Friday, January 27, 2012

ዘመነ መርዓዊ (የሙሽራ ዘመን) ጥር


አትም ኢሜይል
በመ/ር ኃይለማርያም ላቀው

HolyMarriageየጋብቻ ሕይወት በኤደን ገነት እንደተጀመረ ይታወቃል፡፡ ዘፍ 2÷26 በዘመነ ሐዲስም መርዓዊ ሰማያዊ ክርስቶስ በቃና ዘገሊላ ከእመቤታችን ጋር ተገኝቶ የዶኪማስን ጋብቻ ባርኳል ፣ ቀድሷል፡፡ ዮሐ 2÷1-10፡፡ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቃና ዘገሊላ ጋብቻን መባረኩን፣ ዓለምን ለማስተማር መገለጡን ለማዘከር ከጥር መባቻ እስከ ዐቢይ ጾም መግቢያ ያለውን ወቅት ‹‹ዘመነ መርዓዊ›› በማለት ትጠራዋለች፡፡ በመሆኑም በዚህ ወቅት በኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ጸንተው ፣በድንግልና ራሳቸውን ጠብቀው ለኖሩ ሥርዓተ ተክሊልን በመፈጸም አንድ ታደርጋቸዋለች፡፡
እንዲሁም በሥጋዊ ድካም ድንግልናቸውን ሳይጠብቁ ለኖሩ ልጆቿ ከንስሐ በኋላ ለመዓስባን የሚደርሰውን ጸሎት አድርሳ ሥርዓተ ጋብቻን ትፈጽምላቸዋለች፡፡

የጋብቻ ክብር

ሥርዓተ ጋብቻ በቅድስት ቤተክርስቲያን

ቅዱስ ጳውሎስ የጋብቻን ክብር ሲገልጥ፡- ‹‹መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር መኝታውም ንጹሕ ይሁን›› ይላል ዕብ 13÷4፡፡ ሐዋርያው ‹‹መኝታው ንጹሕ ይሁን›› ማለቱ ከብረትና ከእንጨት ተሠርቶ ቅርጻ ቅርፅ ተቀርጾበት በአልጋ ልብስ አሸብርቆ የሚታየውን መኝታ ንጽሕና ሳይሆን የጋብቻ ሕይወትን ንጽሕና ነው፡፡ ንጹሕ የሆነ የጋብቻ ሕይወት፣ ንጹሕ ፍሬን ያፈራል፡፡ ‹‹መልካም ዛፍ መልካም ፍሬን ያፈራል›› ተብሎ እንደ ተነገረ፡፡ እመቤታችን ድንግል ማርያም የተገኘችበት፣መጥምቁ ዮሐንስ የተገኘበት ፣ነቢያት ሐዋሪያት አባቶቻችን የተገኙበት ጋብቻ ንጹሕ ነው፡፡ በዚህ ዓለም የጋብቻ ሕይወታቸውን አክብረው፣በፈቃደ እግዚአብሔር በምክረ ካህን የሚኖሩ ባልና ሚስት ዐረፍተ ዘመን ቢገታቸውም በትንሣኤ እንደ መላእክት በሰማይ በንጽሕና እግዚአብሔርን እያገለገሉ እንደሚኖሩ ተነግሯል፡፡ ማቴ 22÷32፡፡
እንግዲህ ‹‹ዘመነ መርዓዊ›› እስከ ኀልፈተ ሕይወት ከማንለየው የትዳር ጓደኛ ጋር አንድነታችንን የምናጸናበት በመሆኑ በዚህ ዓለም መልካም የጋብቻ መሠረት ጥለው ያለፉ የትዳር ሰዎችን እንዲሁም በጋብቻ ሕይወት ችግር ያጋጠማቸውን ባለ ታሪኮች ከተመለከትን በኋላ ለትዳር ሥምረት ዓምድ /ዘውግ/ የሆኑ ነጥቦችን እናቀርባለን፡፡
