Friday, January 27, 2012

ዘመነ መርዓዊ (የሙሽራ ዘመን) ጥር


አትም ኢሜይል
በመ/ር ኃይለማርያም ላቀው

HolyMarriageየጋብቻ ሕይወት በኤደን ገነት እንደተጀመረ ይታወቃል፡፡ ዘፍ 2÷26 በዘመነ ሐዲስም መርዓዊ ሰማያዊ ክርስቶስ በቃና ዘገሊላ ከእመቤታችን ጋር ተገኝቶ የዶኪማስን ጋብቻ ባርኳል ፣ ቀድሷል፡፡ ዮሐ 2÷1-10፡፡ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቃና ዘገሊላ ጋብቻን መባረኩን፣ ዓለምን ለማስተማር መገለጡን ለማዘከር ከጥር መባቻ እስከ ዐቢይ ጾም መግቢያ ያለውን ወቅት ‹‹ዘመነ መርዓዊ›› በማለት ትጠራዋለች፡፡ በመሆኑም በዚህ ወቅት በኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ጸንተው ፣በድንግልና ራሳቸውን ጠብቀው ለኖሩ ሥርዓተ ተክሊልን በመፈጸም አንድ ታደርጋቸዋለች፡፡
እንዲሁም በሥጋዊ ድካም ድንግልናቸውን ሳይጠብቁ ለኖሩ ልጆቿ ከንስሐ በኋላ ለመዓስባን የሚደርሰውን ጸሎት አድርሳ ሥርዓተ ጋብቻን ትፈጽምላቸዋለች፡፡

Thursday, January 26, 2012

ኪዳነ ምህረት



እግዝእትነ ማርያም
 ኪዳነ ምህረት ማለት የምህረት መሐላ ማለት ነው፡፡ 33 በዓላተ እግዝእትነ ድንግል ማርያም አንዱ ነው፡፡ እመቤታችንም ከጌታችን መቃብር እየሄደች በምትለምንበት ጊዜ አይሁድ ለምቀኝነት አያርፉምና ምን ልታመጣብን ነው በማለት ሊጣሏት ሲመጡ ጌታችንም ከዓይናቸው ሰውሯታል አይሁድም ጠባቂ ቢያቆሙ እመቤታችን ዕለት ዕለት መሄዷን አላቋረጠችን እመቤታችንም እንዲህ ብላ ስትጸልይ ልጄ ወዳጄ ሆይ ከስጋዬ ስጋ ከነፍሴ ነፍስ ነስተህ ሰው በመሆንህ ዘጠኝ ወር 5 ቀን በቻለችህ ማሕጸኔ ከአንተ ጋር ሀገር ለሀገር ስለ መሰደዴ መትተህ ልምናዬን ትሰማኝ ዘንድ እለምንሃለሁ አለች በዚህ ጊዜ ንውጽውጽውታ ሆነ መቃብራት ተሰነጣጠቀ ጌታችንም እልፍ ከእልፍ መላዕክቱ ጋር መጥቶ ሰላም ለኪ ማርያም ምን እንዳደርግልሽ ትለሚኚኛለሽ አላት፡፡ እርሷም መታሰቢያዬን ያደረገውን ስለ ስሜ ለችግረኛ የሚራራውን በስሜ ቤተ ክርስቲያን ያነጻውን መባዕ የሰጠውን ከሃይማኖት ከፍቅር ጽናት ልጁን በስሜ የጠራውን ሁሉ ማርልኝ ከሞተ ስጋ ከሞተ ነፍስ አድንልኝ አለችው፡፡ ጌታችንም ይህን ሁለ እንዳደርግልሽ መሐልኩ ለኪ በርእስየ ወበ አቡየ ሕያው ወበመንፈስ ቅዱስ ብሎ ቃል ገብቶላት አርጓል፡፡ 

Thursday, January 19, 2012

እንኳን ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥምቀት አደረሰን

የጥምቀት አስፈላጊነት
በቀሲስ ብርሃኑ ጎበና


በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከኒቂያ ጉባኤ በኋላ ከተነሱት አባቶች አንዱ “በፊተኛው ትንሣኤ ዕድል ያለው ብፁዕና ቅዱስ ነው ሁለተኛው ሞት በእነርሱ ላይ ሥልጣን የለውም” ራእይ ፳፥፮ የሚለውን የወንጌላዊው ዮሐንስን አባባል በተረጎመበት የእግዚአብሔር ከተማ በሚለው መጽሐፉ ላይ ፊተኛው ትንሣኤ የተባለው ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና የምናገኝበት ጥምቀት እንደሆነ ገልጿል (De Civitate Dei,xx,6)።



