በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
የዚህ ትምህርት መሠረታዊ ዓላማ ክርስቲያኖች ከጌታችንና ከእመቤታችን ስደት በረከት ተሳታፊዎች እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡
ቀዳማዊ አዳም የማይበላ በልቶ በራሱና በልጆቹ የሞት ሞት ተፈረደበት፤ ጸጋ እግዚአብሔር ጎደለበት፤ የሚሠዋው መሥዋዕት የሚጸልየው ጸሎት ግዳጅ የማይፈጽም ሆነበት፡፡ ምድር ከእርሱ የተነሣ እሾክና አሜከላ አበቀለችበት፡፡
ሆኖም (አዳም) ምንም ባልበደለው ሰይጣን እንዲሁ ቢሞትም የተበደለው አምላኩ ግን እንዲሁ ሕይወትን ይሰጠው ዘንድ ወደደ፡፡ (አዳም) አምላክ መሆንን ሽቶ ነበርና ይህን ይሰጠው ዘንድ (አምላክ) ዳግማይ አዳም ይሆንለት ዘንድ ወደደ፤ አስቀድሞ ከነበረው ክብር በላይ ሌላ ክብር ይጨምርለት ዘንድ ፈቀደ፡፡ ጊዜው ሲደርስም አካላዊ ቃል ንጹሕ የሆነ ባሕርዩን (የእመቤታችን ሥጋና ነፍስ) ነሥቶ ዝቅ ያለውን ከፍ ያደርገው ዘንድ ዝቅ አለለት፤ የጸጋ ልብሱን ይመልስለት ዘንድ የማይዳሰስ እርሱ በጨርቅ ተጠቀለለት፤ ወደ ክብሩ ይመልሰው ዘንድ በርካሽ ቦታ ያውም በግርግም ተወለደለት፡፡
ሰብአ ሰገል ይህን ግሩም ምሥጢር አውቀው በኮከብ እየተመሩ ከሩቅ ሀገር ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፤ መጥተውም “የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው?” ብለው ጠየቁ፡፡ በዚህ ጊዜም ንጉሡ ሄሮድስ ደነገጠ፡፡ አይሁዳዊ ሳይሆን ኤዶማዊ ነበርና “የአይሁድ ንጉሥ መጣ ማለት ንግሥናዬ ተነጠቀ ማለት አይደለምን?” ብሎ ተሸበረ፡፡ ከዚህ በኋላ አይሁድን ሰበሰበና ንጉሡ ከወዴት እንደሚወለድ አጠያየቀ፡፡ ጸሐፍትና ካህናትም ከነቢያት ጠቅሰው የሚወለድበትን ቦታ ነገሩት፡፡ ከዚህ በኋላ ሄሮድስ አንድ ተንኮል አሰበ፡፡ ሰብአ ሰገልን በስውር መጥራት፤ ከዚያም ስለ ሕፃኑ በጥንቃቄ እንደሚመረምሩና ተመልሰውም እንዲነግሩት፡፡ እንዲህ ማለቱ የሚሰግድ ሆኖ አይደለም፡፡ እንደተናገርን ተንኮል ስለነበር እንጂ፤ ጌታን ይገድለው ዘንድ ስለወደደ እንጂ፡፡
ሰብአ ሰገልም ንጉሡን ሰምተው ሄዱ፡፡ ቤተ ልሔም ደረሱ፤ የተባለው ንጉሥ አገኙት፤ ሰገዱለትም፡፡ መስገድ ብቻ አይደለም፤ ለነገሥታት ንጉሥ ለእግዚአብሔር ብቻ የሚቀርብ ገጸ በረከትም (ዕጣንና ከርቤን) አበረከቱለት እንጂ፡፡ ሰብአ ሰገል በግርግሙ በዐይነ ሥጋቸው የሚያዩት አንድ ሕፃን፣ አንዲት “ድሀ” ድንግል እንዲሁም አንድ ሽማግሌ ብቻ ነው፡፡ የሚያደርጉትን ነገር በግዙፉ ዐይኑ የሚመለከት ሰው በስንፍና ሊወድቅ ይችላል፡፡ እነርሱ ግን