አንዳንዶች የትዳር ሕይወትን አስፈላጊነት ሲገልዩ ሌሎች የቅርብ ዘመዶቻችንና ወዳጆቻችን ከሰርግ በኋላ ይለዩናል፣ወላጆችም ቀድመው ሊያልፉ /ሊሞቱ/ ይችላሉ፣ ልጆችም አድገው የራሳቸውን ኑሮ ጀምረው ትተውን ይሄዳሉ፣ የትዳር ጓደኛ ግን ትቶ አይሄድም /ትታ አትሄድም/ ይላሉ፡፡ በርግጥ መልእክቱ ‹‹ሰው እናትና አባቱን ይተዋል ከሚስቱ ጋር ይተባበራል ማቴ 19÷3-6 በሚለው የእግዚአብሔር ቃል ቢደገፍም አንዳንድ ሰዎች ሲንዱት ይስተዋላል፡፡ ለዚህ ደግሞ የጻድቁ ኢዮብ ሚስት በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት አንዷ ናት፡፡ ኢዮብና ሚስቱ የጋራ ሀብታቸው እንደ ማለዳ ጤዛ ሳይረግፍ በመካከላቸው ቅራኔ አልነበረም፡፡ ከበጎቹ የሰቡትን አርደው ከወይኑም የጎመራውን ጨምቀው በጋራ ጠጥተዋል፡፡ዐይናቸውንም በዐይናቸው ተመልክተዋል፡፡
ነገር ግን ትላንት የነበራቸው ሀብት ዛሬ እንዳልነበረ ሆኗል፡፡ በዐይኖቻቸውም አይተው የማይጠግቧቸውን ለዐቅመ አዳምና ሔዋን የደረሱ ልጆቻቸውን እንደ ወጡ አልተመለሱም ሰባት ሺ በጎችም፣ ሦስት ሺ ግመሎች፣ አምስት መቶ ጥማድ በሬ፣ አምስት መቶ አንስት አህዮች፣ በተሰማሩበት መስክ ረግፈዋል፡፡ ኢዮብ መላ ሰውነቱ በቁስለ ሥጋ ተመቶ ገላውን በገል ስባሪ ሲፈትግ ሚስቱ ከጎኑ አልቆመችም፡፡ ‹‹አንተ በመግል ተውጠህ በትል ተከበህ ሌሊቱን ሁሉ ስትዛብር ታድራለህ እኔ ግን እየዞርኩ እቀላውጣለሁ›› ብላ ቀላውጣ ለመብላት አስታማሚና ጠያቂ ዘመድ በሌለበት ባዶ ቤት ትታው ሄዳለች፡፡ ኢዮ 1-2፡፡
ለምን? ቢባል ለስፍርና ለቁጥር የሚያታክተው የኢዮብ ሀብት መጥፋት የነበራትን ፍቅር አጥፍቶታል፡፡ ኢዮብ በማጣቱና በመታመሙ ለሕይወቷ እንደ ጠንቅ ቆጠረችው ለባሏ በችግሩ ቀን ከጎኑ መቆም ሲገባት አፈረችበት፡፡
ትዳር ለተመሠረተበት ዓላማ ባለትዳሮች ተገዢ መሆን አለባቸው፡፡ ጋብቻ ለመረዳዳት የሚለው ዓላማ በኢዮብ ሚስት ዘንድ ተዘንግቷል፡፡ ተጋቢዎች ትዳርን ወደው ፈቅደው የሚመሰርቱት በመሆኑ የሚደሰቱ ችግሮችን በጋራ ለመቋቋም ዝግጁ መሆን አለባቸው፡፡ ጌታችን ‹‹ባልና ሚስት አንድ ሥጋ ይሆናሉ›› እንዳለ ከጋብቻ በፊት ይህን ግንዛቤ መጨበጥ ግድ ይሆናል፡፡ ማቴ 19÷5፡፡
የቤተ ክርስቲያን የአገር የወደፊት ጥንካሬ የሚለካው በተቀደሰ ጋብቻ በሚገኙ ፍሬዎች ነው።ስለዚህ ለእግዚአብሔር ህግ የሚታዘዙ ልጆችን ለመውለድ ዛሬንና ነገን ያገናዘበ የትዳር ሕይወትን እግዚአብሔርን አጋዥ አደርጎ በቅዱስ ሥጋው በክቡር ደሙ መመሥረት ተገቢ ነው፡፡ የጋብቻ ሕይወት የፈተና ማዕበል ሳያማታው፣ ነፋስ ሳያዘመው፣ ጎርፍ ሳይሸረሽረው በጽኑ ዓለት ላይ ጸንቶ እንዲኖር መቻቻልን ግድ ይላል፡፡ በኢዮብና በሚስቱ መካከል ከሀብታቸው መጥፋት፣ ከልጆቻቸው ኅልፈትና ከኢዮብ ጤና ማጣት ወዲህ መቻቻል ጠፍቷል፡፡ በትዳራቸው የታየው የአንድ ወገን ጥንካሬ ብቻ ነው፡፡
ዓለማችን በሁሉም ጊዜና ቦታ ሙሉ ላትሆን ትችላለች፡፡ አንዳንድ ጊዜ ኢዮብ በፈተና ውስጥ እንዳለፈ ትዳራችን በፈተና ውስጥ ሊያልፍ ይችላል፡፡ የፈተናውን ማዕበልና ነፋስ ለመገሠጽ መደጋገፍ ያስፈልጋል፡፡ ሀብት ሲጠፋ፣ የጤና መታወክ ሲፈጠር ሚስቶች ወይም ባሎች ፊታቸውን የሚያዞሩት ለምን ይሆን? የኢዮብና የሚስቱ ታሪክ መልስ ይሆነናል፡፡ ነቢዩ ዳንኤል እግዚአብሔር የጠለቀውንና የተሰወረውን ይገልጣል በጨለማ ያለውን ያውቃል ፤ ይላል፡፡ዳን 2÷22፡፡ እግዚአብሔር በኢዮብና በሚስቱ መካከል የገለጠው ጥልቅ ምስጢር አለ፡፡ ይኸውም ሀብትን ተገን ያደረገ ጋብቻ ሀብቱ በሆነ አጋጣሚ ሲጠፋ ጋብቻው ፈራሽ መሆኑን ነው፡፡
