Monday, February 6, 2012

ጾመ ነነዌ

ዲ.ዮናታን ጌታቸው
ነነዌ  ከሰባቱ ዐበይት አጽዋማት መካከል አንዱ ነው። ከ አጽዋማቱ መካከል አንዱም ብቻ ሳይሆን ለዓቢይ ጾም ማዘጋጃም ነው።

እንኳን ለጾመ ነነዌ አደረሰዎት
 ነነዌ በጥንት ጊዜ የነበረች   በጤግሮስ ወንዝ ዳር በናምሩድ የተመሰረተች ከተማ ናት:: ዘፍ 10፥11-12 የከተማው ቅጥር ርዝመት ዐሥራ ሁለት ኪ.ሜ ያህል ነው:: ሰናክሬም በወስጧ ብዙ ሕንጻዎችን ሠርቷል:: ኋላም በባቢሎን መንግሥት ፈርሳለች፡፡

እግዚአብሔር ነብዩ ዮናስን ወደ ነነዌ ምድር በኃጢአታቸው ምክንያት ሊያመጣው ካሰበው የእሳት ዝናም እንዲትርፉ ቢልከው የ እግዚአብሔርን ቸርነት ስለሚያውቀው ቸ ርነትህ ከልክላህ ሳታጠፋቸው ብትቀር እኔ የሐሰት ነቢይ እባል የለምን? ብሎ ሰግቶ ወደ ተርሴስ  ሃገር  ከነጋዴዎች ጋር ተሳፈረ። እግዚአብሔርም ታላቅ ማዕበልን አስነሳ በመርከቧ ያሉ ሰዎችም እርስ በራሳቸው ዕጣን ተጣጥለው በዮናስ ላይ ወደቀ። እርሱም ያደረገውን ሰለሚያውቅ ሌሎቹ በውሰጥ ያሉት እንዳይጣልብዙ ጥረት ቢያደርጉም የግድ መጣል ስለ ነበረበት ወደ ባሕር ተጣለ።  እግዚአብሔርም ታላቅ ዓሣ አንበሪን አዘጋጅቶ በከርሠ ዓሣ አንበሪ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት ቆይቶ  በሦስተኛው ቀን  በአንጻረ  ነነዌ  ተፍቶታል። በግድም ቢሆን ስለ ሚመጣባቸው መዓት አስተምሯል። ትንቢተ ዮናስ ምዕራፍ 1 እና 2። ነብዩ  ዮናስ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ አሕዛብ ሀገር የተላከ ነቢይ ነው።

