Friday, January 6, 2012

እንኳን ለጌታችን ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት በሰላም አደረሳችሁ!


“እነሆ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኅን ተወልዶላችኋል” (ሉቃ.2፡11) አትም ኢሜይል

ታኅሣሥ 27/2004 ዓ.ም
በዲ/ን በረከት አዝመራው እና በዲ/ን አሉላ መብራቱ

“ዘሎቱ ሰብአ ሰገል ሰገዱ ሎቱ፤ አማን መንክር ስብሐተ ልደቱ፤
ለእርሱ ሰብአ ሰገል የሰገዱለት፣ የልደቱ ክብር ድንቅ ነው።”

እግዚአብሔርን በእምነት ደስ ያሰኙ ቅዱሳን ከእስራኤላውያን ተነሥተው ነበር።(ዕብ.11) የአባቶች አለቃ ከሆነው ከአብርሃም ጀምሮ እስከ ጌታችን ሰው መሆን (ዘመነ ሥጋዌ) ድረስ ብዙ ታላላቅ አባቶችና እናቶች በእስራኤል ዘንድ ተገኝተዋል።

christmasየእስራኤል ታሪክ ሁልጊዜ መልካም ታሪክ ብቻ ግን አይደለም፤ እግዚአብሔርን ያሳዘኑባቸው ጊዜያት ጥቂቶች አይደሉም። በዚህ ጊዜ በዙሪያቸው ባሉ ነገሥታት እየተማረኩ ወደ ፋርስ፣ ባቢሎንና ግብጽ እየወረዱ ለአሕዛብ የተገዙበትና የገበሩበት ጊዜም ነበር። ንስሐ ገብተው ወደ እግዚአብሔር ሲመለሱ ደግሞ እግዚአብሔር ከእነርሱ መካከል ሰው እያስነሣ ያድናቸው ነበር። ለአባቶቻቸው የገባውን የዘለዓለም ቃልኪዳን እያሰበ ይረዳቸውም ነበር። (መዝ.77 (78))
እነሆ በዚህ የታሪክ መስመር ውስጥ ወደር የሌለው፣ ሁለተኛ በዓለም ታሪክ የማይደገም ታላቅ ነገር ተከሰተ። የእግዚአብሔር ልጅ የሰውን ሥጋ ለብሶ እንደ ሰው በምድር ላይ ተገለጠ። ጥበበኛው ሰሎሞን “አበባ በምድራችን ታየ” ብሎ የተናገረው ትንቢት ተፈጸመ፤ አበባ ክርስቶስ ምድር በተባለ ሥጋችን ተገልጧልና(መኃ.2፥12)። የዓለም መድኃኒት እግዚአብሔርነቱን ሳይተው ሰው ሆነ። እነሆ የእግዚአብሔር ልጅ የአብርሃም ልጅ ተባለ፤ የዳዊት ጌታ የዳዊት ልጅ ተባለ። (ማቴ.1፥1) የዳዊት ፈጣሪ በዳዊት ከተማ በቤተልሔም በከብቶች በረት ተወለደ። አባቶቻቸው በአንድ ዘመን ዳዊት የነገሠባትን ከተማ ያፈረሱ፣ የዳዊትን ልጆች በባርነት የገዙ የፋርስና የአረብ ነገሥታት የዳዊትን መንግሥት ለዘለዓለም ለሚያጸናው ሕፃን ለኢየሱስ ክርስቶስ ሰገዱ፤ ተገዙ።

ልጁን ለእግዚአብሔር መስዋዕት አድርጎ ለማቅረብ እንኳ እንቢ ያላለውን፣ የአብርሃምን ልጆች ያስገበሩት የአሕዛብ ነገሥታት ዛሬ ለአብርሃም ልጅ ወርቅ፣ እጣን፣ ከርቤ ገበሩ። (ማቴ.1፥11) በበደለኞች እስራኤላውያን ልጆቻቸው ኃጢአት ምክንያት ዝቅ ዝቅ ያለው የእስራኤል ክብር ከእነርሱ ዘር ሥጋን በነሣው በኢየሱስ ክርስቶስ ለዘላለም ከፍ ከፍ አለ።