የኢዮብ ሚስት ኢዮብን ሳይሆን ያገባችው ሀብቱን እንደነበር እግዚአብሔር አጋልጧታል፡፡ ኢዮብን ብታገባው ኖሮ ሲቸገር አብራው ትቸገር፣ ሲታመም አብራው ትታመም ነበር፡፡ ይህ ‹‹የሀብት ጋብቻ››ይፋ የሆነው የኢዮብን ጤና ማጣት ተከትሎ ነው፡፡ ኢዮብ ድህነት ባያገኘው ጤናውም ባይታወክ ሚስቱ ትታው አትሄድም ሀብቱን እንዳገባች ትኖር ነበር፡፡ በሁለቱ ጾታዎች ይህን መሰል ድክመት አለ፡፡ ካነሣነው ታሪክ አንጻር የኢዮብን ሚስት ስንፍና ተመለከትን እንጂ ወንዶችም በዚህ ዓይነት ስሕተት ይዘፈቃሉ፡፡
ቅድመ ትዳር መጠነኛ ጥሪት ማስፈለጉ አያከራክርም፡፡ ምንም ጥሪት ሳይቋጥሩ ‹‹ፍቅር ካለ›› ብለው ጋብቻን መመሥረት እግዚአብሔርን መፈታተን ነው፡፡ እዚህ ላይ ‹‹የፍቅርን ዋጋ›› ዘንግተን አለመሆኑ ሊጤን ይገባል፡፡ እግዚአብሔር ለገበሬ ያረሰውን ይባርክለታል እንጂ አያርስለትም፡፡ ለተማሪዎች አእምሮን ይሰጣል እንጂ አያጠናላቸውም፡፡ ለተጋቢዎችም ጋብቻን ይባርካል እንጂ ከሰማይ ገንዘብ አያዘንብም ከእኛ የልብ መዘጋጀት ካለ እግዚአብሔር ቀርቦ ያለንን ይባርክልናል፡፡ ኃላፊና ጠፊ የሆነውን ገንዘብ ተገን አድርገን የማኅበረሰብ የማዕዘን ደንጊያ ወደሆነው ትዳር ዘው ብሎ መግባት ውሎ አድሮ እንደ ኢዮብ ሚስት ሊያጋልጠን ይችላል፡፡ ስለዚህ እኛ ሳንጋባ ዛሬ ታይቶ ነገ የሚጠፋውን ሀብት ያገባን ወገኖች ከኢዮብና ከሚስቱ ብዙ ልንማር ይገባል፡፡
ዛሬም መሰል ስሕተቶችን እንመለከታለን፡፡ ቅድመ ጋብቻ ሀብትና ጤና  ተሟልተው በሠናይ የተጀመረው ሕይወት በቆይታ እንደ ኢዮብ ችግር ሲገጥመው፣ ውበቱ ሲሟሽሽ፣ ሞልቶ የነበረው ሲጎድል የምንጨካከን አለን፡፡ኢዮብን ያገኙት ችግሮች አግኝቶ ማጣት፣ መከዳዳት፣ መጨካከን፣ ጤና ማጣት ትዳራችንን ሲያጋጥሙ የመጀመሪያውን ትተን በምትኩ ሌላ ጓደኝነት፣ ሌላ ፍቅር፣ ሌላ ጋብቻ የምንፈልግ ወገኖች የሚሳካልን ይመስለናል እንጂ አይሳካልንም፡፡ እዚህ ላይ ሌላ ፍለጋ የተጓዘችው የኢዮብ ሚስት አፈረች እንጂ በትዳሩ የጸናው ጻድቁ ኢዮብ እንዳላፈረ ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ‹‹እግዚአብሔር ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛውን ለኢዮብ ባረከ፡፡›› እንዲል፡፡ ኢዮ 42÷12፡፡
