Tuesday, November 15, 2011

ርትዕት ይእቲ ሃይማኖቶሙ ለቅዱሳን አበዊነ

«ርትዕት ይእቲ ሃይማኖቶሙ ለቅዱሳን አበዊነ ( የአባቶቻችን ሃይማኖት የቀናች ናት)»፡፡
ከማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ የተገኘ
አትም ኢሜይል

የንግግርና ሥነ ጽሕፈት ሙያን የተካኑ ምሁራን በትምህርት ጌጣቸው እንደሚሉት «ውሃን ከጥሩው ሲቀዱት፣ ነገርን ከሥሩ ሲያመጡት» ውሃው ጠጭውን፣ ነገሩም ሰሚውን ያረካዋል፡፡ በዚህ እውነተኛ ሃይማኖትን ከጊዜው ስመ መሳይ ኑፋቄና የለየለት ክሕደት ለይቶ በሚያሳይ ትምህርታችን «አበዊነ = አባቶቻችን» ያልናቸው እነማን እንደሆኑ በጥቅል ማመልከት እንወዳለን፡፡ የቃሉን ዐይነ ምስጢር ቁልጭ አድርጎ ለመግለጽ ያህል አባትነት መልክና ይዘቱ፣ ግብርና ዐይነቱ በጣሙን ብዙ ነው፡፡ ይሁንና እዚህ ላይ «የቀናች፣ የጸናች ሃይማኖት» ባለቤቶች ብለን በትምህርታችን ርእስ በመሪነት ያነሣናቸው፡፡
- ከአዳም ጀምሮ እስከ ኖኅ በደብር ቅዱስ የነበሩ አርእስተ አበውን፣
- ከአብርሃም ጀምሮ እስከ ሊቀ ነቢያት ሙሴ የነበሩትን የእግዚአብሔር ሰዎች፣
- አዕይንተ አርጋብ ዐበይት ደቂቅ ነቢያትን፣


ይልቁንም «አንተ ውእቱ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር ሕያው = አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነህ» ከማለታቸው አስከትለው «እግዚኦ ኀበ መኑ ነሐውር እንዘ ቃለ ሕይወት ዘለዓለም ብከ፣ ወንሕነሰ አመነ፣ ወአእመርነ፣ ከመ አንተ ውእቱ ክርስቶስ ወልዱ ለእግዚአብሔር ሕያው =አቤቱ! የዘለዓለም ደኅንነት የሚገኝበት ትምህርት ከአንተ ዘንድ እያለ ወደማን እንሔዳለን?እኛስ የሕያው እግዚአብሔር ልጁ ክርስቶስ እንደሆንህ ዐውቀን አምነናል» ማቴ.16-16፣ ዮሐ. 6-68-70 ብለው መስክረው ሲያበቁ ሃይማኖትን አብርተው ያረጋገጡ፣ ሁለንተናቸው በደመ እግዚእነ ኢየሱስ ክርሰቶስ ተኮልቶ የበራ፣ የጠራ ጽሩያነ አዕንይት የትምህርት፣ የሃይማኖት፣ የክህነት አባቶቻችን የሆኑ፣ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው የተሟሟቁ ቅዱሳን ሐዋርያትን ነው፡፡

