Thursday, November 1, 2012

ጾመ ጽጌ ክፍል 2

የማኅሌተ ጽጌና የጾመ ጽጌ አጀማመር
  የእመቤታችን የስደቷ መታሰቢያ ወር በቤተ ክርስቲያናችን የሚከበረው በማኅሌት፣ በቅዳሴና በዝክር ነው፡፡ በወርኃ ጽጌ ባሉት ሳምንታት ከቅዳሜ ማታ እስከ እሑድ ጠዋት አበው ካህናት የሚያቀርቡት ዝማሬ ከቅዱስ ያሬድ ድጓ፣ ከማኅሌት ጽጌና ከሰቆቃው ድንግል የተውጣጣና ሦስት ወገን ያለው ነው፡፡ ዝክሩም፣ በአሁኑ ወቅት በከተሞች አካባቢ እየተረሳ ቢመጣም፣ ዘወትር እሑድ የአንድ አካባቢ ሰዎች ማዕከላዊ በሆነ ቦታ ተሰባስበው በእመቤታችን ስም የሚዘክሩት ነው፡፡ ዐቅመ ደካሞች፣ ድሆችና መንገደኞች ተጠርተው በእመቤታችን ስም እንዲበሉና እንዲጠጡ ይደረጋል፡፡ ይህም ትውፊት እመቤታችን ወደ ኢትዮጵያ በመጣች ጊዜ ኢትዮጵያውያን  አባቶችና እናቶች ያደረጉላትን መስተንግዶ ለማሰብ ነው፡፡

 

የጻድቁ አቡነ ዜና ማርቆስ ገድል የጽጌን ጾም አስመልክቶ የሚከተለውን ይተርካል፣ “አቡነ ዜና ማርቆስ የምሁርን ሕዝብ አስተምረውና አሳምነው ካጠመቁ በኋላ እንደገና ለማስተማር ወደ ይፋት ሄዱ፡፡ በዚያም ክርስቶስ ሥጋ ለብለሶ ከድንግል ማርያም ተወልዶ ሰለኛ ኃጢአት ተሰቅሎ ሞተ፣ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተነሣ እያሉ ሲያስተምሩ አንድ አይሁዳዊ ሰማ፡፡ ይህም አይሁዳዊ እንዴት እነዲህ እያለ ያስተምራል ሲል ተቃውሞ አቀረበባቸው፡፡ እርሳቸውም የብሉይና ሐዲስ ዐዋቂና ብልህ ስለነበሩ የሚከተለውን ጥቅስ እየጠቀሱ ያስረዱት ጀመር፡፡”