ደገኛው ኢዮብ የሀብቱ መውደም፣ የጤናው መታወክ ሳይሰማው ቀርቶ አይደለም፡፡ ‹‹እግዚአብሔር ሰጠ እግዚአብሔር ነሳ፤ የእግዚአብሔር ስም የተባረከ ይሁን፡፡›› ብሏል፡፡ ኢዮብ 12÷2፡፡ ደገኛው ኢዮብ ዐስር ልጆቹ ተለዩት የዐሥር ልጆቹ ፈጣሪ እንደማይለየው ጽኑ እምነት ነበረው፡፡ በጎቹ ናቸው እንጂ ያለቁት በጎቹን የሰጠው አምላክ በጎደለው እንደሚሞላለት ያውቃል፡፡ ሚስቱ ብትከዳውም የሚስቱ ፈጣሪ እንደማይከዳው ተገንዝቧል፡፡ ጓደኞቹ ቢክዱትም ጓደኞቹን የፈጠረ ፈጣሪ እንደማይለየው ያውቅ ነበር፡፡ ስለዚህ በትዕግሥት ይህን ሁሉ ጠበቀ፡፡ በመጨረሻም ውጤቱንም ተመልክተናል፡፡ ‹‹እግዚአብሔር  ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛውን ለኢዮብ ባረከ፡፡›› ኢዮ 42÷12፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብም የኢዮብን የትዕግሥት ፍሬ አስመልክቶ እንዲህ በማለት ይመክረናል፡፡ ‹‹እነሆ በትዕግሥት የጸኑትን ብፁዓን እንላቸዋለን ኢዮብ እንደ ታገሠ ሰምታችኋል ጌታም እንደፈጸመለት አይታችኋል ጌታም እጅግ የሚምር የሚፈራም ነውና፡፡›› /ያዕ 5÷1/ ይለናል፡፡ በትዳር ሕይወት ፈተና ቢያጋጥመን ከእግዚአብሔር ጋር ከሆንን የማናልፈው የፈተና ወጥመድ እንደሌለ ልብ ልንል ይገባል፡፡
የተሳካ ጋብቻ
ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹ቤትና ባዕለ ጸግነት ከአባቶች ዘንድ ይወረሳሉ አስተዋይ ሚስት ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ናት፡፡›› ይላል ምሳ 19÷14፡፡ ደገኛው አብርሃም በሸመገለ ጊዜ ሎሌውን፡- ‹‹እጅህን ከጭኔ በታች አድርግ እኔም አብሬ ከምኖራቸው ከከነዓን ሴቶች ልጆች ለልጄ ሚስት እንዳትወስድለት በሰማይና በምድር አምላክ በእግዚአብሔር አምልሃለሁ፡፡ ነገር ግን ወደ አገሬና ወደ ተወላጆቼ ትሄዳለህ ለልጄ ለይስሐቅም ሚስትን ትወስድለታለህ፡፡›› /ዘፍ 24÷3/ ይለዋል፡፡ ሎሌውም የአብርሃምን እጅና ጉልበት ይመታል፡፡ አብርሃም እጄን ምታ ማለቱ፡- ‹‹የሰጠኸኝ አይባረክልኝ በል›› ሲያሰኘው ሲሆን ዳግመኛም ‹‹ጉልበቴን ምታ›› ማለቱ ‹‹የወለድኩት አይባረክልኝ በል›› ሲያሰኘው ነው፡፡ እርሱም ጠንቅቆ ይምላል፡፡
የእምነት አንድነት
እጅና ጉልበትን ጸፍቶ /መትቶ/ መማማል እጅግ አስፈሪ መሐላ ነው፡፡ የአብርሃም ሎሌ የማለውን መሐላ ቢያፈርስ አብርሃም የሰጠው ጥሪት እንደማይባረክለት ልጅም ቢወልድ እንደማይባረክለት ተማምለዋል፡፡ ይህ ሁሉ መሐላ ለምን አስፈለገ? ትልቁ ነገር ይስሐቅ አዋልደ ከነዓንን /የከነዓን ሴቶችን/ እንዳያገባ ነው፡፡
ከነዓን በአባቱ የተረገመ የካም ልጅ ነው፡፡ ከነዓናውያን ከዮርዳኖስ በስተምሥራቅ ይኖሩ የነበሩ ሕዝቦች ናቸው፡፡ ብዙ አማልክትን ያመልኩ ነበር፡፡ ከሁሉም የታወቀ ‹‹በኣል›› የተባለው ጣዖት ነው፡፡ ዘፍ 9÷18-27 ፤ኢያ 17÷13 ፤ እንግዲህ አብርሃም ሎሌውን ያስጠነቀቀው ከጣዖት አምላኪዎች ልጁን እንዳያጋባው ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ተካፋይነት አለውና?