ጥምቀተ ክርስቶስ


ክርስቶስን መሠረት ያደረገ እምነት ሁሉ “ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም” ዮሐ. ፫፥፫ የሚለው የጌታ ትምህርት መመሪያው ሊሆን ግድ ነው። ጌታ እንዳስተማረውም ያለጥምቀት ድኅነት የለም።

ጥምቀት በሚታየው አገልግሎት በውኃ ውስጥ ገብቶ መነከር፣ መዘፈቅ፣ ውኃ ውስጥ ገብቶ መውጣት ማለት ሲሆን በሚታየው አገልግሎት የሚገኘው የማይታይ ጸጋ ግን ብዙ ነው። የሚከተሉት በጥምቀት የሚገኙ የማይታዩ ጸጋዎች ናቸው፡-

ድኅነት

“ያመነ የተጠመቀ ይድናል” ማር. ፲፮፥፲፮። የድኅነት ባለቤት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በግልጽ እንደተናገረው ዘላለማዊ ድኅነትን ለማግኘት የሚሻ ሁሉ  ወልድ ዋሕድ በምትለው ሃይማኖት አምኖ መጠመቅ ግድ ይለዋል። ከጌታ ከቃሉ የተማረ ቅዱስ ጴጥሮስ የመምህሩን ትምህርት መሠረት አድርጎ “ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍስ በውኃ የዳኑበት መርከብ ሲዘጋጅ፤ የእግዚአብሔር ትዕግስት በኖኅ ዘመን በቆየ ጊዜ ቀድሞ አልታዘዙም። ይህም ውኃ ደግሞ ማለት ጥምቀት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል የሰውነትን እድፍ ማስወገድ አይደለም” ብሏል። ፩ኛ ጴጥ. ፫፥፳-፳፩። ኖኅና ቤተሰቡ የዳኑበት ውኃ ምሳሌነቱ የጥምቀት መሆኑን ገልጾ አሁንም በክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት ያመኑ ሁሉ በጥምቀት ድኅነትን እንደሚያገኙ በግልጽ ቃል ተናግሯል።

Friday, January 13, 2012

ምሥጢረ ሥላሴ


እንኳን ለጥር ሥላሴ በዓል በሰላም አደረሳችሁ

ምሥጢር
ሥሉስ ቅዱስ
አመሠጠረ ከሚለው ግስ የተገኘ ቃል ሲሆን ስውር ድብቅ ሽሽግ ማለት ሲሆን አምስቱ አዕማደ ምሥጢራትም ምሥጢር የተባሉበት ምክንያት
በሥጋዊ ጥበብ ምርምር መረዳት ስለማይቻሉ
ላመኑት እንጂ ላላመኑት ሰዎች የተሰወሩ በመሆኑ
 ምሥጢር በሁለት ይከፈላል፡፡ እነርሱም፡-
 የፈጣሪ ምሥጢር፡- ሊገለጥ የማይችል ነው፡፡ እስከ የሌለው ምሥጢርም ይባላል፡፡
 የፍጡራን ምሥጢር፡- በጊዜ የሚገለጥ /የሚታወቅ/ ነው፡፡ የሰውና የመላእክት ምሥጢር በዚህ ውስጥ የሚካተት ነው፡፡

Friday, January 6, 2012

እንኳን ለጌታችን ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት በሰላም አደረሳችሁ!


“እነሆ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኅን ተወልዶላችኋል” (ሉቃ.2፡11) አትም ኢሜይል

ታኅሣሥ 27/2004 ዓ.ም
በዲ/ን በረከት አዝመራው እና በዲ/ን አሉላ መብራቱ

“ዘሎቱ ሰብአ ሰገል ሰገዱ ሎቱ፤ አማን መንክር ስብሐተ ልደቱ፤
ለእርሱ ሰብአ ሰገል የሰገዱለት፣ የልደቱ ክብር ድንቅ ነው።”

