[ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 6]
"ልጄን ከግብፅ ጠራሁት"
(ት.ሆሴዕ 11፥1 )
ከመምህር ዮሐንስ ለማ
እመቤታችን በስደቷ የተጓዘችባቸው |
ሐዋርያዊት የሆነች ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ ክርስቲያናዊ ትውፊታዋን ጠብቃ፣ መንፈሳዊ አገልግሎቷን በሚገባ አራቅቃ፣ ዘመንን በክፍል በክፍል ቀምራ፤ ከመስከረም ጀምሮ እስከ ጳጉሜን ድረስ ያሉት ሰንበታት የራሳቸው የሆነ ከምሥጢረ ድህነት ጋር የተያያዘ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ስያሜ ሰጥታ የሰው ልጆችን ከመርገመ ሥጋ ከመርገመ ነፍስ ለማዳን የተደረገው (የተፈጸመው) አምላካዊ የድኅነት ጉዞ እያዘከረች፣ እያስተማረች... ለዘመናት ቆይታለች፣ አሁንም በማስተማር ላይ ናት ። ለወደፊትም እግዚአብሔር እስከ ፈቀደላት ጊዜ ድረስ ስትመሰክርና ስታስተምር ትኖራለች፡፡ እመቤታችን በትልቅ
የምስጋና አገልግሎት ከሚከበሩላት በዓላት መካከል የወርሐ ጽጌ (ዘመነ ጽጌ ) አንዱና በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ልብ ውስጥ ጥልቅ የልቡና ፍቅር ያለው ይሕ የወርሐ
ጽጌ ወቅት አንዱ ነው
፡፡ በመሆኑም በክፍል አንድ ጽሐፍ የእመቤታችን የቅድስት
ድንግል ማርያምን ስደት በማስመልከት ምክንያተ ስደቷንና ተያያዥ ርዕሶችን ማስነበባችን ይታወሳል፡፡ አሁን
ደግሞ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በስደቷ ወቅት ያሳለፈቻቸውን ውጣ ውረድና ተያያዥ ክስተቶችን እንዲሁም የጉዞዋን
ዋና ዋና መዳረሻዎችን ጭምር ለማስነበብ እንሞክራለን፡፡
ንጉሥ ሄሮድስ እና ሰብአ ሰገል
ከሩቅ ምሥራቅ የመጡት ነገሥታት ( ሰብአ ሰገል ) ለዓመታት ያህል ተጉዘው ኢየሩሳሌም ከደረሱ በኋላ፡-"አይቴ ሀሎ ንግሥ እስራኤል ዘተወልደ ከመ ነሃብ ሎቱ አምሃ ወሰጊድ" ..... ይዘን የመጣነውን መባዕ እና ስግደት እናቀርብለት ዘንድ የተወለደው ሕፃን ወዴት ነው ‘’ ? ወርቅ ለመንግስቱ፣ ዕጣን ለክህነቱ፣ ከርቤ ስለሞቱ እናበረክትለት ዘንድ የተወለደው የዓለም ንጉሥ የት አለ ? እያሉ ሲፈልጉና ሲያፈላልጉ በመልእክተኞቹ አማካኝነት የሰማው የኢየሩሳሌም ንጉሥ ሄሮድስ ይህ ምን ዓይነት ነገር ነው ? የትስ ያለ የዓለም ንጉሥ ነው ? የሚወለደውስ ከማንና መቼ ነው ? አሁን ገና በተወለደ ጊዜ እንዲህ ነገሥታትን ያሰገደ ሕፃን ሲያደግማ እኔንም ያሰጋኛል፤ አልፎም ያጠፋኛል ብሎ እጀግ ከመፍራትና ከመደንገጡ የተነሳ ነገሥታቱን አስጠርቶ ስለ ነገሩ አስፍቶ ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም በኮከብ መሪነት ለዓመታት ያህል መጓዛቸውንና አጠቃላይ የአመጣጣቸውን ታሪክ ተረኩለት፡፡ ታሪኩን ሰምቶና ተረድቶ ከበቃ በኋላ ንጉሡ ሄሮድስ ለነገሥታቱ ስለ ሕፃኑ ጠቅላላ ሁኔታ እንዲያጠኑ ሲመለሱም ምስጢሩን እንዲገልጹለት አደራ ብሎ
