንፈሳዊ ፍቅር የነበረው አባ ጽጌ ድንግል  ማኅሌተ ጽጌ  የተባለውን ድርሰት ደርሷል፡፡  ማኅሌተ ጽጌ ግጥማዊ አካሄድ ያለው ድንቅ ኢትዮጵያዊ ድርሰት ሲሆን  ይህ ድርሰት በማንኛውም ጊዜ የሚጸለይ ቢሆንም በተለየ ሁኔታ ወቅት ተለይቶለት በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ላይ የሚውለው ግን   በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና በልጇ የስደት ዘመን  ማለትም  ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 5 ቀን ድረስ ባለው  ዘመን ውስጥ ነው፡፡ በዚህ ወቅት በየሳምንቱ እሑድ ሌሊቱን በሙሉ የእመቤታችንን ከልጇ ጋር ወደ  ምድረ ግብፅ መሰደድና መንከራተት እየታሰበ በሊቃውንቱ  የሚደርስ የምሥጋና ጸሎትም  ነው ፡፡ ይህ ድርሰት በግጥም መልክ የተደረሰ  ሲሆን በአብዛኛው አምስት ስንኞች ሲኖሩት ብዛቱም 158 ያክል ነው፡፡ እመቤታችን ጣዕሟንና ፍቅሯን እንዲሁም ምስጋናዋን ሲናፍቁ የነበሩትን ቅዱስ ኤፍሬምንና አባ ሕርያቆስን ውዳሴዋንና ቅዳሴዋን እንደገለጸችላቸው  ሁሉ ለፍቅሯ ሲሳሳ ለነበረው ለአባ ጽጌ ድንግል ደግሞ ይህንን የማኅሌተ ጽጌን ድርሰት  እንዲደርስ ምስጢርን ገልጻለታልች


 በቅድስት ሐገር ሐገረ እግዚአብሔር ኢትዮጵያ  የመስከረምና የጥቅምት ወራት የአበባ ወራት ወርኅ ጽጌ (ዘመነ ጽጌ) ናቸው፡፡ ይህም ወቅት ተራሮች በአበባ የሚያጌጡበትና ለዓይን ማራኪ የሚሆኑበት ጊዜ ነው፡፡ በዚህም ዘመን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‘’ ስለ ልብስ ስለምን ትጨነቃላችሁ ? የሜዳ አበቦች እንዴት እንዲያድጉ ልብ አድርጋችሁ ተመልከቱ፡፡ አይደክሙም፣ አይፈትሉም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፣ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከእነዚህ እንደ አንዱ አልለበሰም፡፡ እግዚአብሔር፣ ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን የሜዳን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ፣ እናንተ እምነት የጐደላችሁ፣ እናንተንማ ይልቁን እንዴት፡፡ እንግዲህ ምን እንበላለን፣ ምንስ እንጠጣለን፣ ምንስ እንለብሳለን ብላችሁ አትጨነቁ ‘’ (ማቴ 5÷28-33) በማለት የተናገረውን ቃል በማሰብ መጨነቅ የሚገባን መንግሥተ ሰማያት ለመግባት እንጂ በዚህ ዓለም ስላለው ነገር እንዳልሆነ ተራሮችን በአበባ ያለበሰ አምላክ በአርአያውና በአምሳሉ የፈጠረንን እኛን ለኑሮ የሚያስፈልገንን ምግብና ልብስ እንደማይነሳን እያሰብን የምንዘክርበት ወቅት ነው፡፡

የሊቁ  ድርሰትም ፍሬ ከአበባ÷ አበባም ከፍሬ እንደሚገኘ ሁሉ ማኅሌተ ጽጌም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምንና ልጇን መድኃኒታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስን በአበባና በፍሬ እየመሰለ የሚያስረዳ ድርሰት ነው፡፡ እርሷን በአበባ ሲመስል ልጇን በፍሬ እርሷን በፍሬ ሲመስል  ልጇን ደግሞ በአበባ እየመሰለ ይናገራል፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስትወጽእ በትር እምሥርወ እሴይ፣ ወየዓርግ ጽጌ እም ጕንዱ - ከእሴይ ግንድ በትር ይወጣል፤ ከሥሩም ቁጥቋጦ ያፈራል “(ኢሳ . 11÷1) ብሎ ከእሴይ ዘር የምትገኘውን እመቤታችንን በበትር ከርሷ የሚገኘውን ክርስቶስን ደግሞ በጽጌ መስሎ ትንቢቱን ተናግሯል፡፡ አባ ጽጌ ድንግልም ድርሰቱን በዚሁ አንጻር በመቀመር እያንዳንዱን መልክዕ እመቤታችንንና ልጇን አስተባብሮ በጽጌና በፍሬ በመመሰል፣ ከዚያው በማያያዝ የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ በምሥጢር፣ በታሪክ፣ በጸሎትና በመሳሰለው መልክ ድንቅ በሆነና በተዋበ ሁኔታ አዋሕዶ ደርሶታል፡፡