ደግሞም የእነርሱን ዓላማና ግብር የተከተሉ ሰብአ አርድዕትና ምሉአነ አእምሮ ሠለስቱ ምእት ሊቃውንትን፣ ተጋዳልያን ሰማዕታትና ጻድቃን፣ ቅዱሳን ማለታችን ነው፣ እንጂ የመጀመሪያው የወንድሙ ነፍሰ ገዳይ የቃኤል ልጆችን ሁሉ አደባልቀን፣ ነገርን ከነገር አጣልፈን፤ ምስጢሩንም ደብቀን፣ ከሐድያን፣ ጣዖት አምላኪዎች መስሕታንን ቀደምት አበው ከሆኑ ብለን ሳናስተውል በጅምላው አይደልም፡፡ ስለይህ የእነዚህን ቅዱሳን = የተለዩ አበው የቀናች፣ የጸናች ሃይማኖት የሆነችው «ርትዕት ይእቲ ሃይማኖቶሙ ለቅዱሳን አበዊነ = የአባቶቻችን ሃይማኖት የቀናች የጸናች ናት፡፡» በዚች መሠረትነት ለሁለት ሺኽ ዘመናት እምነቷ፣ ሥርዐቷ፣ ባህሏ ተጠብቆ ለሕዝበ ክርስቲያን የሚገባውን መንፈሳዊና ሐዋርያዊ፣ ማኅበራዊም አገልግሎት ስታቀርብ የኖረች ጥንታዊት፣ ሐዋርያዊትና ብሔራዊት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየዘመናቱ የገጠሙአትን ችግሮች፣ ፈተናዎች በታላቅ ትዕግሥት፣ በጾምና በጸሎት፤ በመንፈሳዊ ጥበብ የማለፍ ልምድና ዕውቀቷ በዓለም የተመሰከረ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በአለንበት ጊዜ እምነቷን፣ ሕጓንና ሥርዐቷን ለማፋለስ በግልና በቡድን የተነሣሡ የእምነት ተቀናቃኞች በየአቅጣጫው በመዝመት ላይ መሆናቸው ለሕዝበ ክርስቲያን ግልጽ እየሆነ መጥቷል፤ አሁንም የበለጠ ሊታወቅ ይገባል፡፡

የመናፍቃንና የሃይማኖት ለዋጮች እንቅስቃሴ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያልተለመደና እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ ቀድሞ የነበረ፣ ያለና ወደፊትም የሚኖር ነው፡፡ ምክንያቱም አዝማቹ ጠላት በሞተ ሥጋ የማያርፍ ዲያብሎስ እንደሆነ በብሩህ ልቡና ይታወቃል፡፡ በመልካም እርሻ /ማሳ/ የተዘራው ንጹሕ ስንዴና ጠላት ጨለማ ለብሶ በስንዴው ማሳ ላይ የበተነው እንክርዳድ እስከ መኸር ጊዜ ዐብረው እንደሚኖሩ ጌታችን ራሱ ባለቤቱ በቅዱስ ወንጌል አስተምሮናል ማቴ. 13-24 - 31 ይህ የማይሻር ቃል ስለሆነ ሌላ ምን ይባላል? ዐይነ ኅሊናችንን ወደ ቀደመው ታሪክ ስናቀና በአበው ሐዋርያት ዘመንም በመልካም እርሻ ላይ በብርሃን የተዘራውን ጥሩ ዘር፣ ለማበላሸት የጥፋት ዘር በጨለማ የሚበትኑ ቢጽ ሐሳውያንና መናፍቃን ቤተ ክርስቲያንን ሲያውኩና ሲያምሱ ኖረዋል፡፡

በቀና ሃይማኖት ስምና ጥላ ተሸፍነው ትክክለኛውን እምነትና መሠረት ለማፋለስ ከማሴርም ዐልፈው ራሳቸውን በአማልክት ደረጃ በማስቀመጥ ሰዎችን ወደ ጥፋት በሚያደርስ መንገድ ለመምራት የቃጣቸው ብዙዎች ነበሩ፡፡ ዳሩ ግን ሁሉም እንደገለባ እሳት ብልጭ እያሉ ጠፍተዋል፡፡ በዓለም ላይ የበተኑት የጥፋት ዘር ግን ክሕደት የሚያብብበት ካፊያ ባካፋ ቁጥር በምንጭ ላይ እንደወደቀ ዘር በፍጥነት ይበቅላል፡፡ የእውነት ፀሐይ ስትወጣ ደግሞ መልሶ ይጠወልጋል፡፡ እንደነ ይሁዳ ዘገሊላ፣ እንደነ ቴዎዳስ ዘግብጽ የመሳሰሉት ከብዙዎች በምሳሌነት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ «ቴዎዳስ ዘግብጽ» አምላክ ነኝ ብሎ ተነሥቶ እሰከ አራት መቶ የሚደርሱ ተከታዮች አፍርቶ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ብዙ አልተጓዙም እርሱም፣ ተከታዮችም ፀሐየ ጽድቅ ሲወጣ እንደሚጠወልገው ሣር ፈጥነው ጠፍተዋል፡፡ ይሁዳ ዘገሊላም እንደዚሁ ነው፡፡ አልቆየም፤ ጠፍቷል፡፡ /ግ.ሐ. 5-37/

