Thursday, November 1, 2012

ጾመ ጽጌ ክፍል 2

የማኅሌተ ጽጌና የጾመ ጽጌ አጀማመር
  የእመቤታችን የስደቷ መታሰቢያ ወር በቤተ ክርስቲያናችን የሚከበረው በማኅሌት፣ በቅዳሴና በዝክር ነው፡፡ በወርኃ ጽጌ ባሉት ሳምንታት ከቅዳሜ ማታ እስከ እሑድ ጠዋት አበው ካህናት የሚያቀርቡት ዝማሬ ከቅዱስ ያሬድ ድጓ፣ ከማኅሌት ጽጌና ከሰቆቃው ድንግል የተውጣጣና ሦስት ወገን ያለው ነው፡፡ ዝክሩም፣ በአሁኑ ወቅት በከተሞች አካባቢ እየተረሳ ቢመጣም፣ ዘወትር እሑድ የአንድ አካባቢ ሰዎች ማዕከላዊ በሆነ ቦታ ተሰባስበው በእመቤታችን ስም የሚዘክሩት ነው፡፡ ዐቅመ ደካሞች፣ ድሆችና መንገደኞች ተጠርተው በእመቤታችን ስም እንዲበሉና እንዲጠጡ ይደረጋል፡፡ ይህም ትውፊት እመቤታችን ወደ ኢትዮጵያ በመጣች ጊዜ ኢትዮጵያውያን  አባቶችና እናቶች ያደረጉላትን መስተንግዶ ለማሰብ ነው፡፡

ጾመ ጽጌ ክፍል 1

የጾም ትርጓሜ
የቤተ ክርስቲያናችን የሥርዓት መድብል የሆነው ፍትሐ ነገሥት ጾምን እንዲህ ይተረጉመዋል፡- ጾምሰ ተከልአተ ብእሲ እመብልዕ በጊዜ ዕውቅ በውስተ ሕግ - ጾምስ በታወቀው ዕለት፣ በታወቀው ሰዓት ሰው ከምግብ የሚከለከለው መከልከል ነው፡፡ አንድም ጾም ሰውን ከምግብ መከልከል ነው፡፡ ይህም ኃጢአቱን ለማስተሰረይ፣ ዋጋውን ለማብዛት እርሱ ወዶ ሕግን ለሠራለት እየታዘዘ የፈቲውን ኃይል ያደክም ዘንድ ሥራም ለነባቢት ነፍስ ትታዘዝ ዘንድ ነው፡፡ ፍት.ነገ.ፍት. መ. አንቀጽ 15564፡፡ በዚህ መሠረት ጾም ማለት ከጥሉላተ መባልዕት /ሥጋ ፣ ቅቤ፣ ወተት፣ እንቁላል እንዲሁም የአልኮል መጠጦች/ መታቀብ ነው፡፡

Monday, October 22, 2012

ዘመነ ጽጌ - ክፍል ሁለት

[ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 6]
"ልጄን ከግብፅ ጠራሁት"   (.ሆሴዕ 111 )
ከመምህር ዮሐንስ  ለማ

እመቤታችን በስደቷ የተጓዘችባቸው
ሐዋርያዊት የሆነች ቅድስት  ቤተ ክርስቲያናችን ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ ክርስቲያናዊ ትውፊታዋን ጠብቃ፣ መንፈሳዊ አገልግሎቷን በሚገባ አራቅቃ፣ ዘመንን በክፍል በክፍል ቀምራ፤ ከመስከረም ጀምሮ እስከ ጳጉሜን ድረስ ያሉት ሰንበታት የራሳቸው የሆነ ከምሥጢረ ድህነት ጋር የተያያዘ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ስያሜ ሰጥታ የሰው ልጆችን ከመርገመ ሥጋ ከመርገመ ነፍስ ለማዳን የተደረገው (የተፈጸመው) አምላካዊ የድኅነት ጉዞ እያዘከረች፣ እያስተማረች... ለዘመናት ቆይታለች፣ አሁንም በማስተማር ላይ ናት ለወደፊትም እግዚአብሔር እስከ ፈቀደላት ጊዜ ድረስ ስትመሰክርና ስታስተምር ትኖራለች፡፡  እመቤታችን በትልቅ የምስጋና አገልግሎት ከሚከበሩላት በዓላት መካከል የወርሐ ጽጌ (ዘመነ ጽጌ ) አንዱና በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ልብ ውስጥ ጥልቅ የልቡና ፍቅር ያለው  ይሕ የወርሐ ጽጌ ወቅት  አንዱ ነው ፡፡ በመሆኑም በክፍል አንድ ጽሐፍ   የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ስደት በማስመልከት ምክንያተ ስደቷንና ተያያዥ ርዕሶችን ማስነበባችን  ይታወሳል፡፡ አሁን ደግሞ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም  በስደቷ ወቅት  ያሳለፈቻቸውን  ውጣ ውረድና ተያያዥ ክስተቶችን  እንዲሁም የጉዞዋን ዋና ዋና መዳረሻዎችን ጭምር ለማስነበብ እንሞክራለን፡፡