…. ከመካከላቸው ውጡና የተለያችሁ ሁኑ፤ ርኩስንም አትንኩ፡፡›› 2ኛ ቆሮ 6÷14-17፡፡ ሲል እንደ ተናገረው የአብርሃም ጥንቃቄ ሃይማኖትን ይመለከታል፡፡ በጋብቻ የሃይማኖት አንድነት መኖር ተገቢ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ‹‹የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ክፍል አለው?›› ተብሎ ተጽፏልና፡፡ ሌላው ‹‹ወደ ተወላጆቼ ሂድ›› ሲል ያስጠነቀቀው ‹‹ዘረኛ›› ሆኖ አይደለም፡፡ ከነዓናውያን ጣዖት አምላኪ ስለሆኑ ነው፡፡የሃይማኖት አንድነት የትዳር መሠረት ነው፡፡ዳግመኛ ‹‹የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም በሕያውና ለዘላለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ›› እንዲል፡፡ 1ኛ ጴጥ 1÷23-25፡፡ አንዳንድ ወገኖች ብኩርናውን ለምሥር ወጥ እንደ ለወጠ እንደ ዔሳው በሃይማኖት ሳይመሳሰሉ እምነታቸውን ለውጠው ትዳርን የሚመሠርቱ ወገኖች አሉ፡፡ አብርሃም ሎሌውን ያስማለውን መሐላ ማጤን ተገቢ ነው፡፡ ዔሳው እንደ ዋዛ ያጣውን ብኩርና ፡- ‹‹በእንባ ተግቶ ምንም ቢፈልገው ለንስሐ ሥፍራ አላገኘም፡፡›› ዕብ 12÷17፡፡ ብዙዎች የተሻለ ነገር ፍለጋ እንዲሁም በአጉል ወደድኩህ ወደድኩሽ ፈሊጥ ሃይማትን ያህል የሕይወት መሠረት ረግጠው ገንዘብ ያለው /ገንዘብ ያላት/ ከተገኘ /ከተገኘች/ ብለው የሚጀምሩት ሕይወት ለዘላለም ጸጸት ሊያጋልጥ ስለሚችል ቅድመ ትዳር የሃይማኖት አንድነት መኖር እንዳለበት ማጤን ያስፈልጋል፡፡
እግዚአብሔር የተጠራበት ጋብቻ /ትዳር/
ኢያውብር /የአብርሃም ሎሌ/ የጌታውን እጅና ጉልበት ከመታ በኋላ ስጋት ተሰማው፡፡ ‹‹ለይስሐቅ የማመጣት ብላቴና ወደ ነበርክበት አልመጣም ያለች እንደሆነ እርሱን ይዤ ልሂድ?›› ይለዋል፡፡ አብርሃምም ልጁን ከከነዓን ሴቶች እንዳያጋባው፡- ‹‹እግዚአብሔር መንገድህን ያቃናልሃል፤ አምጥተህ አጋባው አንጂ ልጄን አትውሰደው›› አለው፡፡ ያን ጊዜ ሎሌው በዐሥር ግመል ጭኖ የልጅቷን እናቷንና አባቷን ሰፈሯንም ወደማያውቅበት አገር እግዚብሔርን መሪ አድርጎ ጉዞውን ይጀምራል፡፡ ጀንበር ሳታዘቀዝቅ ከውኃ ዳር ተቀምጦ፡- ‹‹የጌታዬ የአብርሃም አምላክ ሆይ እለምንሃለሁ ውኃ ከሚቀዱት ሴቶች ከጌታዬ ከአብርሃም ወገን ኾና መልክ ከደም ግባት አስተባብራ የያዘች ብላቴና /ልጃገረድ/ ፤ውኃ እጠጣ ዘንድ እንስራሽን አዘንብዪ የምላት እርስዋም አንተም ጠጣ ግመሎችህን ደግሞ አጠጣለሁ የምትለኝ ቆንጆ እርሷን ለባሪያህ ለይስሐቅ ያዘጋጀሃት ትሁን›› ሲል ወደ እግዚአብሔር አመለከተ፡፡ ጸሎት ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር የሚያገናኝ ሕያው መስመር ነው፡፡ እግዚአብሔር የአብርሃም ሎሌ የሚፈልጋትን ልጅ ከነምልክቷ አስረከበው፡፡ እዲያውም፡- ‹‹ይህን መናገር ሳይፈጽም ወንድ የማታውቅ ድንግል የባቱኤል ልጅ ርብቃ በአጭር ታጥቃ ማድጋዋን ነጥቃ መጣች፡፡ እንስራዋን አውርዳ አጠጣችው ለግመሎቹም እስከሚረኩ ድረስ ቀድታ አጠጣችለት፡፡›› ይላል ዘፍ 24÷12-18፡፡