በዐይነ ልቡናቸው ሌላ የሚያዩት ግሩም ምሥጢር ነበራቸው፡፡ ሰማይንና ምድርን በእጁ የጨበጠው ጌታ ከላይ ሳይጎድል ከድንግል ዕቅፍ አዩት፤ ከምልአቱ ሳይወሰን በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት አዩት፤ የማያንቀላፋው ትጉሁ እረኛ በግርግም ተኝቶ ተመለከቱት፡፡ ከአምልኮተ ጣዖት እንደምን በሚያውቁትና በለመዱት ኮከብ ወደዚህ አስደናቂው ልደቱ መርቶ እንዳመጣቸው እያስተዋሉም “ዕፁብ ዕፁብ” ይላሉ፡፡ በዚህ ብቻ የተገረሙ አይደለም፤ መላእክትም ስብሐተ እግዚአብሔር ሲያደርሱ ስላዩ እጅጉን ተደመሙ እንጂ፡፡ እረኞች ያንን ሰማያዊ ክንውን አይተው ለሕዝቡ ሁሉ ለመንገር ሲፋጠኑም አይተው “በአማን ድንቅ መካር ኃያል አምላክ ነው” እያሉ በአንክሮ በሐሴት ተመሉ እንጂ፡፡ የጥበብ ሰዎች ነገሥታት ቢሆኑም እውነተኛው ንጉሥ እርሱ ብቻ ነውና ሰገዱለት፡፡ በጉልበታቸው ብቻ አይደለም፤ በልባቸውም ጭምር ተምበረከኩለት እንጂ፡፡ መሥዋዕትን አቀረቡለት፤ ሆኖም እንደ አይሁድ በግና ፍየል አይደለም፤ በእውነትና በመንፈስ የሚቀርብ አምልኮ እንጂ፡፡
ይህን አድርገው
ከፈጸሙ በኋላ እንደ ድሮ ኮከብ ሳይሆን መልአክ ተገለጠላቸው፡፡ በመጡበት መንገድም እንዳይሄዱ ነገራቸው፡፡ (ሄሮድስ) በእውን እንደነገራቸው ሊሰግድለት ሳይሆን ሕፃኑን ሊገድለው እንደሚሻ በሕልማቸው ተረድተዋልና ወደ ጨካኙ ንጉሥ እንዳይመለሱ አስጠነቀቃቸው፡፡ እነርሱም ይህን ተረድተው በሌላ መንገድ ተመለሱ፡፡ “የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው?” እያሉ መጥተው “ንጉሠ ሰማይ ወምድር አገኘነው” እያሉ በሌላ መንገድ በሌላ ሃይማኖት በሌላ ኃይለ ቃል ተመለሱ፡፡
እነርሱ ከሄዱ በኋላም የጌታ መልአክ መጣ፡፡ ወደ እመቤታችን ሳይሆን ወደ ዮሴፍ! መጥቶም “ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብጽ ሽሽ፤ እስክነግርህም ድረስ እዚያ ተቀመጥ” አለው፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ ዮሴፍ እመቤታችን ወላዲተ አምላክ መሆኗን አውቋልና መልአኩ “እጮኛህን” አልያም “ሚስትህን” አይለውም፡፡ “ልጅህን ኢየሱስንም” አይለውም፡፡ እንደተናገርን የተወለደው ሕፃን ማን እንደሆነ ወላጂቱም ማን እንደሆነች በሚገባ አውቋልና፡፡