ጥንታዊት ሐዋርያዊት ብሔራዊት ቤተ ክርስቲያናችንን ለመበታተን የሚጥሩት ሁሉ መሠረቷ በክርስቶስ ደም የጸናውንና በቅዱሳን አባቶቻችን ዐፅም የታጠረችውን ቤተ ክርስቲያን ሲገፏትና ሲነቀንቋት ፈተናውን በትዕግሥት በማስተዋልና በትምህርት በመከላከል ትቋቋመዋለች፡፡ ይህ የብዙ ዘመን ልማዷ ነው፡፡ መቼውንም ቢሆን ግራ አያጋባትም፡፡

አባቶቻችን ያቆዩን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ጥንታዊት የቀናች፣ የጠራች፣ ስለሆነች ተካታዮቿን የምታኮራ እንጂ የምታሳፍር አይደለችም፡፡... በሰዎች የግል ድካም እንጻርም አትመዘንም፡፡ ለመከራም አትበገርም፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን እስከ ዛሬ ድረስ በእምነቷ፣ በጾሟና በጸሎቷ የማያቋርጥ የገቢረ ተአምራት ወመንክራት፣ ኀይላትም ሥራ ስትሠራ የምትገኝ ለተከታዮቿ ተስፋ ሆና የምትኖር እውነተኛ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ርግጥ ነው፤ በቅን ልቡናና በትሑት ሰብእና ለተቀበለው ሸክሟ ቀላል ቀንበሯ ልዝብ ነው፡፡ ዳሩ ግን በገድል የተቀመመ ሕጓ፣ ባህሏና ሥርዐቷ ጥብቅ ስለሆነ የሕግና የሥርዐት ቀንበር ላለመደ ስስ ጫንቃ አይመችም፡፡ መንገዱ ቀጭን፣ በሯ ጠባብ ነው፡፡ የእግዚአብሔርም መንግሥት የምትወርሰው በመከራ መስቀልና ብዙ ትዕግሥት፣ በዚሁ ቀጭን መንገድ ተጉዞና በጠባቡ በር ዐልፎ ስለሆነ በቀና ሃይማኖት ጸንቶ፣ በጾም በጸሎት ተወስኖ ሕይወቱን = አኗኗሩን በሥነ ምግባር፣ ገዝቶ በአበው፣ መንፈሳዊ መንገድ መጓዝ ለክርስቲያን አምላካዊ ትእዛዝ ነው፡፡ ማቴ. 7-13-05 የሐዋ.14-22 ይህ ጠባብ በርና ቀጭን መንገድ የሃሪካችን መዛባት የለበትም፡፡ ተቆርቋሪዎች እንሁን፡፡ የወይራ ዛፍ ተቀጥላው ብሳና ቢሆን እጅግ ያሳፍራልና፡፡ በነገረ ጠቢባን «ሳይረቱ አይበረቱ» ተብሏልና፡፡