ሊቁ አባ ጽጌ ድንግል በማኅሌተ ጽጌ ድርሰቱ እመቤታችንን በአበባ እየመሰለ ከተናገረው   ድርሰቱ መሐከል አንዱ  “ ማዕረረ ትንቢት ማርያም ዘዘመነ ጽጌ እንግዳ ወዘመነ ፍሬ  ጽጋብ  ዘዓመተ ረኃብ ፍዳ  ብኪ ተአምረ ዘይቤ ኢዩኤል ነቢየ ኤልዳ ያንጸፈጽፍ እምአድባሪሁ ወእምአውግሪሁ ለይሁዳ  ፀቃውዐ   መዓር  ቅድው  ( ጥዑም ) ወሀሊብ ፀዓዳ ”  በመከር ጊዜ አበባ፣ በአበባ ጊዜ ደግሞ መከር አዝመራ ማጨድና መሰብሰብ የለም፡፡ ምክንያቱም ጊዜያቸው የተለያየ ስለሆነ፡፡ ለምሳሌ በመስከረም ወር የአበባ ጊዜ በመሆኑ አዝመራ መሰብሰብ የለም፡፡ የትንቢት መከር መካተቻ የሆንሽ እንደ ዘመነ ጽጌ የረሃብን ዘመን ያስወገድሽ ማርያም ሆይ፣ የኤልዳ ነቢይ ኢዩኤል ከይሁዳ ተራሮች ጣፋጭ ማርና ፀዐዳ ወተት ይፈሳል ብሎ የተናገረው ትንቢት በአንቺ ታወቀ፣ ተፈጸመ ፡፡ እመቤታችን ነቢያት የተናገሩት የትንቢት ዘር ተፈጸመባት፡፡ ማለትም ነቢያት የአምላክን ሰው የመሆን ነገር በተለያየ ሁኔታ ተናግረዋል፡፡ ጌታችን ነቢያት የተናገሩት ትንቢት መፈጸሙንና ይህንን ፍጻሜ ለማየት የታደሉት ሐዋርያት መሆናቸውን ‘’አንዱ ይዘራል አንዱም ያጭዳል ‘’ የሚለው ቃል እውነት ሆኗል፡፡ እኔም እናንተ ያልደከማችሁበትን ታጭዱ ዘንድ ሰደድኳችሁ፡፡ ሌሎች ደከሙ እናንተም በድካማቸው ገባችሁ በማለት ተናግሮአል (ዮሐ.4÷37-38)፡፡ ይህም ነቢያት የዘሩት ትንቢት በሐዋርያት ዘመን ለአጨዳ ለፍሬ መድረሱን መናገሩ ነው፡፡ ስለሆነም ‘’ማዕረረ ትንቢት ‘’ የትንቢት መካተቻ ማርያም አላት፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ፍሬ ክርስቶስን ያስገኘችና ከእሴይ ሥር በትር ትወጣለች እየተባለ የተነገረላት በመሆንዋ ድንግል ማርያም  በአበባ ትመሰላለች፡፡