ዮናስ ማለት ርግብ ማለት ነው። አባቱ አማቴ ሲባል እናቱ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ የሰራፕታዋ ሴት በመባል ትታወቃለች። 1ኛ ነገ 17፥10 ርግብ የዋህ እንደሆነች እሱም የዋህ ነውና ይህ ቅጽል ተቀጽሎለታል። የርግብ የዋህነት እንደምን ነው ቢሉ በማየ አይኅ (በጥፋት ውሃ )ጊዜ በእባብ አፍ ውስጥ እንቁላል ጥላለች። ጌታም በወንጌል “ኲኑ የዋኃን ከመ ርግብ” እንድ ርግብ የዋኃን ሁኑ ብሎ ተናግሯል።   ማቴ 10፥16 ዮናስም እግዚአብሔር  የሰማይ እና  የምድር የቀላያት እና የአብርሕት ፈጣሪ መሆኑን እያወቀ እያስተማረ ከእርሱ ዓይን እይታ  ለመራቅ እግዚአብሔር በፈጠረው ባሕር ላይ በመርከብ ተሳፍሮ  ሊሸሽ መሞከሩ በራሱ የዋህ ያስብለዋል። በተጨማሪም አብረውት የነበሩ ነጋድያን ከየት ወገን እና ከየት እንደመጣ ሲጠይቁት የሚመልሰው መልስ በራሱ የዋህነቱን  ያሳያል የመጀመርያው “ዕብራዊ ነኝ” ሲል መልሷል ዕብራዊ መሆን ሃይማኖት አዋቂ እና ሃይማኖተኛ  መሆንን ያሳያል። ሁለተኛው ደግሞ  “ባሕሩን እና የብሱን የፈጠረን አመልካለሁ” ብሎ ከ ባህር ፈጣሪ ዐይን እይታ ለመራቅ ወደ ተርሴስ ለመሄድ መሞከሩ  በእርግጥም የዋህ የሚያሰኘው ነው።
ሌላው ደግሞ ዮናስን ያስጨንቀው የነበረው የራሱ ቃል (ትንቢት) ተፈጻሚነት አለማግኘቱ እንጂ የነነዌ ሰዎች በእነርሱ ላይ ሊደርስ ከነበረው መዓት መዳን አለመዳናቸው  አልነበረም። የሚያስደንቀው ደግሞ በእግዚአብሔር ቸርነት የእርሱ ቃል (ትንቢት) ተፈጻሚነት እንደ ማይኖረው አውቆ ወደ ተላከበት ላለመሄድ አጥብቆ  መጠየቁ ነው። ዮና 4፥2 የእግዚአብሔር ነቢይ ለራሱ ቃል ተጨንቆ እንዲህ ያለ የተማጽኖ  ቃል ቢያሰማ በእርግጥም ከየዋህነት እንጂ ሳያውቅ ቀርቶ አደለም።”አቤቱ እለምንሃለሁ በሀገሬ ሳለሁ የተናገርኩት ይህ አልነበረም? አንተ   ይቅር ባይ ታጋሽ ምሕረትህም የበዛ ከክፉው ነገር የምተጸጸት አምላክ እንደሆንክ አውቄ ነበርና᎐᎐᎐” ብሎ የእግዚአብሔር ቸርነት ማድረግ አሳዝኖት፣ የርሱ ታማኝነት የሚያሳጣ መስሎት አዘነ። ልብ እንበል ያልነው ያዘነው ሰብአ ነነዌ በመዳናቸው ሳይሆን የእርሱ ቃል በእግዚአብሔር መሸፈኑ ነው። ነገር ግን ይህ በራሱ የዮናስን የዋህነት ያሳያል ይኸውም ሰብዓ ነነዌ ገና የርሱን ቃል ሰምተው እንደዚያ ያለ ለውጥ ማምጣታቸው በራሱ የእርሱን ታማኝነት ያሳያል። ምክያቱም ገና አንድ ዐረፍተ  ነገር ተናግሮ እንዲያ ለመዳን መንቀሳቀሳቸው የቱን ያህል ቃሉን እነዳመኑትና እንደተቀበሉት  ያሳያል! ይህንንም አለማስተዋሉ የዋህነቱን ይመሰክራል።
እግዚአብሔርም የዋህነቱን ስለሚያውቅ ሲያባብለው እና በተለያየ ሁኔታ  እና ምሳሌ ሲያስተመረው እናያለን። “ በውኑ ትቆጣ ዘንድ ይገባሃልን” እያለ ይናገረው ነበር ዮና 4፥9 እሰከ መጨረሻ። በእውነት በፍጹም ክፋት አስቦት ቢሆን  ኖሮ ሲጀመር እግዚአብሔርም እንዲያስተምርለት አያዘውም ነበር። “᎐᎐᎐ በዓይኑ ትዕቢተኛ የሆነውን እና ልቡ የሚሳሳው ከእኔ ጋር አይተባበርም” እንዲል          መዝ 100፥ 5