ለመሆኑስ አባቶቻችን ታቦት ተሸክመው እየዘመቱ ከጾም ጸሎታቸው ጋር በተጋድሎ አጥንታቸውን ከስክሰው፣ ደማቸውን አፍስሰው በአቆዩአት ኢትዮጵያ ሀገራችን ነጻነታችንን ማን ይነካብናል ብለን እንሰጋለን? ሕግ አክባሪነትና ወሰን የሌለው ትዕግሥታችን ካልሆነ በስተቀር ለመሥዋትነቱ ከቶ የእነማን ልጆች እንደሆን ሊዘነጋ አይገባምና በአካልም በመንፈስም ስለ ሃይማኖታችን እንበርታ፡፡ የእውነተኛ ሃይማኖት ዐላማው፣ ውጤቱ እስከ ሞት ድረስ እንኳ ትንሽም አለመፍራት መሆኑን ማስታወስ አለብን፡፡ ት.ዳ.3-13-ፍጻ፡፡ አሁንም እንደ ቀድሞው መንፈሰ ኀይልን ታጥቀን እንነሣ፤ አምላካችን እንደ አባቶቻችን የኀይልና የጥበብ መንፈስን እንጂ የፍርሀትና የመደንገጥ ሀብትን አልሰጠንምና በሃይማኖታችን ማንንም አንፍራ፤ አንሸበር፡፡ የዜግነት ግዴታችንን እየተወጣን መብታችንን ጠብቀን ለማስጠበቅ እንታገል፡፡ 2ጢሞ.1-7፡፡


በሰፊዋ ሀገራችን እንኳን ተወልደው ያሉ ዜጎቿ ቀርቶ ከተለያዩ ሀገሮች የሚመጡ ባዕዳን ሁሉ በተለያየ እምነታቸው ተከራይተውና ተጎራብተው እንዲኖሩ ቤተ ክርስቲያናችን አልተቃወመችም፡፡ ከማንኛውም የእምነት መሳይ ተቋም ደልላ የእንጀራ ልጆች ለማፍራትም አትፈልግም፡፡ ከጅሏትም አያውቅ፡፡ ይህን የሚያደርጉ ግን ሌሎች ናቸው፤ እዚህ ላይ ስማቸው ባይጠራም በዚሁ የሃይማኖት መሳይ ኑፋቄ የደላላነት ግብራቸው ይታወቃሉ፡፡ ማቴ. 7-15

«የሁሉ ሰው መብትና ነጻነት ሰብአዊ ፍላጎትም ተጠብቆ በእኩልነት እንኑር» የሚለውን የአስተዳደር መርሕ እንቀበላለን፡፡ አምላካዊ ሕግም ነው፡፡ በሃይማኖት ከማይመስሉን ጋር ግን በእምነት ጉዳይ መቼም ቢሆን አንድነት የለንም አይስማማንም፡፡ ከይዞታችንና መብታችን ሌሎች እንዲገቡብንም አንፈልግም፡፡ እኛም ከነሱ የምንሻው ምንም ነገር የለም፡፡ አይጠቅመንምና፡፡ ይህ ምርጫችን ነው፡፡ ግድ የሚለን የለም፡፡ «ሲኖሩ ልጥቅ፣ ሲሔዱ ምንጥቅ» የሚለው የአበው ምሳሌያዊ ቃለ ኀይል ሥጋችንን ዐልፎ ዐጥንታችንን በማስተዋል አለምልሞታልና፡፡ ይልቁንም «ብርሃንን ከጨለማ ጋር የሚቀላቅለው ማነው?» የሚለው ቃለ ቅዱስ መጽሐፍ ጠፈር፣ ደፈር ሆኖ ይከለክለናል፡፡ክርስትናችንን ይበርዝብናል ክልክል ነው፡፡ 2ኛቆሮ.6-14-ፍጻ፡፡ ይህን በጥሞና እንገንዘበው፡፡ እኛ ሃይማኖት መጽደቂያ፣ ምግባረ ሃይማኖት ማጽደቂያ እንጂ የሥጋ መተዳደሪያ እንዳልሆነ በውል ስለምናውቅ የሃይማኖትን ጉዳይ ከማናቸውም ሥጋዊና ጊዜያዊ ደስታ ጥቅም ጋር አናያይዘውም፡፡. . . ለዚህም ብለን ሃይማኖትና ሥርዐታችንን አንሸጥም፤ አንለዋውጥም፡፡ ይህ የቅዱሳን አበው ትውፊታችን ነው፡፡ ከደማችን የተዋሐደ ክርስቲያናዊ ጠባያችንም ይኸው ነው፡፡ ሮሜ12-18 ነገር ግን ይህ አቋምና ጠባያችን ከሞኝነት ተቆጥሮ ያላችሁን ሁሉ እንቀማችሁ እንቀስጣችሁ የሚሉንን አምረን እንቃወማለን፡፡ ይገባናልም፡፡ ብዙዎች የእምነት ተቋሞች ሳይሆኑ ነን ባዮች የታሪክና የሃይማኖት መሠረታቸውን እየለቀቁ፣ የነበራቸውን ትውፊት በቁሳቁስና በኃላፊ ጥቅም እየለወጡ ባዶ እጃቸውን ስለቀሩ እኛ ከቅዱሳን አበው ወርሰን ጠብቀንና አጥብቀን የያዝነውን ነፍስ እንዳላወቀ ሕፃን «ካክሽ» እያሉ በማስጣል እኛነታችንን ሊአስረሱን ይፈልጋሉ፤ አልፈው ተርፈውም ወቅትንና አጋጣሚን ዐይነተኛ ተገን /መሣሪያ/ በማድረግ፣ ነገሮችንም ከፖለቲካና ከግዚያዊ ችግር ጋር በማስተሳሰር የሕዝብን አስተያየት ለማዘናጋትና የመብታችን ተካፋዮች ለመሆን መስለው ይቀርባሉ፡፡ ከሃይማኖት መሳይ ቤተሰባቸው ለጊዜያዊ ችግር የሚገኘውን ጥቂት ርዳታ የሃይማኖት፣ የታሪክና የቅርስ መለወጫ ሊአደርጉትም በእጅጉ ይሻሉ፡፡

እውነተኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን «ኩራት እራቱ» ስለሆነ እንደኤሳው ብኩርናውን በጊዜያዊ ጥቅም /ነገር/ አይለውጥም፡፡ «ነብር ዥንጉርጉርነቱን» እንደማይለውጥ የኢትዮጵያ ሕዝብም፣ ለሃይማኖቱ፣ ለክብሩ፣ ለታሪኩና፣ ለነጻነቱ መሞት እንኳ የተለየ መታወቂያው፣ የማይለወጥ ጠባዩ ነው፡፡ ኤር. 13-23፡፡

በዐያሌው ከልብ የተወደዳችሁ፣ እውነቱ ያልተሰወራችሁ የቤተ ክርስቲያን አባላት ሆይ!

የእምነታችሁና ሥርዐታችሁ ጠባቂዎች፣ የቤተ ክርስቲያናችን ሕይወቷ ደስታዋና ክብሯ ተከታዮቿ እናንት ምእመናን ስለሆናችሁ ልጆቻችሁና ወዳጆቻችሁ በዐዲስ የሃይማኖት ትምህርት መሰል ክሕደት እንዳይወስዱ ጊዜና ቦታ በማይገድባቸው ወደ ጥፋት በሚወስዱ ሰፋፊ መንገዶች ከሚመሩ አዘናጊዎች መናፍቃንና ቢጽ ሐሳውያን መምህራን እንድትጠበቁ፣ «ዐደራ»! ትላችኋለች እናታችሁ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን፡፡ ደግሞም በቅዱሳን አበው ሃይማኖታችሁ እንድትጸኑ ታሪካችሁን፣ ሀገራችሁን ባህላቸሁን፣ ፍቅራችሁን፣ አንድነታችሁን ጠብቃችሁ በጥንቃቄና በሥርዐት እንድትኖሩ፣ እኛም እጅግ ጥብቅ የሆነ መንፈሳዊ ፍቅር የተመላ መልእክታችንን በእናት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሕያው ስም ከቅን ልቡና በመነጨ ሐሳብ አናስተላልፋልን፡፡ 1ቆሮ.14-15