ስለዚህ እመቤታችን በመከር ወራት የምትገኝ አበባ ናት፡፡ በመከር ጊዜ የአበባ መገኘት ያልተለመደ ስለሆነ  ‘’ወዘመነ ጽጌ እንግዳ ‘’  እንግዳ የሆነ አበባ አላት፡፡ ከዚህ በኋላ ‘’ብኪ ተአምረ ዘይቤ ኢዩኤል ነቢየ ኤልዳ፣ ያንጸፈጽፍ እምአድባሪሁ ወእምአውጋሪሁ ለይሁዳ፣ ፀቃውዓ መዓር ጥዑም ወሀሊበ ፀዓዳ ‘’ በማለት ነቢዩ ኢዩኤል የተናገረውን ትንቢት አፈጻጸም ይናገራል፡፡ ነቢዩ ኢዩኤል በዘመኑ ጽኑ ረኅብ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ሕዝቡን በምሕረት እንደሚጐበኛቸውና ረሃቡ እንደሚጠፋ ይነግራቸው ነበር፡፡ ‘’ብዙ መብል ትበላላችሁ÷ ትጠግቡማላችሁ፣ ከዚህ በኋላ እንዲህ ይሆናል፣ ተራሮች በተሃ ጠጅ ያንጠበጥባሉ÷ ኮረብቶችም ወተትን ያፈስሳሉ÷ በይሁዳም ያሉት ፏፏቴዎች ሁሉ ውኃን ያጐርፋሉ ‘’ (ኢዩ 3÷18 2÷26)

በዚህ በወርኃ ጽጌ ( በዘመነ ጽጌ )   የሚጾሙ ክርስቲያኖች ሲኖሩ ጾመ ጽጌ መንፈሳውያን ሰዎች ሳይታዘዙ በራሳቸው ፈቃድ የሚጾሙት ጾም ነው፡፡ ወይም የትሩፋት ጾም ይባላል፡፡ በቀኖና ከታዘዙት 7 አጽዋማት ውጪ ትርፍ ጾም ማለት ነው፡፡ ከታዘዘው አትርፎ የጾመ ሰው የመጾሙን ዋጋ ያገኛል፡፡ ብዙ መንፈሳዊ ሥራ የሰራ ሰው ብዙ ክብር እንደሚያገኝ መጽሐፍ ይናገራል፡፡ ‘’እጅግ ወዳለችና ብዙ ያለው ሐጢአትዋ ተሰርዮላታል፡፡ ጥቂት ግን የሚሰረይለት ጥቂት ይወዳል’’ (ሉቃ. 747) የጽጌን ጾም የሚጾሙ ሰዎች በክብርም ከእመቤታችን ጋር ይተባበራሉ፡፡ ነገር ግን የጽጌን ጾም የሚጾሙ ሰዎች ለመመጻደቅ መጾም የለባቸውም፡፡ የማይጾሙ ሰዎችንም መንቀፍና መክሰስ የለባቸውም፡፡ የጽጌ ጾም እንዲጾም በቀኖና ቤተክርስቲያን ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ ተደርጎ ስላልተወሰነ የማይጾሙ ሰዎች ሕገ ጾምን እንዳፈረሱ አድርጎ መውሰድ ስሕተት ነው፡፡ ይልቁንም የሚጾሙ ሰዎች ቢችሉ መጾማቸው እንዳይታወቅባቸው ቢያደርጉ የተሻለ ነው፡፡ "ስትጾሙ እንደግብዞች አትጠውልጉ"  (ማቴ. 616 ) የተባለው ለዚህ ዓይነቱ ጾም ነው፡፡

ጽጌ ማለት አበባ ማለት  ሲሆን  ምድሪቱ  በአበባ  የምትሞላበት ጊዜ በመሆኑ አበው ሊቃውንት እመቤታችንን በብዙ ኅብር መስለዋታል፡፡ በአበባ /ጽጌ/ በወይን ሐረግ፣መልካሙን የወይን ፍሬ አስገኝታለችና አበባ ፍሬን እንዲያስገኝ ድንግል ማርያምም ለሰው ያልተቻለውንና የማይቻለውን አንዴ ብቻ የሆነውን መለኮትን በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት በማህፀንዋ ወሰነችው ፡፡   አዳምና ልጆቹ እንዳይበላ በተከለከለችዋ ፍሬ ምክንያት ገነትን ከሚመስል ቦታ እግዚአብሔርን ከሚያክል ጌታ ተለዩ የሰው ልጅ ድቀት ተጀመረ ሁሉን አጣ የመጀመሪያ በደል /ጥንተ አብሶ/ ማለት ይህ ነው፡፡ የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር የመለየትን ረጅም ግዜን ገፋ ገዥ የነበረው የሰው ልጅ ተፈጥሮ ሰለጠነበት፣ ጠላት በዛበት፣ ምድሪቱ ከፋችበት አዳምም ባለቀሰው መሪር እንባ 5500 ዘመን ሲፈጸም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሐልሁ የሚል ተስፋ ተሰጠው የህይወት ፍሬንም ዳግም እንዳይበላ በሱራፊ ታጠረችበት፡፡ ይህም የሚያመላክተው ሞትን የምታመጣ ዕፀ በለስን የበላ አዳም ደግሞ ዕፀ ህይወት ቢበላ ኖሮ ካሳ የማያስፈልገው ኢመዋቲ (immortal sinner) እንዳይሆን የእግዚአብሔር ቸርነት ከለከለችው፡፡