ሌላው የነነዌ  ሰዎች በንስሓ  ሕይወት በመለወጥ እንደምሳሌ የሚጠቀሱ ናቸው። ይኸውም ገና በከተማዋ ገብቶ “በሦስት ቀን ወስጥ ትገለበጣለች” ስላለ ብቻ ሀገሩም አመነው አዋጅን አውጀው ፍጹም ጾምን ጾሙ፤ የእግዚአብሔርን መዓት በምሕረት መልሰዋል። የነነዌ ሰዎች ነቢዩ ዮናስ ገና “ ትገለበጣለች “ ስላለ ብቻ ሀገሬው ሙሉ ከንጉሥ እስከ ገረድ ከልኂቅ እስከ ደቂቅ ሆነው ለለውጥ መነሳታቸው በራሱ ሙሉ በሙሉ የንስሓ  ሕይወታቸውን የሚያረጋግጥ ነው። በ አሁኑ ጊዜ መምህራን ሁሉ ትምህርተ ሃይማኖትን እያስተማሩ የንስሓ ሕይወትን እየሰበኩ ለውጡ ግን የትምህርቱን ያህል አለመሆኑ የሰሚውን ጉድለትና ደካማነት ያሳያል  “᎐᎐᎐ዳሩ ግን የሰሙት ቃል ከሰሚዎቹ ጋር በእምነት ስላልተዋሓደ አልጠቀማቸውም”ዕብ 4፥2 እንዲል። ልብ እንበል! ነቢዩ ዮናስ ለሰብአ ነነዌ የተናገረው  “ በሦስት ቀን ውስጥ ነነዌ ትገለበጣለች” የሚል አምስት ቃልን ብቻ  ነው ። በዚህች ቃል ብቻ ይህን የመሰለ ለውጥ ማምጣት መቻል በራሱ ፍጹም የእግዚአብሔርን ሥራ እንድናደንቅ ይረዳናል። ስለ ነነዌ ሰዎች የንስሓ ሕይወት ጌታ ራሱ በወንጌሉ መስክሯል። ለሕዝቡም መፈራረጃ  አድርጓቸዋል። ሉቃ 19፥32 “᎐᎐᎐በዮናስ ስብከት ንስሓ ገብተዋልና” እንዲል። በተጨማሪም  የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ይፈርዱበታ ይላል ማቴ 12፥41
ሌላው እግዚአብሔር መቼም ቢሆን ሰው የተመኘውን አያስቀርም። አዳም አምላክነትን ተመኘ ዘመኑ ሲፈጸም አምላክ ሰው  ሆኖ ተምኔቱን (ምኞቱን) ፈጽሞለታል። ዮናስም ምንም እንኳን በቀጥታ እንዲጠፉ ባይፈልግም ውሸታም እንዳይባል ስለሚፈልግ ቀድሞ በተናገረው ቃል መሠረት ትንቢቱ ተፈጽሟል። በ ናሆም ስንክሳር ላይ “ወበልዓ አሐደ ኅብረ” ይላል ንስሓ ያልገቡትን አንድ ሀገር ያሉትን አጥፍቷል። ሌላው ዮናስ በሦስት ቀን ውስጥ እንዳለ በሦስተኛው ትውልድ ተወግታ  ጠፍታለች።
የመጨረሻው ዮናስ ለክርስቶስ  ምሳሌው ሆኗል። ይኽውም በሉቃ 11፥30 “ ዮናስ ለነነዌ  ሰዎች  ምልክት እንደሆናቸው እንዲሁ ደግሞ የሰው ልጅ ለዚህ ትውልድ ምልክት ይሆናል” እንዲል። በጌታ ሞትም ምሳሌውሆኗል “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይሻል ከነቢዩ ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም ዮናስ በዓሣ አንበሪ ሆድ ሦስት ቀን እና ሦስት ሌሊት እንደ ነበር እንዲሁ የ ሰው ልጅ በምድር ልብ ውስጥ ሦስት ቀን እና ሦስት ሌሊት ይኖራል” እንዲል ማቴ 12፥39።
 ሰለዚህ እንዲህ ያሉተን ነገር እያሰቡ የነነዌን ሀገር ሰዎች ተግባር ማየት ከእነርሱም መማር ያስፈልጋል ። ጌታ እግዚአብሔር ዕድሜ ለንስሐ ይስጠን ይቆየን!!
ከባሕራን ድረ ገጽ የተገኘ

No comments:

Post a Comment