መድኀኒታችን እንዳስጠነቀቀው ከሐሰተኞች መምህራን ተጠበቁ፤ የዘመኑን ምትሐታዊ ሒደትና ይዘት ዕወቁ፤ በመንፈሳዊ ሕይወት ጽኑ፡፡ በተለያዩ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ችግሮች ምክንያት ከዓለም ኅብረተሰብ የምናገኘው ጊዜያዊ ርዳታ በሰብአዊና ማኅበራዊ ግዴታ ላይ የተመሠረተ እንጂ የሃይማኖትና የታሪክ ለውጥ መዋዋያ አይደለም፡፡ የመልካም ጠባይና ማንነት መለወጫም አይደለም፡፡ ድኽነትን ከየቤታችን ለማጥፋት ሥራን እንውደድ፡፡ እርስ በርስ እንረዳዳ፡፡ ችግረኛውን ተባብረን ነፃ እናውጣው፡፡ እንደቀሞው ባህላችን ያለንን ተካፍለን ዐብረን እንብላ እንጂ መነፋፈግን አንልመድ፡፡ በዚህ ጊዜ የበረከት አምላክ ረድኤት በረከቱን ይሰጠናል፡፡ ወገንና መጠናችንንም ለይተን ዕንወቅ እንጂ የቅዱሳን አበው ልጆች እዚህ ላይ አትኩረን ልብ እንበል፡፡ በምንም ሰበብ እንደ ገደል ውሃ ክንብል አንበል፡፡ ይህን ከመሰለው ደካማ ሐሳብም ልጆቻችሁን በብዙ ዘዴ ጠብቁ፡፡ የሃይማኖት ፍቅር ቁም ነገሩም ከቤተሰብ በላይ ስለሆነም ይህን አትርሱ፡፡ ምንም ቢሆን ክፉን ማስወጣት ያቃተው ስንኳ ቢኖር መውጣት አያቅተውም፡፡ ማቴ. 10-36-40

በቤተሰብ አባላት በወዳጅ ዘመድና በጎረቤት መስለው የሚመጡ የበግ ለምድ ለባሾችን ዕወቁባቸው፡፡ ፊልጵ. 3-2 ዋናው ዘዴ ከእነርሱ ጋር ዐብሮ አለመራመድ፣ ዐብሮ አለመገኘት ነው፡፡ ከደጃቸውም አለመቆም ነው፡፡ የእነርሱ የሆነንም ሁሉ አለመከጀል፣ ፈጽሞ አለመንካት ነው፡፡ የጠላት ገንዘብ ምግብ፣ ልብስና ቁሳቁስ በሙሉ የተወገዘ፣ እርኩስ ነው፡፡ ሕርም ነው፣ መርዝ ነው፡፡ ደዌ ክሕደትን ያመጣል እንጂ ጤና ሕይወት አይሆንም፡፡ እንወቅ፡፡ በሌላ በኩል በእውነቱ ከሆነ አንድ ልጅ እናቱ መልካም ፍትፍት ምግብ አዘገጅታ ባትሰጠው እንኳ ከጎረቤት ሔዶ በመርዝ የተቀመመ ምግብ መብላትና መታመም፣ ዐልፎም መሞት የለበትም፡፡ እንደዚሁም ታዲያ በሥራዋና በመልካም አቋሟ ሁሉ እንደ መማር፣ ባይሆንም እንደ መጠየቅ «እናቴ ቤተ ክርስቲያን ጮኻ ባታስተምረኝ ነው» እያሉ ከክሕደትና ኑፋቄ ማኅበር እንደ እሳት ራት ዘሎ መግባት አግባብ አይደለም፤ የሰውነት መመዘኛም አይሆንም፡፡ እንግዲያውስ ተጠበቁ፡፡ ተጠንቀቁ፤ ሌላ የሚያዋጣ ነገር ፊጽሞ አይገኝም፤ ዐጉል መዋተት ብቻ ይሆናል፡፡ በዚህ ዐዲስ ዘመን ዐዳዲስ የሃይማኖት መሳይ ድርጅት የቀናች አንዲት እውነተኛ የአበው ሃይማኖትን ሊተካት ቀርቶ ሊመስላት አይችልም፡፡ ይህን የመሰለው ሐሳብ የዘባቾች ከንቱ ዘበት ነው፡፡