የክርስቶስ ሰው መሆን ግን ከእስራኤል ታሪክ ያለፈ የሰው ልጅ ሁሉ ደስታ ነው። እነሆ ሰው የመሆኑ ዜና የሰው ልጆችን ሁሉ ደስታ አሰኘ “እነሆ ለህዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና።” የሚል ዜና በሰማያውያን መላእክት ተሰበከ። (ለቃ.2፥11) የምድር ኃያላን ነገሥታት በከብቶች በረት ውስጥ በጨርቅ ተጠቅልሎ ለተኛው ሕፃን መብዐ አቀረቡ። ንጹሐንና ኃያላን የሚሆኑ የሰማይ መላእክት እግዚአብሔር ለሰው ፍቅር ሲል እንደ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግም ተኝቶ ሲያዩ በታላቅ ትሕትና ከእረኞች ጋር ዘመሩ። (ሉቃ.2፥13)

“ብርሃንህንና እውነትህን ላክ፤ እነርሱ ይምሩኝ፣ ወደ ቅድስናህ ተራራና ወደ ማደሪያህ ይውሰዱኝ።” ያለው የዳዊት ጸሎት መልስ አገኘ (መዝ. 42፥3)። ማንም ሊቀርበው በማይችል ዘለዓለማዊ ብርሃን ዉስጥ ከአባቱ እና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የሚኖር ብርሃን ወልድ ለጨለማው ዓለም ብርሃን ይሆን ዘንድ ተወለደ። ወደ ጽድቅ ፀሐይ ያደርሳቸው ዘንድ የእርሱ የሆነው ኮከብ ሰብአ ሰገልን ከምሥራቅ መራቸው። እነሆ ለዘለዓለም የሚያበራው ፀሐይ በቤተ ልሔም ወጣ። ነቢዩ ኢሳይያስ “በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርሃን አየ በሞት ጥላ አገርም ለኖሩ ብርሃን ወጣላቸው” ብሎ የተናገረው ትንቢት ተፈጸመ (ኢሳ.9፥2)። እርሱ የቅድስናው ተራራና ማደሪያው ወደ ሆነች ወደ መንግሥተ ሰማያት ይወስደናል፤ በዚች የዘለዓለም አገራችንም የሚያበራልን ፀሐይ እርሱ ነው(ራእይ.21፥23)።

በዳዊት ከተማ በቤተልሔም ድንቅ ነገር ተደረገ። ዳዊት በወርቅ ያጌጠ የተልባ እግር መጎናጸፊያ የለበሰባት ቤተልሔም የሰማይና የምድር ፈጣሪ በጨርቅ ተጠቅልሎ ተገኘባት። ቤተልሔም ከዳዊት ዘመን አብልጣ ከበረች፤ የእግዚአብሔር ክብር አብርቶባታልና፤ የልዑላን መላእክት ዝማሬ ተሰምቶባታልና።(ሚክ.5፥2)

Picture2“የእሥራኤል እረኛ ሆይ አድምጥ …በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ ተገለጥ” ብሎ የለመነው የዳዊት ልመና በእውነት ተፈጸመ።(መዝ.70(71)፥1) የእስራኤል እረኛ በእረኞች መካከል በከብቶች በረት ተወለደ። (ሉቃ.2፥7)እረኞች ለእረኛቸው ዘመሩ፤ ላሞችና በጎች በበረት የተኛውን ሕፃን በትንፋሻቸው አሟሟቁት። በኦሪት ድንኳን በሙሴ ሕግ መሠረት ለመስዋዕት ይቀርቡ የነበሩ እንስሳት በልደቱ ደስ ተሰኙ፤ የእነርሱን መሥዋዕት የሚያስቀር አማናዊው የእግዚአብሔር በግ ተወልዷልና።

ለሰው ሁሉ ብርሃን የሚሰጥ እግዚአብሔር በጨለማው ዓለማችን ተወለደ።(ዮሐ.1፥9-14) ነቢያትና መምህራን ጠፍተውባት፣ የኃጢአት ጨለማ ዉጧት፣ በድንቁርና ባሕር ውስጥ ሰጥማ በነበረችው የሰው ልጆች ዓለም የእውነት ፀሐይ ወጣ። እነሆ ይህን ይገልጥ ዘንድ መድኅን በእኩለ ሌሊት ተወለደ፤ በተወለደ ጊዜ ግን የእግዚአብሔር ክብር በዙርያው አበራ። (ሉቃ.2፥8-9)