ጸሎት
ሐዋርያው ያዕቆብ፡- ‹‹የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች፡፡›› ይላል፡፡ ያዕ 5÷16 አብርሃም ሎሌውን ወደ ሜስጴጦምያ /ሶርያ/ ሲልከው መንገዱ ሁሉ እንዲቃናለት ይጸልይ ነበር፡፡ ብዙዎቻችን ለልጆች የጋብቻ ሕይወት መቃናት የአባትና እናት እንዲሁም የጓደኛ ጸሎት አስፈላጊ ነው፡፡ ለወላጆቻችን ለንስሐ አባቶቻችን ስለ እጮኛችን ግልጽ አንሆንም፡፡ የጋብቻችን ሰዓት እንኳ መቃረቡን የምንናገረው በመጨረሻ ሰዓት ነው፡፡ ከድብቅነታችን የተነሳ ራሳችንንና ሌሎችን እንጎዳበታለን፡፡ ቤተሰቦቻችንና መንፈሳዊ አባታችን በጸሎት እንዲያግዙን መንገዱን ዝግ ስለምናደርግ እንጎዳበታለን እንጂ አንጠቀምም፡፡ በጸሎት ሊረዱን የሚችሉ ወላጆቻችንን እንዲሁም መንፈሳዊ አባትም ማማከር ተገቢ መሆኑን ልንረዳ ይገባናል፡፡
የአብርሃም ሎሌ መንገዱ ሁሉ የተቃናለት አስቀድሞ በመጸለዩ ነው፡፡መልካም የትዳር ጓደኛ ለማግኘት እግዚአብሔርን መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ የጋብቻ ሕይወት ምድር ላይ መሠረቱ ቢጣልም ወደ ረቂቅ ጉዞ አምርቶ እንደ እግዚአብሔር መላእክት በሰማይ ልዩ ዝማሬ ወደሚያቀርቡበት ብቃት ይዘልቃል፡፡ ለዚህ የክብር ሕይወት ለመብቃት መጸለይ የሚያሳፍር ጉዳይ አይደለም፡፡ ስለዚህ እንደ አብርሃምና እንደ ሎሌው እንደ ይስሐቅ ለጋብቻ ሥምረትም ይሁን በሂደት ለሚያጋጥሙ ችግሮች መፍትሔ ለማግኘት መጸለይ ይኖርብናል፡፡
ርብቃ ለጋብቻ የተገኘችው በጸሎት ነው፡፡ ርብቃ በእናት አባቷ በወንድሞቿ ‹‹አንቺ እኅታችን እልፍ አእላፋት ሁኚ ዘርሽም የጠላቶችን ደጅ ይውረስ›› ዘፍ 24÷60፡፡ ብለው መርቀው ሸኝተዋታል፡፡ ይህ የእናት አባቷና የወንድሞቿ ምርቃት ርብቃን በሕይወት ዘመኗ ተከትሏታል፡፡ ‹‹ዘርሽ የጠላትን ምድር ይውረስ›› እንደተባለች እስራኤልን ከእርሷ አብራክ የተገኙ ዘሮቿ ምድረ ርስት ከነአንን ወርሰዋል፡፡ ፍጻሜው ገን በልጅነት የምንወርሳት መንግሥተ ሰማያትን የሚያመላክት ትንቢታዊ ቃል ነው፡፡ ከእርሷ የልጅ ልጅ የተወለደው መድኅነ ዓለም ክርስቶስ የጠላትን ግዛት በመስቀሉ አፍርሶ ከእርሱ ርቀን የነበርነውን ወደራሱ አቅርቦናል፡፡ መንግሥተ ሰማያትንም እንደሚያወርሰን ቃል ገብቶልናል፡፡ ዛሬ በካህናት አባቶች መባረክ፤ በእናት አባት አንደበት መመረቅ ምን ያህል በረከት እንደሚያስገኝ ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡
አንዳንድ ወጣቶች ‹‹አባቴና እናቴ ማግባቴን ባያውቁ ምን አለበት? ይላሉ፡፡ ነገር ግን ለመንፈሳዊ አባትና ለቤተሰብ ተናግረን ቤተሰብም እንደ ቤተሰብነቱ መንፈሳዊ አባትም እንደ ሃይማኖታችን ሥርዓት ጸልየውልን መሸኘት ለበረከት ያበቃናልና ችላ ልንለው አይገባም፡፡