ሰው ሆኖ በተዋሕዶ ተገልጾ በባሕርይ ክብሩ ያለ መድኀኒታችን የባሕርይ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስንም ከባለቤቱ እንደባዘነ የቤት እንስሳ በዚህ ዘመን በየሜዳውና በየግል አጋጣሚ «አገኘሁት» አይባልም፡፡ ድፍን ያለ ሐሰት ነው፡፡ እናስተውል፡፡ ወይም እራሳቸውን እንኳ በማያውቁ ልሙጥ ማይማን ዘባቾች «ተቀበሉት» የሚባልለት ቁስ አካል፣ አልያም ማደሪያ የሌለው ባይተዋር አይደለም፡፡ ዓለምን በእጁ የያዘ እርሱ በእኛ የሚወሰን ይመስል የተለያየ ችግር ባለባቸው፣ ተግባር ሥጋዊን በጠሉ፣ የዕለት ምግብ ፈላጊዎች ልንጎተትና በእነርሱ ዐቅም ተታለን በየዛኒጋባው ልንመሰግ የሚገባን ሰብአዊ ግብር አይደለንም፡፡ አሁንም በሃይማኖት ቁሙ፣ ጠንክሩ፣ ንቁም በተማራችሁትና በያዛችሁት እውነተኛ ሃይማኖታችሁ ጽኑ፡፡ ባይረዳችሁ እንኳ ከእናታችሁ ቅድስት ቤተክርስቲያን ተግታችሁ ተማሩ፤ ጠይቁ፡፡ «ርትዕት ይእቲ ሃይማኖቶሙ ለቅዱሳን አበዊነ = የቅዱሳን አባቶቻችን ሃይማኖት የቀናች፣ የጸናች እውነተኛም ናት» አማራጭ ተለዋጭ ፈጽሞ የላትም፤ ዘለዓለማዊት ናት፡፡ በባዕድ ዘመን አመጣሽ ትምህርት እንዳትወሰዱ አሁንም፣ ምን ጊዜም ተጠበቁ፤ ዕወቁ፤ ተጠንቀቁ፡፡ በቃለ አበው ሐዋርያት ተገዝታችኋል፡፡ ስለእውነተኛዋ ሃይማኖታችሁ በየትና በማን እንደምትማሩ ለይታችሁ አስተውሉ፡፡ ተረዱም፡፡ በቀናች ሃይማኖታችሁ ጸንታችሁ በሰላም በብርታት እንድትኖሩም፣ ለጸሎትና ምህላ ትጉ በሥራችሁ ሁሉ እንዳትሰናከሉም፣ እንቅፋታችሁን «ወአምላከ ሰላም ለይቀጥቅጦ ለሰይጣን በታሕተ እገሪክሙ ፍጡነ = የሰላም አምላክ ፈጥሮ ሰይጣንን ከእግራችሁ በታች ይቀጥቅጠው!!!» ኀያሉ አምላክ ኀይል፣ ከለላ፣ ይሁነን፡፡ የእመቤታችን ቅድስት፣ ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ጸሎት ግርማ ሞገስ ይሁነን፡፡ ሮሜ 16-20፣ 1ኛቆሮ.16-13፣ ገላ.1-8፣ ቆላ.2-6-11

ምንጊዜም «ክፉ አይልከፋችሁ፣ ደግ አይለፋችሁ»

ከሊቀ ትጉሃን ኀ/ጊዮርጊስ ዳኘ
በጠ/ቤተ ክህነት የዕቅድና ልማት መምሪያ ም/ሓላፊ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
አምላከ ሰማያት ወምድር

No comments:

Post a Comment