ካሰናበታቸዉ በኋላ መልዓከ እግዚአብሔር ተገልጾ በሌላ መንገድ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ስለነገራቸውና ምስጢሩንም ስለገለጸላቸው የሄሮድስ ተንኮላዊ አደራን ወደ ጎን ትተው መልዓኩ እንደነገራቸው በሌላ መንገድ ወደ ሃገራቸው ተመለሱ፡፡ከሰብአ ሰገል መረጃን ለማግኘት ያደረገው ጥረት ሳይሳካለት ቀርቷል፡፡
ሰብአ ሰገል
ወደ እርሱ ባለመመለሳቸው የተበሳጨው ሄሮድስ የራሱን እርምጃ ለመውሰድ ወሰነ፡፡ ምንጊዜም ሄሮድስ የሚፈልገው በቤተልሔም የተወለደውን የአይሁድ ንጉሥ የተባለውን ሕፃን ክርስቶስን አግኝቶ መግደል ነው፡፡ ስለሆነም ሕፃኑ
ክርስቶስ ያለበትን ቦታ የሚጠቁም ሰው አላገኘም፡፡ ትክክለኛውን መረጃ ባያገኝም ከሰብአ ሰገል አንደበት የሰማውን ለእንቅስቃሴው መነሻ አድርጎ ተነሣ፡፡ሄሮድስ እንደ መረጃ የተጠቀመው ፡-
ሰብአ ሰገልን የመራቸው ኮከቡ የተገለጠበትን ዘመን ነው፡፡
ሰብአ ሰገልን ጠይቆ የኮከቡን ዘመን ተረድቶ
ነበር፡፡ ኮከቡ ለሰብአ ሰገል ከተገለጠ ወይም ሰብአ ሰገልን መምራት ከጀመረ ሁለት ዓመት እንደሆነው በጥንቃቄ ተረድቷል፡፡ ሰብአ ሰገልን የመራቸው ኮከብ ሁለት ዓመት ከሆነው የአይሁድ ንጉሥ የተባለው በቤተልሔም የተወለደው ሕፃን ክርስቶስም ሁለት ዓመት ሊሆነው ይችላል የሚል ግምት መገመት ጀመረ ፡፡
ቦታው ቤተልሔም መሆኑ እና የአይሁድ ንጉሥ የተባለው ሕፃን የሁለት ዓመት ሕፃን መሆኑ በመረጃ ተደግፏል፡፡ ነገር ግን በቤተልሔም ብዙ የሁለት ዓመት ሕፃናት ይኖራሉ፡፡ የአይሁድ ንጉሥ የተባለውን ሕፃን እንዴት ለይቶ ማወቅ ይቻላል? የሄሮድስ ልቡ የሚረጋጋበት መፍትሔ
አላገኘም፡፡
ሌላ አማራጭ መፈለግ ግድ ሆነበት፡፡ ከዚህ በኋላ ሄሮድስ በቤተልሔምና በአውራጃዋ የሚኖሩትን ሁለት ዓመት የሆናቸውን እና ከሁለት ዓመት በታች የሆኑትን ሕፃናት መግደል አማራጭ የሌለው የጭንቀቱ መፍትሔ አድርጎ ወሰደው፡፡መፍትሄውም በቤተልሔም ሕፃናት ላይ
ይህን የእልቂት ትእዛዝ ማስተላለፍ በማሰብ ነው፡፡ ሄሮድስ ከቤተልሔም ሕፃናት አንዱ ተነስቶ እንዳይቀር እጅግ ይጠነቀቅ ነበር፡፡ ወታደሮቼ በየሰፈሩ እየዞሩ ሕፃናትን ቢገድሉ ብዙ ወላጆች ልጆቻቸውን ይሰውራሉ ሕፃናቱም ከሞት ያመልጣሉ ከሚያመልጡትም ሕፃናት አንዱ ክርስቶስ ሊሆን ይችላል፡፡ ሌላው ደግሞ የሚገደሉት ሕፃናት ከሁለት ዓመት በታች መሆናቸው በግምት አይታወቁም በማለት ይጨነቅ ነበር፡፡ ሄሮድስ ብዙ ሐሳቦችን ሲያንሸራሸር ከቆየ በኋላ ሁሉም ሕፃናት በቤተመንግሥቱ አንድ ቀን ቢገኙ የተሻለ ነገር እንደሆነ አሰበ፡፡ ነገር ግን ሕፃናቱ እንዴት እንደሚሰበሰቡ ሌላ ፈተና ሆነበት በንጉሣዊ ትእዛዝ ወላጆች ልጆቻቸውን