እግዚአብሔርን በእምነት ደስ ያሰኙ ቅዱሳን ከእስራኤላውያን ተነሥተው ነበር።(ዕብ.11) የአባቶች አለቃ ከሆነው ከአብርሃም ጀምሮ እስከ ጌታችን ሰው መሆን (ዘመነ ሥጋዌ) ድረስ ብዙ ታላላቅ አባቶችና እናቶች በእስራኤል ዘንድ ተገኝተዋል።

christmasየእስራኤል ታሪክ ሁልጊዜ መልካም ታሪክ ብቻ ግን አይደለም፤ እግዚአብሔርን ያሳዘኑባቸው ጊዜያት ጥቂቶች አይደሉም። በዚህ ጊዜ በዙሪያቸው ባሉ ነገሥታት እየተማረኩ ወደ ፋርስ፣ ባቢሎንና ግብጽ እየወረዱ ለአሕዛብ የተገዙበትና የገበሩበት ጊዜም ነበር። ንስሐ ገብተው ወደ እግዚአብሔር ሲመለሱ ደግሞ እግዚአብሔር ከእነርሱ መካከል ሰው እያስነሣ ያድናቸው ነበር። ለአባቶቻቸው የገባውን የዘለዓለም ቃልኪዳን እያሰበ ይረዳቸውም ነበር። (መዝ.77 (78))
እነሆ በዚህ የታሪክ መስመር ውስጥ ወደር የሌለው፣ ሁለተኛ በዓለም ታሪክ የማይደገም ታላቅ ነገር ተከሰተ። የእግዚአብሔር ልጅ የሰውን ሥጋ ለብሶ እንደ ሰው በምድር ላይ ተገለጠ። ጥበበኛው ሰሎሞን “አበባ በምድራችን ታየ” ብሎ የተናገረው ትንቢት ተፈጸመ፤ አበባ ክርስቶስ ምድር በተባለ ሥጋችን ተገልጧልና(መኃ.2፥12)። የዓለም መድኃኒት እግዚአብሔርነቱን ሳይተው ሰው ሆነ። እነሆ የእግዚአብሔር ልጅ የአብርሃም ልጅ ተባለ፤ የዳዊት ጌታ የዳዊት ልጅ ተባለ። (ማቴ.1፥1) የዳዊት ፈጣሪ በዳዊት ከተማ በቤተልሔም በከብቶች በረት ተወለደ። አባቶቻቸው በአንድ ዘመን ዳዊት የነገሠባትን ከተማ ያፈረሱ፣ የዳዊትን ልጆች በባርነት የገዙ የፋርስና የአረብ ነገሥታት የዳዊትን መንግሥት ለዘለዓለም ለሚያጸናው ሕፃን ለኢየሱስ ክርስቶስ ሰገዱ፤ ተገዙ።

Tuesday, January 3, 2012

የጥያቄዎች መልስ



የገና እና የጥምቀት በዓላት ሲደርሱ በምእመናኑ ዘወትር የሚጠየቁ ጥያቄዎች አሉ፡፡ እነዚህን እና መሰል የሕዝቡን የዘወትር ጥያቄዎች መልስ የያዘ የማያዳግም ጥራዝ ማውጣት ከሊቃውንት ጉባኤ የሚጠበቅ ነው፡፡ አብዛኞቹ ጉዳዮች አበው ቀድመው ሥርዓት የሠሩባቸው እና ማብራርያ ብቻ የሚያስፈልጋቸው ናቸውና፡፡ ለዛሬ ሦስቱን ብቻ እንመልስ፡፡
ገና እና ጥምቀት ዓርብ እና ረቡዕ ቢውሉ ይበላባቸዋል ወይስ ይጾማሉ?
ፍትሐ ነገሥት፡ ዳግመኛ በየሳምንቱ ዓርብ እና ረቡዕን መጾም ነው፡፡ በዓለ ሃምሳ፣ የልደት እና የጥምቀት በዓል የተባበሩባቸው ጊዜ ካልሆነ በቀር /ዐንቀጽ 15 566/
የዓርብን እና የረቡዕን ጾም ግን ከልደት፣ከጥምቀት እና ከበዓለ ሃምሳ በቀር ዘወትር ይጹሙ /ዐንቀጽ 15፣ቁ 603/
የገና እና የጥምቀት ቅዳሴ ስንት ሰዓት ነው?
ፍትሐ ነገሥት፡ ስለ ልደት እና ጥምቀት ግን በዚያ ዘመን በኒቂያ የተሰበሰቡ ሊቃውንት ቅዳሴው በሌሊት ይሆን ዘንድ አዘዙ /ዐንቀጽ 15 595/
ልደት ጋድ አለው?