“ትወዕዕ በትር እምሥርወ እሴይ፣ ወየዓርግ ጽጌ እምጒንዱ”፣ ትርጓሜውም “ከእሴይ ሥር በትር ትወጣለች ከግንዱም አበባ ይወጣል ያቆጠቁጣል” ማለት ነው፡፡ በትር አመቤታችን ድንግል ማርያም ስትሆን ጽጌ ደግሞ ከእርስዋ የተወለደው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ሲሉ አቡነ ዜና ማርቆስ በትንቢተ ኢሳያስ ምዕራፍ 111  ያለውን ትርጓሜውንና ምሥጢሩን ዘርዝረው ባስረዱት ጊዜ አይሁዳዊው አምኖ ትምህርታቸውን ተቀበለ፡፡
አቡነ ዜና ማርቆስም ሐዲስ ኪዳን አስተምረው አሳምነው ካጠመቁት በኋላ አመነኮሱት፣ ስሙንም ጽጌ ብርሃን ምሁረ ኦሪት ስለ ነበር መጻሕፍተ ሐዲሳትን ለማጥናት ምቹ ሆነለት፣ ቀጥሎም ከርሳቸው ጋረ እየተዘዋወረ ወንጌል ያስተምር ጀመር፡፡
ይህንንም ከፈጸመ በኋላ እንደ መዝሙረ ዳዊት መቶ ሃምሳ አድርጎ ማኅሌተ ጽጌ ደረሰ፡፡ አባ ጽጌ ብርሃን ይህንን በደረሰበት ጊዜ የወረኢሉ ተወላጅና የደብረ ሐንታው አባ ገብረ ማርያም አማካሪው ነበር፡፡ ድርሰቱንም ሲደርስ ቤት እየመታና በአምስት ስንኝ እየከፋፈለ ነው፡፡ አባ ጽጌ ብርሃንና አባ ገብረ ማርያም መስከረም 26 ቀን እስከ ኅዳር 5 ቀን ድረስ ማኅሌት ጽጌ ለመቆምና የጽጌን ጾም ለመጾም በየዓመቱ በደብረ ብሥራት እየመጡ ይሰነብቱና ቁስቋምን ውለው ወደየበዓታቸው ይመለሱ ነበር፡፡
ይህም ማኅሌተ ጽጌ ድርሰት በሰምና ወርቅ የተደረሰ ሆኖ አበባን ሰም፣ ጌታንና እመቤታችንን ወርቅ እያደረገ ስለሚናገር ለሚያነበውና ለሚጸልየው እጅግ ያስደስታል፡፡
እንግዲህ ከላይ ከቀረበው የአባታችን የገድል ክፍል ለመረዳት እንደሚቻለው አባ ጽጌ ማኅሌት መቆም ወቅቱንም በፈቃዳቸው መጾም  ጀምረዋል፡፡ ዘመኑም በ14ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ነው፡፡
ከዚያ ወዲህ ግን ጥቂት በጥቂት እያለ አብያተ ክርስቲያናት በወርኃ ጽጌ የጽጌን ማኅሌት መቆም ጀመሩ፡፡ ጥቂት መነኮሳትና አንዳንድ ምእመናንም በገዛ ፈቃዳቸው ወቅቱን መጾም ያዙ፡፡ በዘመናችን በወርኃ ጽጌ የጽጌን ማኅሌት መቆም ስለ ተለመደ ከማታው በሦስት ሰዓት ይደወላል፡፡ ሴቱ ወንዱ፣ ትንሹም ትልቁም ይሰበሰባል፣ ማኅሌተ ጽጌ እየተዜመ፣ አስፈላጊ የሆነው በጸናጽል በከበሮ እየተመረገደና እየተወረበ እየተሸበሸበ እስከ ጠዋቱ 12 ሰዓት ድረስ ተቁሞ ይታደራል፡፡ የጽጌ ጾም የውዴታ /የፈቃድ/ እንጂ የግዴታ አይደለም፡፡
የእመቤታችንን ስደት በማሰብ ከትሩፋት ወገን የሚጾም ስለሆነ ምእመናን ሁሉ እንዲጾሙት አይገደዱም የሚጾመው የማይጾመውን ለምን አልጾምክም ብሎ ሊፈርድበት፣ ለራሱም እየጾምኩ ነው ብሎ መናገር አይገባውም፡፡ የፈቃድ መሆኑንም የሚያሳየው ይኸው ነው፡፡ የማይጾመውም በልቡ ያመሰግናል፣ስደቷን እያሰበ ማኅሌቷን እየዘመረ ያሳልፋል፡፡
ለ. ጾመ ዮዲት
ይህን ጾም በሀገራችን ምእመናን ጾመ ጳጉሜን በማለት ይጠሩታል፡፡ እንደ ጽጌ ጾም የታወቀ ባይሆንም በዓመቱ መጨረሻ ወር በጳጉሜን የሚጾም ነው፡፡ የዮዲት ጾም የሚባለውም እርሷ ስለ ጾመችው ነው፡፡ የፋርስ ንጉሥ ናቡከደነፆር በሠራዊቱ ተመክቶ ሹም ጠላት አጥፋ፣ ድንበር አሰፋ ካመነው እጅ መንሻ እየተቀበልህ ያላመነውን እያሳመንህ ና ብሎ ለጦር አበጋዙ ለሆሎፎርኒስ ትእዛዝ ሰጠ፡፡ ዮዲ2፣2-7፡፡ እርሱም እንደታዘዘው በኃይላቸው የታመኑ 12 ሺህ እግረኞችንና በፈረስ የተቀመጡ 12 ሺህ ጦረኞችን እየመራ ዘምቶ ካመነው እጅ መንሻ እየተቀበለ ያላመነውን እያሳመነ ብዙ አገሮችን እያጠፋ ሲሔድ ከአይሁድ ከተማ ደረሰ፡፡
የእሥራኤል ልጆችም ሆሎፎርኒስ የአሕዛብን አገር እንዳጠፋና ንብረታቸውን እንደዘረፈ ሰምተው ስለ ቤተ መቅደሱ መፍረስና ሰለ ንዋያተ ቅድሳት መርከሰ ማቅ ለብሰው አመድ ነስንሰው ከቤተ መቅደሱ በር ወድቀው አለቀሱ፡፡ እግዚአብሔር ልመናቸውን ሰምቶ ከዚህ ጥፋትና ወረራ እንዲያድናቸው እንዲጠብቃቸው መሠውያውንም ሳይቀር ማቅ አለበሱት፡፡ ዮዲ. 42-15፡፡
እብሪተኛው ቢትወደድ ግን የሕዝበ እሥራኤልን ምንጫቸውንና ውኃ አስቀድሞ በመያዝ እንዲቸገሩና ወደው ፈቅደው እጃቸውን እንዲሰጡ ለማድረግ የውኃውን ጉድጓድ ተቆጣጥሮ በሠራዊቱ አስጠበቀ፡፡ በመሆኑም የእሥራኤል ልጆች በውኃ ጥም ከመቸገርና ከመሞት ይልቅ እጃቸውን ለጠላት ለመስጠት ወሰኑ፡፡ ነገር ግን ዖዝያን የአባቶቻቸው አምላክ መልስ እስኪሰጣቸውና ቸርነቱን እስኪመልስላቸው መከራውን በትዕግሥት እንዲቀበሉ ስለመከራቸው ጸኑ፡፡ ዮዲ. 710-32፡፡
ዮዲት ባሏ ሞቶባት ከወንድ ርቃ ንጽሕናዋን ጠብቃ በጾም፣ በቀኖና፣ በትኅርምት፣ በኀዘን፣ በጸሎት ተወስና ትኖራለች “ብንችል እንዋጋለን ባንችል እንገብራለን” ሲሉ እሥራኤልን ሰምታቸው ፈጣሪያችሁን ለምን ትፈታተኑታላችሁ ያድነናል አትሉምን? ብላ ማቅ ለብሳ በራስዋ ላይ ትቢያ ነስንሳ ወደ እግዚአብሔር አለቀሰች፡፡
የፍጥረቱን ጥፋት የማይሻ ቸር አምላክም ሕዝቡን የሚያድንበትን ዕውቀትና ጥበብ ግብር በገባች በሦስተኛ ቀን ገለጸላት፡፡ ዮዲ. 82፡፡ ዮዲት እጅግ መልከ መልካም ፍጹም ደመ ግቡ ስለነበረች እግዚአብሔር በሰጣት አካል የወገኖቿን ጠላት አስታ የምታጠፋበትን ዘዴ አዘጋጀች፡፡ በመጀመሪያ ወደ እግዚአብሔር ጸለየች፡፡ ከዚያም  “ወዴት ትሔጃለሽ አትበሉኝ አምላክ እሥራኤል ይከተልሽ ብሉኝ”ብላ የኀዘን ልብሷን ጣለች፡፡ ሰውነቷን ታጠበችና ሽቱ ተቀባች፣ ባሏ በሕይወት ሳለ የምትለብሰውን የክት ልብሷን ለበሰች፣ የሚመለከቷትን ሰዎች ሁሉ እስክታስት ድረስ ፈጽማ አጌጠች፡፡ ዮዲ.102-3፡፡ ስትጨርስም እግዚአብሔር በመልክ ላይ መልክ ጨምሮራት ለመንገድ ስንቅ የሚሆናትን ወይንና የስንዴ አምባሻ ብላቴናዋን አስይዛ ከእየሩሳሌም ቅጥር ወጥታ የፈረስ ሰራዊት ወዳለበት ሄደች፡፡