የጨለማ ዘመን ፍጹም ተስፋ ያልጠፋበት ፍጹምም ተስፋ ያልተፈጸመበት ዘመን ነበር፡፡ እግዚአብሔር ከአዳም ጀምሮ ለአርእስተ አበው ቃል ኪዳን ይገባ ነበር፡፡ በዚህም ቃል ኪዳን ውስጥ እመቤታችን በተስፋ አበው ውስጥ ታልፍ ነበረ ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በድጓ "ማርያምሰ ተሐቱ ውስተ ከርሱ ለአዳም ከመ ባህርይ ጸአዳ ማርያምም በአዳም አብራክ ውስጥ እንደ ነጭ ዕንቁ ታበራ ነበር" በማለት ገልጦአታል፡፡ ነገር ግን የአበው ተስፋ፣ የነቢያት ትንቢት ሲፈፀም የድንግል ማርያም የህይወት ፍሬ /በገነት ተከልክላ የነበረችው የገነት ፍሬ/ አማናዊው ጌታ የሚበላ የሕይወት ፍሬ ሆኖ ከእመቤታችን ተወለደ ቅዱስ ኤፍሬም በሐሙስ ውዳሴ ማርያም ሲናገር ‘’ ከፈለነ ንብላዕ እምዕጸ ሕይወት ዘውዕቱ ሥጋሁ ለክርስቶስ ወደሙ ክቡር በእንተ ፍቅረ ዚአነ መጸአ ወአድኅነነ   ዳግመኛ ከዕፀ ኅይወት  እንበላ ዘንድ አደለን ይኸውም እኛን  ስለመውደድ ሰው ሆኖ ያዳነን የክርስቶስ ክቡር ሥጋው  ክቡር ደሙ ነው ‘’ በማለት እንደገለጸው፡፡  በወርኃ ጽጌ እመቤታችን ጌታን በጀርባዋ አዝላ በረኀ ለበረሃ ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር የተሰደደችበትን ሙሉ  ታሪክ  በጥልቀት ስንመለከት ፡፡

   ከላይ በርእሱ የተጠቀሰውን  ቃል  ( ልጄን ከግብፅ ጠራሁት    .ሆሴዕ  . 111  )  የሚለውን  የትንቢት ቃል የተናገረው ከክርሰቶስ ልደት በፊት በስምንተኛው ምእተ ዓመት አጋማሽ ገደማ የነበረው  የብኤሪ ልጅ ነቢዩ ሆሴዕ   ነው   ሆሴዕ  ማለት   እግዚአብሔር ያድናል ማለት ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ታሪኳ ከተዘረዘሩላት ሀገሮች መካከል ግብጽ አንዷ ስትሆን ግብጽ የብዙኀን አባት አብርሃም በረሃብ ምክንያት የተሰደደባት፣ ዮሴፍ በባርነት የተሸጠባት፣ ወገኖቹ እስራኤላውያን ለሁለት መቶ አስራ አምስት ዓመታት ያህል በባርነት የተገዙባት በኋላም የአለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ከድንግል ማርያም ጋር የተሰደደባት ሀገር ስትሆን መሪዎቿም አህዛብ አማልዕክቷም ጣኦታት ነበሩ፡፡ ነቢዩ ሆሴዕ የጌታችንን ሥደት ቀድሞ በትንቢት ከተናገሩት ውስጥ  አንዱ ሲሆን ልጄን ከግብፅ ጠራሁት በማለት የስደቱን ማብቃት ተናግሯል፡፡ በዚህ ትንቢት መሰረት መሰደዱን አልተነበየም፡፡ ነገር ግን ከስደት መመለሱን መናገሩ ካልተሰደደ መመለስ የለም በመመለሱ መሰደዱን ተናገረ፡፡