ተወዳጆች ሆይ! የዮሴፍን የእምነቱ ብዛት የምታስተውሉ ሁኑ፡፡ ምክንያቱም መልአኩ በነገረው ነገር አንዳች የሚደናገጥ አይደለምና፡፡ አረጋዊው ዮሴፍ “መልአኩ ሆይ! የምትነግረኝ ነገር ለመቀበል እጅጉን የሚያስቸግር ነው፡፡ አስቀድመህ ሕዝቡን ሁሉ ያድናቸዋል ብለህ ነግረኸኛል፤ አሁን መረዳት እንደምችለው ግን ራሱን እንኳን ማዳን አልተቻለውም፡፡ እንድንሄድ የምትነግረንም ሀገርም እንዲሁ ቅርብ አይደለም፤ የባዕድ ሀገር እንጂ የምናውቀውም አይደለም፡፡ ስለዚህ አሁን የምትነግረኝ ሁሉ አስቀድመህ ከነገርከኝ የሚቃረን ነው” አላለውም፡፡ አዎ! ዮሴፍ ፍጹም የእምነት ሰው ስለ ነበር እንዲህ ያለ የስንፍና ቃል አልተናገረም፡፡ መልአኩ “እስክነግረህ ድረስ እዚያ ተቀመጥ” አለው እንጂ እስከ መቼ ድረስ እንደሆነም አልነገረውም፡፡ ዮሴፍ ግን ሁሉንም በጸጋ ተቀበለው፤ ታዘዘው፤ እሺ በእጄ ብሎ እናቱንና ብላቴናውን ይዞ ወደ ግብጽ ሄደ፡፡ ዳግመኛም፡- “አንተስ ከእኛ ጋር ትሄዳለህን?” ብሎ መልአኩን አልጠየቀውም፡፡ የመላእክት ጌታ ከእርሱ ጋር እንደሆነ ያውቃልና አንድም ጌታ ባለበት አንድ ብቻ ሳይሆን ሕልቆ መሳፍርት መላእክት በዙርያው እንዳሉ ያውቃልና ኮብላይ ለልማዱ መንገዱ በሌሊት እንዲሄድ በሌሊት ሸሸ፡፡
ከእናንተ መካከል፡- “ጌታ የተሰደደው ስለምንድነው?” ብሎ የሚጠይቅ ሰው ሊኖር ይችላል፡፡ እኛም እንዲህ ብለን እንመልስለታለን፡፡ ጌታችን ስለ ብዙ ምክንያት ተሰዷል፡፡ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል፡-
1.
ፍፁም ሰው
መሆኑን ለማረጋገጥ፡- ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ አምላክነቱ በተአምራት ከሚገደሉት ሕፃናት ድኖ ቢሆን “እነዚህ ክርስቲያኖች አካላዊ ቃል በተለየ አካሉ ፍጹም ሰው ሆኗል ይሉናል እንጂ እርሱ ሰው አልሆነም፤ ሰውስ ቢሆን ኖሮ ሄሮድስ ከሚያስገድላቸው ሕፃናት ጋር አብሮ ይሞት ነበርና” እያሉ በተሳለቁ ነበር፡፡ ስለዚህ እንዲህ ብለው ምክንያትን ለሚያመጡ በጥበቡ ምክንያት ያሳጣቸው ዘንድ ለተሰደዱት ወደብ የሚሆንላቸው እርሱ ተሰደደ፡፡ በመልዕልተ መስቀል የሚሞትበት ጊዜ ገና አልደረሰምና ተሰደደ፡፡
2.
ሰማዕትነትን ለመቀደስ፡-
ሰማዕትነት በእሳት መቃጠል በስለት መታረድ ብቻ አይደለም፡፡ ከሀገር ወደ ሀገር መሰደድም ሰማዕትነት ነው፡፡ ስለዚህ ይህን ይቀድስ ዘንድ ጌታ ተሰደደ፡፡ ፍቁራን ሆይ! አስደናቂውን ነገር ታስተውሉ ዘንድ እንማልዳችኋለን! በእውነት የአምላክ በሥጋ መሰደድ አይደንቅም፤ ለድኅነተ ዓለም የመጣው ጌታ ሰይጣን በሄሮድስ አድሮ ቢያሳድደው አይደንቅም፡፡ ምንም በደል ሳይኖርባት ለታመመው ዓለም መድኃኒትን ስለ ወለደች ብቻ የተሰደደች የድንግል ማርያም ስደት ግን እጅጉን ያስደንቃል! መላእክት ደስ ብሎዋቸው ያመሰገኗት እመቤት አሁን በበረሀ ልጇን አዝላ ስትደድ ማየት ያስደንቃል! የሕይወትን ውኃ የሚሰጥ ልጅ ይዛ በውኃ ጥም አፏ ሲደርቅ ማየት ያስደንቃል! ድካምን የማታውቅ የአሥራ አምስት ዓመት ብላቴና ጌታን ተሸክማ በሐሩር በቁር ስትንከራተት ማየት በእውነት ያስደንቃል፡፡ ወዮ! እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ! ይኽን ሁሉ መከራ እንደምን ቻልሽው? የዓለምን መድኅን ወልደሽ እንዴት ይኼ ሁሉ እንግልትና ስደት ደረሰብሽ? ከመከራ ሁሉ የሚገላግል ጌታን በመሀል እጅሽ ይዘሽስ እንደምን አላጉረመረምሽም? ለመሆኑ በዚሁ ዕድሜሽ ወደማታውቂው የባዕድ ሀገር ስደትን ያስተማረሽ ማን ነው? እኮን እንምን ቻልሽው? በቤተ መቅደስ ሰማያዊ መናን ስትመገቢ ያደግሽ ንዕድት ክብርት ቅድስት ሆይ! የአሁኑን ረሀብ እንደምን ተቋቋምሽው? የሲና በረኻን ጥም እንደምን ታገሥሽው? ይራዱሽ ዘንድ እናትሽ ሐና ዘመድሽም ኤልሳቤጥ አሁን ከአጠገብሽ አልነበሩም፡፡ ታድያ የተሸከምሽው ሕፃን እንደ ሰውነቱ ውኃ ሲጠማውና እፍኝ ውኃ አጥቶ ሲያለቅስብሽ ወላዱ አንጀትሽ እንደምን ቻለ? ተወዳጆች ሆይ! እመብርሃንስ ይህን ሁሉ ቻለች፡፡ ችላም ታላቅ መጽሐፍ ሆነችልን፡፡ ታድያ በጉልህ ከሚነበበው ከዚህ መጽሓፏ (ሕይወቷ) ምን እንማራለን? ምን ያህልስ ታጋሾች እንሆን?
3.
ካሣ ለመክፈል፡-
አዳም ከገነት አፍአ ወደ ምትሆን ወደ ምድር ተሰዶ ነበር፡፡ ጌታም የተሰደደውን አዳም ይመልሰው ዘንድ ካሣ ይከፍልለት ዘንድ ተሰደደለት፡፡ ፍቁራን ሆይ! ካሣ በመስቀል ላይ ብቻ የተከፈለ እንዳልሆነ ታስተውላላችሁን?
4.
ክፉን በክፉ
መመለስ እንደሌለብን ያስተምረን ዘንድ፡- ሄሮድስ ስለ ንግሥናው ተጨንቆ መድኅኑን ሲያሳድደው፣ እናቶችን ሲያስለቅስ፣ የንጹሕ ጨቅላ ሕፃናትም ደም ሲያፈስ ጌታ በቁጣ የመለሰለት አይደለም፡፡ ይልቁንም ኃይል እንደሌለው ተሰደደ እንጂ፡፡ ሆኖም ፈርቶ አልነበረም፡፡ እንደተናገርን ክፉን በክፉ መመለስ እንደሌለብን አንድም ለክርስቲያን ስደቱ ፍርሐት እንዳልሆነ ያስተምረን ዘንድ እንጂ፡፡
ከእናንተ መካከል፡-
“መሰደዱንስ ይሁን፤ ሌላ ብዙ ሀገር እያለ ስለምን ወደ ምድረ ግብጽ ተሰደደ?” ብሎ የሚጠይቅ ሰው ሊኖር ይችላል፡፡ እኛም እንዲህ ብለን እንመልስለታለን፡- ጌታችን ስለ ብዙ ምክንያት ወደ ግብጽ ተሰዷል፡፡ ጥቂቶቹን ለመግለጽ ያህል፡-
1.
ወንጌላዊው ራሱ
እንደነገረን በነቢዩ ሆሴዕ “ልጄን ከግብጽ ጠራሁት” የተባለውን ትንቢት ይፈጽም ዘንድ /ሆሴ.11፡1/፡፡
2.
ምሳሌው ይፈጸም
ዘንድ፡፡ ይኸውም ያዕቆብ ከእነ ልጆቹ በረሀብ ምክንያት ወደ ግብጽ ተሰዶ ነበር፤ ጌታም ከእናቱ፣ ከሰሎሜ እንዲሁም ከአረጋዊው ዮሴፍ ጋር ሄሮድስ “እንዳይገድለው” ተሰደደ፡፡ ያዕቆብ ወደ ግብጽ በመሰደዱ በረሀብ ከመሞት ዳነ፤ ጌታም ወደ ግብጽ በመሰደዱ በሄሮድስ ያለ ጊዜው ከመሞት “ዳነ”፡፡
3.