ዘመነ ጽጌ - ክፍል አንድ

[ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 6]

"ልጄን ከግብፅ ጠራሁት"   (.ሆሴዕ 111 )

ከመምህር ዮሐንስ  ለማ

እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ  ቤተክርስቲያን  ሕግና ስርአት መሰረት ከመስከረም 26 ቀን  እስከ ሕዳር 6 ቀን  ያለው 40 ቀን  የእመቤታችንን እና የልጇን ስደት በማሰብ ወርኃ ጽጌን (ዘመነ ጽጌን) ታከብራለች፡፡ ይህ 40 ቀን የእመቤታችንና የጌታችን ስደት የሚታሰብበት ዘመን ነው፡፡ ወቅቱ የአበባና የፍሬ ወቅት በመሆኑ እመቤታችን በአበባ ጌታችን በፍሬ እየተመሰሉ ጌታችን በአምልኮት እመቤታችን በፈጣሪ እናትነቷ በተለየ ምስጋና ይመሰገናሉ ፡፡

 በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሳው ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ አምሥቱን ጸዋትወ ዜማ ሲደርስ 14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሳው አባ ጊዮርጊስ ደግሞ ሰዓታትን ደርሷል፡፡ በዚሁ ዘመን ከአባ ጊዮርጊስ ጋር ጥልቅ መንፈሳዊ ፍቅር የነበረው አባ ጽጌ ድንግል  ማኅሌተ ጽጌ  የተባለውን ድርሰት ደርሷል፡፡  ማኅሌተ ጽጌ ግጥማዊ አካሄድ ያለው ድንቅ ኢትዮጵያዊ ድርሰት ሲሆን  ይህ ድርሰት በማንኛውም ጊዜ የሚጸለይ ቢሆንም በተለየ ሁኔታ ወቅት ተለይቶለት በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ላይ የሚውለው ግን   በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና በልጇ የስደት ዘመን  ማለትም  ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 5 ቀን ድረስ ባለው  ዘመን ውስጥ ነው፡፡ በዚህ ወቅት በየሳምንቱ እሑድ ሌሊቱን በሙሉ የእመቤታችንን ከልጇ ጋር ወደ  ምድረ ግብፅ መሰደድና መንከራተት እየታሰበ በሊቃውንቱ  የሚደርስ የምሥጋና ጸሎትም  ነው ፡፡ ይህ ድርሰት በግጥም መልክ የተደረሰ  ሲሆን በአብዛኛው አምስት ስንኞች ሲኖሩት ብዛቱም 158 ያክል ነው፡፡ እመቤታችን ጣዕሟንና ፍቅሯን እንዲሁም ምስጋናዋን ሲናፍቁ የነበሩትን ቅዱስ ኤፍሬምንና አባ ሕርያቆስን ውዳሴዋንና ቅዳሴዋን እንደገለጸችላቸው  ሁሉ ለፍቅሯ ሲሳሳ ለነበረው ለአባ ጽጌ ድንግል ደግሞ ይህንን የማኅሌተ ጽጌን ድርሰት  እንዲደርስ ምስጢርን ገልጻለታልች

ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብጽ ሽሽ


   በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
የዚህ ትምህርት መሠረታዊ ዓላማ ክርስቲያኖች ከጌታችንና ከእመቤታችን ስደት በረከት ተሳታፊዎች እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡
  ቀዳማዊ አዳም የማይበላ በልቶ በራሱና በልጆቹ የሞት ሞት ተፈረደበት፤ ጸጋ እግዚአብሔር ጎደለበት፤ የሚሠዋው መሥዋዕት የሚጸልየው ጸሎት ግዳጅ የማይፈጽም ሆነበት፡፡ ምድር ከእርሱ የተነሣ እሾክና አሜከላ አበቀለችበት፡፡

  ሆኖም (አዳም) ምንም ባልበደለው ሰይጣን እንዲሁ ቢሞትም የተበደለው አምላኩ ግን እንዲሁ ሕይወትን ይሰጠው ዘንድ ወደደ፡፡ (አዳም) አምላክ መሆንን ሽቶ ነበርና ይህን ይሰጠው ዘንድ (አምላክ) ዳግማይ አዳም ይሆንለት ዘንድ ወደደ፤ አስቀድሞ ከነበረው ክብር በላይ ሌላ ክብር ይጨምርለት ዘንድ ፈቀደ፡፡ ጊዜው ሲደርስም አካላዊ ቃል ንጹሕ የሆነ ባሕርዩን (የእመቤታችን ሥጋና ነፍስ) ነሥቶ ዝቅ ያለውን ከፍ ያደርገው ዘንድ ዝቅ አለለት፤ የጸጋ ልብሱን ይመልስለት ዘንድ የማይዳሰስ እርሱ በጨርቅ ተጠቀለለት፤ ወደ ክብሩ ይመልሰው ዘንድ በርካሽ ቦታ ያውም በግርግም ተወለደለት፡፡ 

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
 ባለፈው ዝግጅታችን ስለቅዱሳን ሐዋርያት አጠቃላይ መግቢያ አቅርበን በቀጣይነትደግሞ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የእያንዳንዱን ሐዋርያ የተጋድሎ ሕይወት በዝርዝርእንደምናቀርብ ቃል ገብተን ነበር (የባለፈውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ-http://mekrez.blogspot.com/2012/09/blog-post_12.html) በመሆኑም ለዛሬየሐዋርያት አለቃ የሆነውን የሐዋርያው የቅዱስ ጴጥሮስን ሕይወትና ተጋድሎ እነሆብለናል መልካም ንባብ።

 ቅዱስ ጴጥሮስ የተወለደው በገሊላ ባሕር ዳርቻ ( የገሊላ ባሕር ስያሜዎችአሉት፡- () የገሊላ ባሕር (በገሊላ አውራጃ ስለሚገኝ) በዙሪያው ባሉ ጌንሴሬጥናጥብርያዶስ በሚባሉ ከተሞች ስም ደግሞ () ባሕረ ጌንሴሬጥ እና () ባሕረጥብርያዶስ ይባላል) ባለች ቤተሳይዳ በተባለች ከተማ ውስጥ ነው የአባቱ ስም ዮናሲሆን ትውልዱም ከነገደ ሮቤል ነው። እናቱ ደግሞ ከነገደ ስምዖን ወገን የሆነችነበረች።  በመሆኑም እንደ ኦሪት ሥርዐት ስም ሲያወጡለት በእናቱ ነገድ ስምስምዖን ብለውታል። አባቱ ዮና የያዕቆብና የዮሐንስ አባት ከሆነው ከዘብዴዎስ ጋርየሥራ ባልንጀራ ሲሆን የሁለቱም  ሥራቸው ዓሣ እያጠመዱ መሸጥ ነበር። እድሜው፭ ዓመት ሲሆን ኦሪትን እየተማረ እንዲያድግ በአቅራቢያቸው ወዳለ ወደቅፍርናሆም ምኩራብ ሰደዱት። ቅዱስ ጴጥሮስ በቅፍርናሆም እየተማረ ካደገ በኋላበዚያው ቤት ሠርቶ ኮንኮርድያ (ጴርጴቱዋየምትባል ሚስት አግብቶ እንደ አባቱዓሣ እያጠመደ በመሸጥ መኖር ጀመረ። 