የጌታን ሕይወት ከእመቤታችን የእመቤታችንን ከጌታ ለያይቶ ማየት አይቻልም መለኮታዊ ተግባራትን እና የማዳን ስራዎችን  ካልሆነ በቀር ምክንያቱም ለእርሱ ብቻ የተወሰነና ሊያደርገው የተገባ የአባቱ ተልዕኮ ስለነበረ "ፈቃዴን ለማድረግ አይደለም አንጂ የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ከሰማይ ወርጃለሁ" (ዮሐ.638 ዮሐ.530) ነቢያት የተነበዩት ጊዜ ደርሶ በነቢዩ በሆሴዕ እንዳለውና መልአኩ ገብርኤል ለዮሴፍ ተገልጦ እንደነገረው አንድ ልጇን ይዛ ወደ ግብጹ ተሰደደች ( ማቴ.213 )

1.የእመቤታችንና የልጅዋ  ምክንያተ ስደት ወደ ምድረ ግብጽ

የእመቤታችን ስደት ብለን ስንናገር ከልጅዋ ጋር መሆኑን አንባቢ ሁሉ ልብ ሊለው የተገባ ሲሆን ስለ የእመቤታችን ስደት ምክንያት አበው ያስተማሩንን፣ መጽሐፍት የመዘገቡልንን በጥቂት እንዘረዝራለን፤ ትንቢተ ነቢያት እግዚአብሔር ሊያደርግ ያሰበውን ፈቃዱን ሁሉ ለሰው ልጅ እየገለጠ ነቢያትን ትንቢት እያናገረ መምህራንን እየላከ መጽሐፍትን እያጻፈ መሆኑን ልብ ማለት ተገቢ ነው፡፡ "እግዚአብሔር ይነግሮሙ ለሕዝቡ በመጽሐፍ" እግዚአብሔር ለህዝቡ በመጽሐፍ ይናገራቸዋል መባሉ "በቀንና በሌሊት ባሪያዎቼን ነቢያትን ሁሉ ልኬባቸው ነበር፣ አዎ ልኬባቸዋለሁ"  ( ኤር.725 ) በማለት ገልጧል፡፡ ከነዚህም ትንቢታት መካከል ስለ እመቤታችንና ጌታ ስደት ሲሆን፡-  ( ነቢዩ ኢሳይያስ . 191) "ናሁ እግዚአብሔር ይነብር ዲበ ደመና ቀሊል እነሆ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና እየበረረ ወደ ግብጽ ይመጣል ‘’፡፡  ትንቢተ ስምዖን፡- "ባንቺ ደግሞ ሰይፍ ያልፋል አላት" ( ሉቃ. 234 ) ስምዖን በንጉሡ በጥሊሞስ ጊዜ መጻህፍተ /ብሉያትን/ ከጥንቱ ዕብራይስጥ ወደ ግሪክኛ ለማስተርጎም ሰባ ሊቃናትን ባዘዘበት ወቅት ስምዖን የኢሳያስ መጽሐፍ ይደርሰዋል፡፡ "እነሆ ድንግል ትጸንሳለች ወንድ ልጅንም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች"፡፡ የሚለው ቃል ሲተረጎም ቢከብደው እንዴት ድንግል ትጸንሳለች ብዬ ልተርጉም ብሎ ሴት ትወልዳለች በማለት ቢጽፍ ተኝቶ ሲነሣ የጻፈው ጠፍቶ ድንግል ትጸንሳለች የሚል ተጽፎ ያገኛል፡፡ ይህ መሆኑ ቢገርመው መልአኩ መጥቶ ይህንን ሳታይ አትሞትም ብሎት ተሰወረ፡፡ በዚህም የትንቢቱን ፍጻሜ በቤተመቅደስ እጅግ አርጅቶ ሳለ ጠበቀ፡፡ ዮሴፍና እመቤታችን እንደ አይሁድ የመንጻት ሕግ በስምንተኛው ቀን ወደ ቤተመቅደስ ሲወስዳት ትንቢቱን ይጠብቅ የነበረው አረጋዊው ስምዖን የጌታን ማዳን አየ "እነሆ የብዙዎች ልብ አሳብ ይገለጥ ዘንድ ይህ በእስራኤል ላሉት ለብዙዎቹ ለመውደቃቸውና ለመነሳታቸው ለሚቃወሙትም ምልክት ተሾሞአል፡፡ በአንቺም ደግሞ በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል አላት"  ( ሉቃ. 234 ) በማለት ትንቢቱ መፈጸሙን ሲያይ ይህንን ካየሁ ባሪያህን በሰላም አሰናብተው ብሎ ሲለምን ገና ወደፊት የሚሆነውን የእመቤታችንን ስደት በልጇ አማካኝነት ወደፊት የሚደርስባትን መከራ ተነበየ፡፡ "ወለኪሰ ይበውእ ውስተ ነፍስኪ ኩናተ ኑፋቄ" ሰይፍ ያረፈበትን ለሁለት እንደሚከፈል ሁሉ የእመቤታችን ልብ ከሐዘን ምሬት የተነሣ እንደምትጎዳ የተነበየው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ከልጅዋ ጋር ተሰደደች ልብዋን  እንደ ሰይፍ የከፈሉት የእመቤታችን አምስቱ ሐዘናት የሚባሉት፤