ገዳማተ ግብጽን
ለመባረክ፡፡ ተወዳጆች ሆይ! ይህን በጥንቃቄ የምታስተውሉት ሁኑ፡፡ ጌታችን ከእናቱ ጋር ወደ ግብጽ በተሰደደ ጊዜ ቤተ ልሔም በሕፃናት ደም ስትጨቀይ ነበር፤ (በተቀበረችበት ቦታ የልጅ ልጆቿ በግፍ ሲሞቱ አይታ) ራሄል መጽናናት እምቢ እስክትል ድረስ አለቀሰች፡፡ የግብጽ በረሀዎች ግን በቅዱሱ ቤተ ሰብእ ኪደተ እግር ሲባረኩ ነበር፡፡ ቤተ ልሔም በሕፃናት ደም አኬልዳማ ስትመስል የተዋሕዶ ጠበቆች የሚሆኑ እነ ቅዱስ አትናቴዎስ፣ እነ ቅዱስ ቄርሎስ፣ እነ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ የሚፈልቁባቸው ገዳማተ አስቄጥስና
ሲሐት ግን ሲባረኩ ነበር፡፡ ቤተ ልሔም የአጋንንት መፈንጫ ስትሆን ገዳማተ ግብጽ ግን ገነትን መስለው ነበር፡፡ ቤተ ልሔም የዋይታ ምድር ስትሆን የኢትዮጵያ ገዳማት ግን ሲባረኩ ነበር፡፡ ስለዚህ እነዚህን ለመባረክ ተሰደደ፡፡
4.
የወንጌል አንዱ
አካል ነው፡፡ አስቀድሞ ማለትም በዘመነ ብሉይ (እግዚአብሔር) እስራኤል ዘሥጋ ወደ ግብጽና ወደ ባቢሎን እንዲሰደዱ ፈቅዶ ነበር፡፡ ይኸውም እነዚህ ቦታዎች አምልኮተ ጣዖት በርትቶባቸው ስለነበር ነው፡፡ ስለዚህ ሀልወተ እግዚአብሔር በጥቂቱም ቢሆን ከስዱዳኑ አይሁዳውያን እንዲማሩ፣ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማድረግ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ እስራኤል የገፉትን እንጀራ (ጌታ ራሱ) እንዲቀበሉት፣ እንዲበሉት አደረጋቸው፡፡ ወደ ግብጽ እርሱ ራሱ ከእናቱ ጋር ሲሄድላቸው ወደ ባቢሎን ደግሞ ያመኑትን ሰብአ ሰገልን ላከላቸው፡፡
ተወዳጆች ሆይ!
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ጋራ ወዳለበት መሄድ የማይናፍቅ ማን ነው? እንግዲያውስ ኑና አብረን ከስደቱ በረከት ተካፋዮች እንሁን፡፡ ኑና ከስብሐተ መላእክት ጋር የምተባበር እንሁን፤ ኑና ከነ አባ ጽጌ ድንግል ጋር እንዘምር፤ ኑና ከነ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ጋር እናሸብሽብ፤ ኑና ከቅዱሳን ሁሉ ጋር ከማኅሌቱ እንታደም፡፡ ኑና ክፉውን መሸሽ ፍርሐት እንዳልሆነ እንማር፡፡ ኑና የእመቤታችንን ሕይወት እናንብብ… ኑና ከተሰደድንበት እንመለስ… ኑና እንባረክ ዘንድ እንፍቀድ… ኑ ሄሮድስን ትተን እንሽሽ… ኑና ቂም በቀልን ትተን እንሽሽ… ኑ የንጹሐን ደም ከሚፈስበት መንደር እንራቅ፡፡
ቅዱስ እግዚአብሔር
ሆይ! እንድንፈቅድ ቀስቅሰን… ስንፈቅድም አበርታን! አዛኚቱ ሆይ! የበረሀው ጉዞ ውጦ እንዳያስቀረን በቃል ኪዳንሽ እርጂን! አሜን!!
ምንጭ: http://mekrez.blogspot.com/
ምንጭ: http://mekrez.blogspot.com/
No comments:
Post a Comment