ለመንግሥቱ ወርቅ ተገበረለት። ኃያል መንግሥቱን ግን በምድር ላይ በትሕትና ገለጠው፤ በከብቶች በረት በመወለድና በአህያ ውርንጭላ ተቀምጦ በመሄድ።Picture1 (ሉቃ.19፥28-38) የአባታችን የዳዊት መንግሥት ያለልክ ከፍ ከፍ አለች፤ እግዚአብሔር ሰው ሆኖ የዳዊት ልጅ ሆኗልና። ቅዱስ ገብርኤል ቅድስት ድንግል ማርያምን ባበሠራት ጊዜ “እርሱ ታላቅ ይሆናል፣ የልዑል ልጅም ይባላል፤ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፣ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘለዓለም ይነግሣል፣ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለዉም” ብሎ የተናገረው ዛሬ ተፈጸመ(ሉቃ.1፥32) በባሕርይው የፍጥረት ሁሉ ገዥ የሆነው የእግዚአብሔር ልጅ ከዳዊት ልጅ ሥጋን ነሥቶ ሰው በሆነ ጊዜ የአባቱን የዳዊትን ዙፋን እስከ ጽርአ አርያም ድረስ ከፍ ከፍ አደረጋት። እነሆ ንጉሥ ክርስቶስ በያዕቆብ ቤት(በምዕመናን) ላይ ለዘለዓለም ነገሠ። ለመንግሥቱ የአሕዛብ  ነገሥታት ተገዙላት፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ናትና ፍጥረታት ሁሉ ይገዙላታል።(ኤር.23፥5)

ለክህነቱ እጣን ተሰጠው። ክህነቱም የአበውን እና የሌዋውያንን ክህነት የምትፈጽም የዘለዓለም ሰማያዊት ሥራው ናት። እነሆ የአብ ሊቀ ካህናት እርሱ የሰውን ባሕርይ ከራሱ ጋር አስማማ። ራሱ ካህን፣ ራሱ መስዋዕት፣ ራሱ ተቀባይ ሆኖ የፈጸማት የክህነት ሥራው የዘለዓለም ድኅነትን አስገኘች።

ለሞቱ ከርቤ ቀረበለት። እነሆ እግዚአብሔር ሰው የሆነበት ዋናው ምክንያት በሞቱ ሞትን ድል ለመንሣት ነውና በልደቱ ሞቱ ተሰበከ። ከርቤ ለሞቱ ሲቀርብለት የማይሞተው እርሱ ለሰው ልጆች ሲል የሚሞት ሥጋን እንደለበሰ ታወቀ።

የአሕዛብ ነገሥታት ወርቅ ገበሩለት፤ ምእመናን ደግሞ ጽሩይ፣ ንጹሕ፣ ሰማያዊ የሆነ ልቦናን እና እምነትን ለእርሱ እናቀርባለን። (1ኛ ጴጥ.1፥6) ሰብዐ ሰገል እርሱ የፈጠረውን ወርቅ ገበሩለት፤ እኛም በርሱ ጸጋና ሥራ ያገኘነውን ንጹሕና ሰማያዊ እምነታችንን እናቀርብለታለን።(ይሁ.3)

ነገሥታቱ ዕጣን ገበሩለት፤ ምእመናን ደግሞ ቂም በቀል የሌለበትን፣ ከመልካም እና ንጹሕ ልብ የሚወጣ የምስጋና ጸሎት እናቀርባለን፤ “ጸሎቴን በፊትህ እንደ ዕጣን ተቀበልልኝ፥ እጅ መንሣቴንም እንደ ሠርክ መስዋዕት ትሁን።” እንዳለ ንጉሥ ዳዊት።(መዝ.140፥2)

ስለሰው ልጆች ፍቅር ሲል ለሚቀበለው ሞት ከርቤ ገበሩለት፤ ምእመናን ደግሞ ለእግዚአብሔርና ለሰው ልጆች ያለንን ፍቅር ለእርሱ እናቀርባለን። ነገሥታቱ እርሱ ከፈጠረው ከርቤ ወስደው እጅ መንሻ አቀረቡ፤ ምእመናን ደግሞ ከእርሱ ከተማርነው፣ ከመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ከተቀበልነው ፍቅር መልሰን ለእርሱ እናቀርባለን። “እርሱ ስለኛ ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቷልና በዚህ ፍቅርን አውቀናል፤ እኛም ስለ ወንድሞቻችን ነፍሳችንን አሳልፈን ልንሰጥ ይገባናል(1ኛ ዮሐ.3፥16)።”
ስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክብር አሜን!!

ከማኅበረ ድረ ገጽ የተወሰደ።

No comments:

Post a Comment