አይሁድ እንዲገድሉት በቤተመቅደስ ስምዖን ትንቢት በተናገረ ጊዜ  ( ሉቃ.234 )

እጅና እግሩን አስረው በጲላጦስ አደባባይ በገረፉት ጊዜ  ( ዮሐ. 191 )

ጌታን ከኢየሩሳሌም ለበዓል ሔደው ሲመለሱ በመንገድ ባጣችው  ጊዜ  (ሉቃ. 241 )

በዕለተ ዓርብ ዕራቆቱን ተቸንክሮ በሁለት ወንበዴዎች መካከል በሰቀሉት ጊዜ ( ማቴ.2738 )

ወደ አዲስ መቃብር ውስጥ ባወረዱት ጊዜ ያዘነችው ሐዘን ( ማቴ.2759 )

አረጋዊው ስምዖን የተናገረው ትንቢት በእመቤታችን የሕይወት ዘመን ሁሉ በልጅዋ ምክንያት ሰይፍ የተባለ መከራ አልፎባታል በዚህም ሊቁ አባ ሕርያቆስ የእመቤታችነን ምልጃ ሲጠይቅ "አዘክሪ ድንግል አንብዐ መሪረ ዘውኀዘ እም አዕይንትከ ወወረደ ዲበ ገጸ ፍቁር ወልድኪ" ድንግል ሆይ በልጅሽ ፊት የወረደውን ከአይንሽ የፈሰሰውን ዕንባ አሳስቢ በማለት ለኛ ለኃጢአተኛ ልጆችዋ የምታማልደን ስለእንባዋ ይቅር እንደሚለን የተናገረው፡፡

.ስደተ ቅዱሳንን ለመባረክ  ወደ ምድረ ግብጽ ተሰደዱ

የክርስትና ህይወት የመስቀል ላይ ጉዞ በመሆኑ ክርስቶስን አምነው ለተከተሉት ሁሉ በመከራና በስደት እንደሚያልፍ ጌታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ከአለም ተመርጠው ለተከተሉት ደቀ መዛሙርቱ ሲያስተምር "እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ" በማለት ተናገረ ( ማቴ. 1624 ) በዚህም ቃል መሠረት ከቅዱሳን ሐዋርያት ጀምሮ የተነሡ ክርስቲያኖች በብዙ መከራ ውስጥ አለፉ በበረሃ ተሰደዱ፣ በዱር በገደሉ ተቅበዘበዙ በሰይፉ ተተረተሩ፣ በድንጋይ ተወገሩ፡፡ ዛሬም ቢሆን በእምነት የተሰደድን የተጨነቅን የምንጸልየው ስደትን ከኛ በፊት በሕጻንነቱ በቀመሰ ስደትን በሚያውቅ አምላክ ፊት ነው፡፡