የሣራ ድንኳን ዘወትር የሐዘን እንጉርጉሮ ይደመጥበት ነበር፡፡ ምክንያቱም የቤቱ እመቤት ሣራ ዐረፍተ ዘመን ወስኗታል፡፡ ይስሐቅም እናቱን ሞት በሚባል ባላጋራ ስለተነጠቀ ከድንኳኑ ውስጥ የተሰቀሉትን ልብሶቿንና ጌጣጌጦቿን እየተመለከተ ዘወትር ያነባ ነበር፡፡ ርብቃ ለይስሐቅ በዚህ ሰዓት ነበር የደረሰችለት፡፡ ‹‹ይስሐቅም ወደ እናቱ ወደ ሣራ ድንኳን አገባት ርብቃንም ወሰዳት፡፡ ሚስትም ሆነችው ወደዳትም ይስሐቅም ከእናቱ ሞት ተጽናና፡፡›› ይላል፡፡ ዘፍ 24÷27፡፡ ማንም ሰው እንደሚያውቀው የእናት ውለታ ታላቅ ነው፡፡ ይስሐቅ ርብቃን በማግኘቱ እያደር እንደ ድንጋይ ትራስ የሚቆረቁረውን የእናቱን ሞት ረስቶ ከሐዘኑ ተጽናንቷል፡፡ ጌታችን ‹‹ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ›› ያለው ስለዚህ ነው፡፡ ማቴ 19÷5፡፡ ርብቃ ይስሐቅን ከእናቱ ሞት ልታጽናናው ችላለች፡፡ ለምን? ቢባል ርብቃ በጸሎት ስለ ተገኘች ነው፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹ቤትና ባለጠግነት ከአባቶች ዘንድ ይወረሳሉ አስተዋይ ሚስት ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ናት፡፡›› ያለው ስለዚህ ነው፡፡ ምሳ 19÷14፡፡ የርብቃ አስተዋይነት የባሏን ሐዘን በማስረሳት ተመስክሯል፡፡ ሚስት መሆን ታላቅ ሓላፊነት ነው፡፡ ሚስትነት ከእግዚአብሔር የሚሆን ማስተዋልንና ጸጋን የሚጠይቅ ነው፡፡ ርብቃ በነበራት ጸጋ እግዚአብሔር ነው የባለቤቷን የይስሐቅን እያደር የሚቆረቁር የእናት ሐዘን ልታስረሳው የቻለችው፡፡ ዛሬም ይህን ጸጋ እግዚአብሔር ለማግኘትና በአግባቡ ለመጠቀም የሚስትን አስተዋይነት ይጠይቃል፡፡ ባል አዝኖ ቢመጣ፣ ቢጎሰቁል፣ባዘን ቢሆን ከጐን ሆኖ ማጽናናት ተገቢ እንደሆነ ከርብቃ ልንማረው የሚገባ ፀጋ ነው፡፡ የእርሷንም አስተዋይነት ገንዘብ ማድረግ በትዳራችን ሞገስ እንድናገኝ ያደርገናል፡፡
ፈተናን መቋቋም
ሥርዓተ ጋብቻ ከፈፀሙ በኃላ ልጅ አለመውለድ (አለማግኘት) ለተጋቢዎች ትልቅ ፈተና ነው፡፡ ለዚህም ወደ ኋላ ተመልሰን የራሔልን ሕይወት መመልከት ይገባል፡፡ ራሔል ልጅ መውለድ እየፈለገች መውለድ አልቻለችም ነበር፡፡ ያን ጊዜ ያዕቆብን ‹‹ልጅ ስጠኝ ይህስ ካልሆነ እሞታለሁ አለችው፡፡›› ይላል ዘፍ 30÷1፡፡ ተጋብቶ ልጅ አለመውለድ ምን ያህል ፈታኝ እንደሆነ ከዚህ መገንዘብ ይቻላል፡፡
ራሔል የማኅፀኗን ፍሬ በማጣትዋ ሞትን ተመኝታለች፡፡ ርብቃና ይስሐቅ ተጋብተው ሃያ ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ ልጅ አልወለዱም፡፡ ይህ ሁኔታ የርብቃን ሥነ ልቡና በጥቂት መጉዳቱ አይቀርም፡፡ ይስሐቅ በእናት ሞት ሐዘን ሲንገላታ ርብቃ ከጐኑ ሆና እንዳጽናናችው ዛሬ እርሱም በተራው ሚስቱ ልጅ ባለመውለዷ ስትፈተን ስለ ሚስቱ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፡፡ መካን ነበረችና እግዚአብሔር ተለመነውና ሚስቱ ፀነሰች፡፡ ዘፍ 25÷21፡፡
