Tuesday, January 22, 2013

የመገለጥ ሃይማኖት በአስተርእዮ


በዲያቆን ብርሃኑ አድማስ
የጥምቀት በዓል አከባበር በጎንደር ከተማ
ሃይማኖት የምንቀበለውና የምንጠብቀው እንጂ የምንሠራውና የምናሻሽለው አይደለም ከታኅሣሥ 29 ቀን ጀምሮ እስከ ዐቢይ ጾም መግቢያ ድረስ ያለው ወቅት /ጊዜ/ ዘመነ አስተርእዮ /የመገለጥ ወራት/ እየተባለ ይጠራል፡፡ በታኅሣሥ 29 ቀን የጌታችን ልደት ስለሆነ በዚህ አምላክ በሥጋ የተገለጠበት በዓል ይከበራል፡፡ ጥር 11 ቀን ደግሞ በጌታችን ጥምቀት የሥላሴ አንድነት ሦስትነት በይፋ የተገለጠበት ነው፡፡ ጥር 12 ቀን ደግሞ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምድር ማስተማር በጀመረበት ጊዜ በቃና ዘገሊላ ሰርግ ቤት ተገኝቶ ውኃውን ወደ ወይን በመለወጥ አምላክነቱን በይፋ የገለጠበት በዓል ነው፡፡ እነዚህ ሦስት ዓበይት መገለጦች ወቅቱን በአጠቃላይ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ የተገለጠበትን መታሰቢያ አደረጉት፡፡ አምልኮተ እግዚአብሔርን ትክክለኛ ሃይማኖት ከሚያሰኙት መሠረታዊ ነጥቦች ዋነኛውና ቀዳሚው የመገለጥ ሃይማኖት /Revealed Religion/ መሆኑ ነው፡፡