. ጣኦታተ ግብጽን ለማጥፋትና ለመደምሰስ ወደ ምድረ ግብጽ ተሰደዱ

ግብጽ ከነገሥታቶቿ ጀምሮ ጣኦትን የሚያመልኩ አህዛብ የነበሩ ህዝቦች ነበሩ፡፡ እነዚህ ጣኦታት ደግሞ የበሬ፣ የላም፣  የአንበሳ፣ የወፍ ምስል አስቀርጸው ያመልኩ ስለነበር ለዚህም ከሙሴና ከአሮን ጸሎት የተነሳ የግብጻውያን የእጃቸው ሥራ መጥፋቱን፣ እግዚአብሔር በናቡከደነጾር አድሮ ወደ ግብጽ መምጣቱን፣ ጣዖታትን ማጥፋቱን የተነበየበት ከመሆኑ በላይ በዘባነ ማርያም ኅዙል /በማርያም ጀርባ ታዝሎ/ በፈጣን ደመና በተመሰለች ከእመቤታችን ጋር ወደ ግብጽ ተሰዳለች፡፡ ሊቃውንት እመቤታችንን ሲመስሏት ደመና ኢሳይያስ የሚሏትም ስለዚህ ነው፡፡ በዚህ ትንቢት ላይ እንደተገለጸው ግብጽ በጣዖታት የተሞላች በመሆኗ የጌታችን ስደት በግብጽ ያሉ ጣዖታትን ለማጥፋት እንዲሆን ተጠቅሷል፡፡ ግብጻውያን ከጥንት ጀምሮ በማስመሰል ደንጊያ ጠርበው እንጨት አለዝበው ማዕድን አቅልጠው  የእንስሳትን ምስል  የላም፣ የፍየል፣ የአንበሳ የወፍ  ምስልን በመቅረጽ ያመልኩ ስለነበር ከተማዋ በጣኦታት የተሞላች ነበር ፡፡ እነዚህን ለማጥፋት የጌታ ስደት ወደ ግብጽ ይሆን ዘንድ ትንቢት አናገረ፡፡ጌታችን ጣኦታትን ሊያፈርስ ወደ ግብጽ ተሰደደ ገና ከተማዋ ሲገባ በጣኦታቱ ላይ ያደሩ አጋንንት ይጮሁ ጣኦታቱም ይሰባበሩ ጀመር ከዚህም ባሻገር በኛ ሕይወትም ውስጥ ጌታን ለመቀበል ጌታ ስራ እንዲሰራብን በቅድስና ለመኖር የልብን ጣዖታት ማጥፋት ማጽዳት ይገባል፡፡ አልያ ጌታንና ጣዖትን በልባችን ማኖር አንችልም ቅዱስ ጳውሎስ "መኑ ደመሮ ለብርሃን ምስለ ጽልመት" ብርሃንም ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው? ክርስቶስ ከቤልሆር ጋር መስማማት አለው ወይስ የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ክፍል አለው ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ከጣዖት ጋር ምን መጋጠም አለው፡፡ እኛ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነንና፡፡ ያለው ለዚሁ ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት፡-  ( መዝ. 833 ) "ወፍ ለእርስዋ ቤትን አገኘች ዋኖስም ጫጭቶችዋን የምታኖርበት ቤት አገኘች"፡፡ በማለት ሲተነብይ ወፍ ለእርስዋ ቤትን አገኘች ሲል ነቢያት የተነበዩት ፍጻሜውን በእመቤታችን ማግኘቱን አንድም እመቤታችን በስደት ግብጽ መኖርያዋ ማድረጓን ዋኖስም ጫጭቶችዋን የምታኖርበት ሲል ዮሴፍና ሰሎሜም የሚኖሩበት ቤት ማግኘታቸውን ተናገረ፡፡ ለእመቤታችን ማደሪያ ጠፍቶ ማደሪያዋን ግብጽ ማድረጓን ተንብየዋል፡፡ነቢዩ ሆሴዕ፡- "እስራኤል ሕጻን በነበረ ጊዜ ወደድኩት ልጄንም ከግብጽ ጠራሁት"  ( ምዕ. 111 )   እስራኤል በግብጽ ሳሉ እንደተመረጡ ከዚያም አገር አውጥቶ መንግስት ይሆኑ ዘንድ እንዳበቃቸው የተናገረበት ትንቢት ከመሆን ጋር የጌታችን ወደ ግብጽ መሰደድ ሔሮድስ እስኪሞት በዚያ መቀመጡን ከዚያም መመለሱን የሚያመለክት መሆኑን ቅዱስ ማቴዎስ የነቢዩን ቃል ፍጻሜ አድርጎ ተናግሯል  ( ማቴ. 215 )