Monday, September 10, 2012

ዘመነ ማቴዎስ ወንጌላዊ እና ቅዱስ ድሜጥሮስ ተካሌ ወይን



እንኳን ለዘመነ ማቴዎስ 2005 .. በሰላም አደረሳችሁ 
ዕንቁጣጣሽ
አዲሱ ዓመት የንስሐ የቅድስና የደስታ የፍስሐ የፍቅር ያድርግልን

ሐዋርያው ቅዱስ ማቴዎስ
ማቴዎስ ወንጌላዊ 
ድሜጥሮስ መስታወት ነው፡-በመስታወት ከዓይን ጉድፍ ከጥርስ እድፍ አይተው እንደሚያጸዱበት ሁሉ ባሕረ ሐሳብንም የተማረ ሰው ዓለም ከተፈጠረ ጊዜ ጀምሮ እስከ ምጽአት ድረስ የሚሆነውን ቁጥር ያውቃልና፡፡ ባሕረ ሐሳብ ማለት ቁጥር ያለው ዘመን ማለት ነው፡፡ አንድም ሐሳብ ባሕር ይለዋል ዘመን ያለው ቁጥር ሲል ነው፡፡

ድሜጥሮስ መነጽር ነው፡- መነጽር የራቀውን አቅርቦ፣ የረቀቀውን አጉልቶ፣ የተበተነውን ሰብስቦ እንዲያሳይ እርሱም የተበተኑ አጽዋማትን በዓላትን አቅርቦ ያሳያልና፡፡
ድሜጥሮስ ጎዳና ነው፡- በጎዳናው ተጉዘው ከቤት እንደሚደርሱ ሁሉ፣ ባሕረ ሓሳብም ወደ ኋላ ያለፉትን ወደፊትም የሚመጡትን አጽዋማት በዓላትን ለይቶ ያሳውቃልና፡፡

 ድሜጥሮስ ተራራ ነው፡- በተራራው ጫፍ ላይ በወጡ ጊዜ ምንጩ ሜዳው፣ ግጫው፣ ኮረብታው እንደሚታይ ሁሉ ድሜጥሮስም የአጽዋማት በዓላትን ኢየዓርግ ኢይወርድ ጠንቅቶ ጽፏልና፡፡
ድሜጥሮስ መስተገብረ ምድር (በግብርና የሚተዳደር) ነው፡-
ይህስ ጥንተ ነገሩ እንደምን ነው ቢሉ፡-

Tuesday, August 21, 2012

††† የማኅበረ በዓለ ወልድ መልዕክት †††


                                             
በጎርፍ ምክንያት የሚሸረሸር መሬት፦ ዝም ካልነው መሬቱ ተሸርሽሮ፦ የመሬቱ ገጽታ ተቀይሮ ፤ ከጥቅም ውጪ ሆኖ ይቀይራል። የመሬቱን መሸርሸር ለማቆም ግድብ መሥራት የግ ይላል። እኛ አሁን መነጋገርና መሥራት ያለብንም መገደብ ያልቻልነው ለምንድን ነው? የት እና እንዴት ነው የምንገድበው? በሚሉት ጉዳዮች ላይ ነው። ከዚያም በኋላ በሌሎች ቦታዎች ላይ ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር በዕቅድ መሥራት እንችላለን። የአጭርና ረዥም ጊዜ ዕቅድ ንድፍ ይዘን የምንጓዝ ከሆነ እንደየአካባቢውና እንደየሁኔታው ለሚፈጠሩ ችግሮች መሠረታዊና ለቦታው የሚስማማ የአሠራር ዘዴዎችን መዘርጋት ቀላል ይሆናል።
እንግዲህ በዚህ ዘመን ያለነው ክርስቲያኖች ከዚህ የምንማረው ምንድን ነው? ከእኛስ የሚጠበቀው እስከምን ድረስ ነው? እስከሞት ድረስ መታመን እንችላለን ወይ? ቤተክርስቲያን እየደረሰባት ያለው ፈተና  እንዴት ሊበዛ ቻለ? መፍትሔውስ ምንድን ነው? በኢትዮጵያ፦ በሰሜን አሜሪካ እና በሌሎች ክፍላተ ዓለማት ብዙ ማኅበራት አሉ፦ በኅብረት መሥራት አይቻልም ወይ? ቤተክርስቲያንን በየጊዜው እየከበባት ያለውን የጥፋት ዘመቻ መግታት የሚቻለው እንዴት ነው? ከሃይማኖታችን ኃላፊነት ግዴታ አንጻር ብዙ ያልሠራነው እኛ ወይስ የሃይማኖት መሪዎች? ዛሬ በየገዳማቱ ላይ በተደጋጋሚ እየደረሱ ላሉት ጥቃቶች ተጠያቂው ማን ነው? መፍትሔዎቻቸውስ? ቤተክርስቲያንን አብዝቶ እየጎዳት ያለው የውስት ወይስ ከውጪ የሚመጣ ፈተና? የቤተክርስቲያን ጠላቶች ዓላማ ግልፅና  የታወቀ ሲሆን መግታት ያልቻልንበት በምን ምክንያት ነው? በሰከነ  ልብ፦ በበሰለ አዕምሮ ፦ በለዘበ አንደበት፦ የቤተክርስቲያንን ጥቅም ባማከለ ሁኔታ እስኪ እንነጋገር፦ እንመካከር፦ እንጸልይ። በነገር ሁሉ እግዚአብሔር ማስተዋሉን ይስጠን! አሜን! ፪ ጢሞ ፪፡፯

