Wednesday, December 14, 2011

“አንተም ተው አንተም ተው” - አርዮስንና ቅዱስ ቄርሎስን?!

በስመ አብ ፡ ወወልድ ፡ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን፡፡
ፍቅርን አውቃለሁ በተግባርም እገልፃለሁ የሚል - - - ነገር ግን ፍቅሩ የይምሰል የዲያቢሎስ ያልሆነበት የመንፈስ ቅዱስን ፍቅር የተገነዘበ በማስተዋልም የከበረ በተዋህዶ እምነቱ የሚኮራ በእውነት ፊት ፡ በፍቅር ሽንጎ ፡ በማስተዋልም ጥበብ ዳኛ ይሁንና ይህንን ይዳኝ ፦ በሽንጎው ላይ  ቅዱስ ቄርሎስና አርዮስ ቆመዋል፡፡ ስለጥንተ ነገራቸው፦

1)     አርዮስ የክርስቶስን አምላክነት የሚጠራጠር በተዋህዶ የምታምን ቤተክርስቲያንንም በአዲስ ትምህርት ለመለወጥ የሚተጋ ሲሆን ከአንድም ብዙ ጊዜ ትምህርቱ ስህተት እንደሆነ ሊቃውንቱ በመፅሃፍ ቅዱስ አስረጅነት በመንፈስ ቅዱስ ምስክርነት ቢያስረዱትና ቢመክሩት እምቢ ያለ ፡ ክርስቶስን ከአብ አንድነት የለየ ሲሆን ፡ ቤተክርስቲያን በዚህ እምነቱ ከአንዴም ሁለት ሶስት ጊዜ ብትለየውም አርዮስ ግን በገንዘብ የሚታለሉትን ካህናት ፡ ባለማስተዋል የሚሄዱትን ምእመናንና አለማዊ ነገስታትን በትምህርቱና በወቅቱ በነበረው የግጥም ፡ የዜማና የስነፅሁፍ እውቀት ደጋፊ አድርጎ ከአንድም ሁለት ሶስት ጊዜ ተፅፅቻለሁ እያለ ወደ መቅደስ ይገባ የነበረ ነው፡፡ ይቅርታንም ካገኝ በኅላ ምንፍቅናውንና በልቡ ያደረ ሰይጣንን ከራሱ ሊያስወግድ አልፈቀደምና መልሶ መላልሶ ወደቀደመ ክህደቱ የሚመላለስ ነው፡፡ ትምህርቱ ይህ ሲሆን ህይወቱ ደግሞ በቀደመው እድሜው የቤተክርስቲያን ዲያቆን በነበረበት የወጣትነት ጊዜ በዘመኑ የነበሩ የአህዛብ ነገስታት ቤተክርስቲያናት ወደ ጣኦትነት እንዲቀየሩ የቤተክርስቲያን ካህናትም የጣኦት ካህናት እንዲሆኑ ሲታዘዝ እውነተኞቹ ካህናት ገሚሱ ሰማእት ሲሆን ገሚሱ ሲሰደድ አንዳንዶች ግን የክርስቶስን ቤተመቅደስ እጣን ባጠኑበት እጃቸው ቅዱስ ወንጌሉን ባስተማሩበት አፋቸው ሰማእትነት ርቋቸው ፡ መፅናት አቅቷቸው ፡ የመንፈስ ፍሬ ታጥቶባቸው  ነበርና የጣኦት አገልጋይ ለመሆን አላፈሩም፡፡ ከነዚህ ውስጥ አንዱ አርዮስ ነበር፡፡