 ሸማ አጣቢዎች አገኟትና  “ ዛሬስ እስራኤል መዋጋት ቢሳናቸው አንዳንድ እያሉ ወባት ሊገቡ መጡብን?” ብለው ለእኔ ትገባለች ለእኔ ትገባለች እያሉ ተሻሙባት፡፡ የንጉሥ ጃንደረባ ጋይ የሚባል ይህችስ ለጌታዬ ትገባለች አለ፣ ለምን እንደመጣች ጠይቀዋት ለመልካም ነገር እንደመጣች ሲረዱ ከጦር አበጋዙ አደረሷት፡፡ ዮዲ.1012-22፡፡ እርሱም የጾመኛ ምቀኛ እንዲሉ ለምን መጣሽ ቢላት እስራኤል ሊገቡ ጥቂት ቀርቷቸዋል፣ እርስት ሄዶብኝ እንድትመልስልኝ አስቀድሜ ደጅ እጠናለሁ ብዬ መጣሁ አለችሁ፡፡ እርሱም ወገን ለመርዳት እንደመጣች ተረዳ፣ የተለበጠ ነጭ ሀር ልብስ በተነጠፈበት በድንኳኑ እንዲያስቀምጧት እርሱ ከሚበላው ምግብ እንዲሰጧት አዘዘ፡፡ እርሷ ግን የአህዛብ ምግብ በልታ እንዳትረክስ በቂ ስንቅ የያዘች መሆኗን ገልጻ በፈለገችበት ጊዜ ለመውጣትና ለመግባት የምትችልበትን ሁናቴ አመቻቸች፡፡
አሕዛብ በዚህ ቀን ተወልደን ከዚህ ማእረግ ደርሰን ከጨለማ ወደ ብርሃን ከጠባብ ወደ ሰፊ የወጣንበትን ሲሉ የተወለዱበትን ቀን ያከብራሉ፡፡ በአንዲትም ዕለት ቢትወደዱ የአሽከሮች የምሣ ግብዣ አድርጎ ሲያበላ ሲያጠጣ ያችን እብራዊት ጥሩ ብሎ አስጠርቶ ከፊቱ አስቀምጦ ሲበላ አብዝቶ ሲጠጣ ውሏል፡፡ ዮዲ. 121-20፡፡ ከዚያም አሽከሮችን ከሁሉ አስወጥቶ ድንኳኑን ቆልፎ እንደተኛ ከባድ እንቅልፍ ያዘው ዮዲትም በሃያሉ አድረህ ሥራ ብትሠራ አትመሰገንም ነገር ግን በእኔ በደካማይቱ አድረህ ሥራ ብትሠራ ትመሰገናለህ እያለች ከፀለየች በኋላ ከራስጌው ያለውን ሰይፍ አንስታ የራስ ጠጉሩን ይዛ አንገቱን ቆርጣ በድኑን ከመሬት ጥላ ቸብቸቦውን በአቁማዳ ቋጥራ ለብላቴናዋ አሸክማ ግንዱን በታች ገልብጣ ዙፋኑን በላይ  አድርጋ ወደ ሃገሯ ተመለሰች፡፡ ዮዲ 13.1-10፡፡
ሕዝበ እሥራኤል በዚህ ድርጊቷ እጅግ ተደነቁ፣ ጠላታቸውን በእጃቸው የጣለላቸውን አግዚአብሔር አምላካቸውንም አመሰገኑ፡፡ በኋላም የሆሎፎርኒስን ራስ በተራራው ላይ ሰቅለው መዋጋት ጀመሩ፡፡ አረ ዛሬስ እሥራኤል ወንዳ ወንድ ሆኑብን ይህቺ ዕብራዊት የሌሊቱ አልበቃ ብሏት ቀኑንም ልትደግመው ነውን? ሒደህ ንጉሣችንን አስነሣው ብለው ብላቴና ቢልኩ ግንዱ በታች ዙፋኑ በላይ ሆኖ አገኘው፡፡ አውራ የሌለው ንብ አለቃ የሌለው ሕዝብ መቆም አይሆንለትምና ይህች ዕብራዊት እንዴት ተጫወተችብን ብለው ሸሽተዋል፡፡ እግር በራስ እየሆኑ አልቀዋል፡፡ እስከዮርዳኖስ እየተከተሉ አጥፍተዋቸዋል፡፡
 ዮዲት ጠላቷን ለማጥፋት የቻለችው በጦምና በጸሎት ከእግዚአብሔር አምላክ ኃይል አግኝታ ነው፡፡ ስለዚህ ምዕመናን ጥንተ ጠላታችን ሰይጣንንና ፈቃደ ስጋን ለማሸነፍ በጾም ከፈጣሪያችን ኃይልን መጎናጸፍ አለብን ብለው በጳጉሜ ወር ይጾማሉ፡፡ ኃጢያታቸውን ለንስሐ አባታቸው ተናገረው ተናዝዘው ቀኖና ተቀብለው የሚጾሙም አሉ፡፡ በሌላም በኩል በጳጉሜ ወር ዕለተ ምጽአት የሚታሰብባት በመሆንዋ ያን እያሰቡ የሚጾም አያሌ ናቸው፡፡ ጳጉሜን የዓመታት መሸጋገሪያ እንደሆነች ምጽአትም ከዚህ ዓለም ወደ ወዲያኛው መሸጋገሪያ ነውና፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ከእመቤታችን ረድኤት በረከት ያሳትፈን
 
 
 
 

No comments:

Post a Comment