በትዳር ውስጥ ለሚፈጠር ፈተና ጸሎት ምን ያህል ኃይል እንዳለው መገንዘብ ተገቢ ነው።ዛሬ ተጋብተን ልጅ በማጣታችንም ሆነ በሌሎች ምክንያቶች ብንፈተን ባሎች ለሚስቶቻችን ብንጸልይ ለርብቃና ለይስሐቅ መፍትሔ የሰጠ አምላክ መፍትሔ ሊሰጠን እንደሚችል ከሁለቱ የትዳር ሕይወት እንማራለን፡፡ እንዲህ ሲባል ሚስት ለባል መጸለይ አይገባትም ማለት አይደለም፡፡ ርብቃ ባለመውለዷ ይስሐቅ ጠንቋይን አላማከረም፡፡ ያማከረው እግዚአብሔርን ነው፡፡ እግዚአብሔር የተዘጋውን ይከፍታል፡፡ ስንታበይ ደግሞ የተከፈተውን ይዘጋል፡፡
ንጽሕና
ድንግልና ለሴቷም ይሁን ለወንዱ የመታመን መገለጫ ነው፡፡ ለዚህ የመታመን መገለጫ መጥፋት ብዙ እስራኤላውያን ወጣቶች ማቅ ለብሰው አመድ ነስንሰው አንብተዋል፡፡ ትዕማር አላግባብ ለጠፋ ድንግልናዋ አመድ ነስንሳ በአደባባይ አልቅሳለታለች፡፡ የዮፍታሔ ልጅ ለተከበረ ድንግልናዋ ከጓደኛዋ ጋር ሁለት ወር አልቅሳለች፡፡ መሳፍንት 16÷37-40፡፡2ኛ ሳሙ 13÷19፡፡
ርብቃ ወንድ የማታውቅ ድንግል ነበረች፡፡ ዘፍ 24÷16፡፡ ድንግልና የእውነተኛ ትዳር ትክክለኛ መንገድ ነው፡፡ ለትዳራችን ሥምረት ማረጋገጫ ማዕበል ሳይመታው ጎርፍ ሳይጎርፍበት ነፋስ ሳያዘመው ፀንቶ እንዲዘልቅ ድንግልና ሥነ ልቡናዊ ዋጋ አለው፡፡ የጋብቻ ጨዋነት መንፈሳዊ ጥንካሬ ከፍ የሚለው የትዳር ባልደረቦች በሚኖራቸው የቅድመ ጋብቻ ድንግልና ነው፡፡ በጋራ ወስነው በድንግልናቸው አሐዱ ብለው የጀመሩትን ሕይወት በቅድስና አብረው ስለሚካፈሉት ጋብቻቸው ስኬታማ የመሆኑ ዕድል ከፍ ያለ ነው፡፡
አንዳንዶች ይህን የተከበረ ንጽሕናቸውን አላግባቡ ያጠፉታል፡፡ ለትዳር ትልቁ ነገር መተማመን ነው፡፡ ያለድንግልና የተመሰረተ ጋብቻ አለመተማመን እንዲፈጠር በተወሰነ መልኩ ክፍተት ይፈጥራል፡፡ ስለዚህ መተማመን የሰፈነበት የትዳር ሕይወት ለመምራት የሁለቱም ወገን ድንግልና አስፈላጊ ነው፡፡
በእርግጥ ከዚህ ጋር በተያያዘ ‹‹ጉዳይህ ከደም ጋር ከሆነ ዶሮ እረድ ጣት ቁረጥ›› ሌላም የሚሉ ዘመነኞች አይታጡም፡፡ እነዚህ ወገኖች በአጭሩ የድንግልናን ምንነት ያልተረዱ ናቸው፡፡ በሴት እኅቶቻችን ድንግልናቸውን በተፈጥሮና በሥራ ብዛት እንዲሁም ተገድዶ በመደፈር ንጽሕናዋን ልታጣ ትችላለች፡፡ ይህ እንግዲህ በተወሰነ ደረጃ ንጽሕናን እንዳያጎድፍ በግልጽና በአግባቡ ለጓደኛ ማስረዳት ዓይነተኛ መፍትሔ ነው፡፡ ሌላው ንስሐ ዘማዊን ድንግል ስለሚያደርግ ንስሐ ገብቶ መጋባት አንድ የሕይወት አቅጣጫ ስለሆነ ድኅረ ንስሐ ተማምሎ በመጋባት አዲስ ሕይወት ለመምራት ይቻላል፡፡
ከማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ የተገኘ 
/ምንጭ ሐመር 1997 ዓ.ም /
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

No comments:

Post a Comment