Sunday, July 29, 2012

“እስከ ሞት ድረስ የታመንህ ሁን “ ራዕየ ዮሐንስ ምእራፍ ፪ ፥ ፲


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡ አሜን! 

“ካለውና ከነበረው ከሚመጣውም በዙፋኑም ፊት ካሉት ከሰባቱ መናፍስት ከታመነውም ምስክር ከሙታንም በኩር የምድርም ነገሥታት ገዥ ከሆነ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን አሜን!””

“እስከ ሞት ድረስ የታመንህ ሁን “ ራዕየ ዮሐንስ ምእራፍ  ፪ ፥ ፲

በዘላለማዊ የኪዳን ደም ሊታደገንና ለነፍሳችን ፍጹም እረፍትን ሊሰጠን፡ ወደ ክብሩ ዙፋን ሊያደርሰንና ወደ ቅዱሳን ሕብረት ሊደምረን በቀራንዮ ለቤዛነታችን መስዋዕት የሆነው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ሞት ድረስ ለታመነው ሐዋርያ በፍጥሞ  ደሴት በግዞት ሳለ ወደፊት በቤተክርቲያን ላይ ሊደርስ ስላለው መከራ፦ ስደትና ፈተና  እንዲሁም ለቤተክርስቲያን መሪዎችና ለማህበረ ምእመናን ፦ ከእነርሱ ስለሚጠበቀው ኃላፊነትና ክርስቲያናዊ ግዴታ ምን እንደሆነ በአጽንኦት የሚያመላክት፤ አማናዊ ቃሉን ለሚጠብቁ እና እንደ ፈቃዱም ጸንተው ለሚኖሩት ያዘጋጀላቸው ፍጹም የሆነ ሰማያዊ ክብር እና ጸጋ በማስረገጥ በራዕይ የገለጠለት ምስጢራዊ የትንቢት ቃል ነው።

በራዕየ ዮሐንስ ምዕራፍ ሁለት እና ሦስት የተጻፉት ትንቢታዊ መልዕክቶች በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን በእስያ (በዛሬዋ የቱርክ ክፍለ ግዛት) አካባቢ በቅዱሳን ሐዋርያት ትምህርት የተመሰረቱ እና ታላቅ መንፈሳዊ አገልግሎት ይሰጥባቸው የነበሩ ሰባት አብያተ ክርስቲያናት ፦ የአገልግሎት ጥንካሬ እና ድክመት ምን እንደሆኑ በዝርዝር ከማስረዳታቸውም ባሻገር የእነዚያ አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች እና  ምእመናን በተለያዩ ምክንያቶች በወቅቱ ከደረሱባቸው ወደ ፊትም ሊመጡባቸው ከሚችሉ ፈተናዎች እና መከራዎች እንዴት ማምለጥ እንደሚችሉ ከእግዚአብሔር የተላከላቸውን መልዕክት ሰምተው፦ በእምነትም ጸንተው፦ በመንፈሳዊ ተጋድሎ በርትተው በእግዚአንሔር ኃይል እና መንፈስ በመታገዝ በአሸናፊነት መጓዝ የሚችሉባቸውን መንገዶች የሚያሳዩ መልዕክቶች ናቸው። ለዚህም ነው በእያንዳንዷ መልዕክት መዝጊያ ላይ “ መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን  ጆሮ ያለው ይስማ።” በማለት ያሳሰበው።

ከሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከልም ከወቀሳው ቃል የዳኑት ሰምርኔስ እና ፊላዴልፊያ  ሲሆኑ የአምስቱ አብያተ ክርስቲያናት አለቆች እና  ምዕመናን ወቀሳ እና ተግሳጽ ደርሶባቸዋል። “እስከሞት ድረስ የታመንህ ሁን.....” የሚለው ቃል በወቅቱ የተነገረውም በሰምርኔስ ቤተ ክርስቲያን ተሹሞ ለነበረው ለቅዱስ ሄሬኔዎስ ነው። በእርሱ እና በምእመናን ላይ እስራት እና  ጽኑ የሆነ መከራ እንደሚደርስባቸው እያሳሰበ በዚህ ሁሉ ግን ሊደርስባቸው በሚችለው ነገር ሳይሳቀቁ ፍርሃትን በእምነት አስወግደው እስከ ሞት ድረስ እግዚአብሔርን በመታመን እንዲጸኑ፦ ይህንን ቢያደርጉ የሕይወትን አክሊል እንደሚቀዳጁ በማስረገጥ ነው መልዕክቱን ያጠቃለለው።

Monday, July 16, 2012

ቤተክርስቲያን እንዴት ተመሠረተች ? ክፍል ፩


 ስለ ክርስትና ሃይማኖት ስለ ቤተክርስቲያን በምንናገርበት ጊዜ ሁሉ ትዝ የሚለንና የምናስተውለው የመጀመሪያው ሰው የአዳም ሁኔታ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን እግዚአብሔር ሁላችንን አባት አዳምን በአርአያውና በመልኩ ከፈጠረው በኋላ ባረከው፡፡ ኹሉንም እንዲገዛ ሥልጣን ሰጠው፡፡ በረከቱን ሥልጣኑንና ሲሳዩን ከሰጠው በኋላ ፈጣሪውን የሚያስታውስበት ትእዛዝ አዘዘው፡፡ እሱ ግን በተሳሳተ ምክር ተመርቶ ከፈጣሪው ትእዛዝ ወጣ፡፡ በዚህ ጊዜ የሞት ፍርድ ተፈረደበት፡፡ ይህም የሞት ቅጣት ለርሱ ዐቅም ቀላል አልነበረም፡፡ በሱም ብቻ አልቀረም የልጅ ልጆቹ ይህን የሞት ቅጣት በውርስ ተካፈሉት፡፡ የዚህ የሞት ጽዋ ተካፋዮች ሆኑ፡፡ የአዳም ሕግን መተላለፍ የልጆቹም ተባባሪነት በእግዚአብሔርና በነሱ መካከል ያለውን ልዩነት እያሰፋው ሔደ፡፡ የፈጠራቸው እግዚአብሔርን ዘንግተው የሰማይና የምድርን ሠራዊት ማምለክ ጀመሩ፡፡ በጨረቃ፣ በፀሐይና በከዋክብት፣ በእሳት፣ በውኃ፣ በእንስሳትና በአራዊት፣ በዛፍና በተራራ፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር የሰውን ዘር ጨርሶ ለመደምሰስ ስላልፈለገ ይህን የሰው ልጅ መራራና አሰቃቂ ታሪክ ከመጀመሪያው ጀምረው ሲከታተሉ የነበሩ በአንድ አምላክ በማመን የታወቁ ጥቂት ሰዎችን አተረፈ፡፡ እነሱም ከአበው ሄኖክን፣ ኖህን፣ አብርሃምንና ሎጥን ሌሎችንም የመሳሰሉትን ነው፡፡