. ሰው መሆኑን ለመግለጽ  ወደ ምድረ ግብጽ  ተሰደደ

ኢየሱስ ክርስቶስ አገሩን ሳይለቅ ከሄድሮስ ዓይን መሠወር ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን በአምላካዊ ጥበቡ ከሄሮድስ ዓይን ተሰውሮ ቢሆን ሥጋ መልበሱ ሰው መሆኑን አይገለጽም ነበር፡፡ በሄሮድስ ዓይን የማይታይ ከሆነ ሥጋ ሳይለብስ የለበሰ መስሎ የተገለጸ ሥጋና አጥንት የሌለው /ምትሐት/ ነው በተባለም ነበር፡፡ ከአዳም አካል አንድም ያልጎደለው ሙሉ ዳግማዊ አዳም መሆኑን እና የለበሰው ሥጋ የሚደማ የሚቆስል በሰይፍም ሆነ በጦር ቢወጋ ጉዳት የሚደርስበት ሰብአዊ ባሕርይ ያለው መሆኑን ለማስረዳት ስደተኛ ሆነ፡፡ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ከጠላቱ ማምለጥ የሚችለው ከጠላቱ ፊት ዞር በማለቱ እና በመሸሹ ስለሆነ ጌታም ከጠላቱ ከሄሮድስ ለማምለጥ ሰው እንደመሆኑ ወደ ግብጽ ሸሸ፡፡

. ዲያብሎስን ለማሳደድ ወደ ምድረ ግብጽ  ተሰደደ

አዳም ዕፀ በለስን በልቶ ከፈጣሪው ጋር ተጣልቶ ከገነት ከወጣ በኋላ የእግዚአብሔርና የሰው ግንኙነት እየራቀ ሄደ፡፡ ይህን የፈጣሪና የፍጡር መራራቅ ያመጣው ዲያብሎስ ሲሆን በፈጣሪ መራቅ ፈንታ እርሱ መቅረብ ይፈልግ ነበር፡፡ ስለሆነም ፈጣሪው ከሰው ጓሮ ወደ ወጣበት የሰው ልጅ ሳይጠራ መምጣት ወይም መቅረብ ጀመረ፡፡ ዲያብሎስ የአዳምን ልጆች ተቆጣጠራቸው፡፡ ልባቸውን በፍቅረ ጣኦት ሸፍኖ አምልኮተ እግዚአብሔር እንዳያዩ አደረጋቸው ብዙ የአዳም ልጆችም የአግዚአብሔርን ፈቃድ ሳይሆን የሰይጣንን ፈቃድ ሲፈጽሙ ኖሩ፡፡ ጌታም "አሁን የዚህ ዓለም ገዥ ወደ ውጪ ይጣላል" (ዮሐ. 1231 ) በማለት ሰይጣን ዓለሙን ተቆጣጥሮት እንደነበረ ይገልጻል፡፡ እግዚአብሔር ወልድ የሰውን ሥጋ በለበሰ ጊዜ የፈጣሪና የፍጡር ግንኙነት እንደገና ተመሠረተ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ አገሩን ለቆ በመውጣቱ ዲያብሎስን ከተቆጣጠረው ከሰው ልቡና አስወጣው ጌታ ከሄሮድስ ፊት እየራቀ ሲሄድ ዲያብሎስም ከሰው ፊት እየራቀ ሄደ፡፡ የጌታ ስደት በተዘዋዋሪ የዲያብሎስ ስደት ሆነ ጌታ የሚቀበለው መከራ ሁሉ ዲያብሎስን በርቀት የሚመታ መሣርያ ነበር፡፡ በመጨረሻም በመስቀል ላይ የሆነው የጌታ ሞት የዲያብሎስ ሞት ሆነ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለመ ዓለም አሜን ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡አነሳስቶ ያስጀመረኝ አስጀምሮ ያስጨረሰኝ የቅዱሳን አባቶቻችን አምላክ ይክበር ይመስገን ፡፡አሜን  !!!!!!

 ይቀጥላል … … … … … … ይቆየን   ……………

መስከረም 20 /2005 /

Source: http://dhkidusraguel.org/ 

No comments:

Post a Comment