እየያዙ እንዲመጡ ቢደረግ በኃይል ወይም በግድ የሆነ ነገር ውጤታማ እንደማይሆን እና ብዙ ሕፃናት እንደሚቀሩ መገመት አላቃተውም፡፡ የቤተልሔም ሕፃናት አንድ ሳይቀር እንዲሰበሰቡ ለማድረግ የወላጆች ፈቃደኝነት አስፈላጊ ሆኖ አግኝቶታል፡፡ ንጉሥ ሄሮድስ በቤተልሔምና በአውራጃዋ የነበሩትን ሁለት
ዓመት የሆናቸውን ከዚያም የሚያንሱትን ሕፃናት ሁሉ አስገደለ ( ማቴ. 2፡16-18 ) ።
ሄሮድስ ሕፃናትን ለመግደል በቤተመንግሥቱ ለመሰብሰብ
የተጠቀመበት
ምክንያተ ፈጠራ
የሄሮድስ ቅንዓት እጨመረ ከመሄዱም በላይ ነገሥታቱን ሲጠብቅ ሁለት ዓመት መሆኑን ተከትሎ በነገሩ ተሳልቀውበት (አታልለውት) በሌላ መንገድ መሄዳቸዉን
ከተረዳ በኋላ ሰይጣን የጭካኔ ጦሩን መዞ አንድ ጊዜ በልቦናው ላይ ስለተከለበት ሁለት ዓመትና ከዚያ በታች ያሉ ሕፃናት ሁሉ በእርዳታ ስም በየሀገሩ እንዲሰበሰቡ የሚል ሰይጣናዊ የአረመኔነት መግለጫ የሆነ አዋጅ በብሔራዊ ደረጃ አሳወጀ፡፡
ሄሮድስ ሕፃናትን በቤተመንግሥቱ ለመሰብሰብ አንድ ምክንያት ፈጠረ፡፡ እንዲህም አለ የሮሙ ንጉሥ ቄሣር የላከው መልእክት ከእኔ ደርሷል፡፡ ሁለት ዓመት የሆናቸውን እና ከሁለት ዓመት የሚያንሱትን ሕፃናት እንድቆጥር ቄሣር አዞኛል፡፡ ለሕፃናቱ ወላጆች ገንዘብ እና ልብስ ይሰጣቸዋል፡፡ ሕፃናቱም በቤተመንግስት በመልካም አስተዳደግ ያድጋሉ፡፡ ማርና ወተት እየተመገቡ ጥበብ እየተማሩ በቤተመንግስት አድገው የመንግስት ሠራተኞች ይሆናሉ፡፡ ይህንም የተንኮል አነጋገር በአዋጅ አስነገረ፡፡ ያን ጊዜ አይሁድ የሮሙ ንጉሥ የቄሣር ቅኝ ተገዦች ነበሩ፡፡ ሄሮድስም የአይሁድ ንጉሥ ሊሆን የቻለው ከቄሣር ተወክሎ ነው፡፡ ስለሆነም ትእዛዙ ከቄሣር እንደመጣ አድርጎ በውሸት ማዕበል ቤተልሔምን አጥለቀለቃት፡፡ ትእዛዙ ግን ከሮሙ ንጉሥ ከቄሣር የመጣ ሳይሆን የሐሰት አባት ከሆነው ከዲያብሎስ የመጣ ነው፡፡ዛሬም ሐሰት ከዲያብሎስ
እየተወለደ በቤተመንግስት ያድጋል፡፡ ሐሰት ለገዢዎች የሥልጣናቸው እድሜ ማራዘሚያ ይመስላቸዋልና ነው ( ዮሐ.8፡44 ) ።
ንጉሥ ሄሮድስ እና የ144000 ሕፃናት ሞት በቤተመንግስት
ከዚህ በኋላ ብዙ ሕፃናት ከእናቶቻቸው ጋር በሄሮድስ ትዕዛዝ በቤተመንግሥት ለመታረድ ተሰበሰቡ፡፡ ልጅ ያላቸው ወላጆች ልጆቻቸውን እየያዙ ሲሄዱ ልጅ የሌላቸወ ድሃዎች ደግሞ ሀብት ንብረት ልብስ ቀለብ ለመቀበል የሀብታሞችን
ልጆችን እየተዋሱ ይዘው ሄደው ነበርና በጠቅላላው በሄሮድስ ቤተመንግስት
144 000 ሕፃናት ተሰበሰቡ፡፡ ሄሮድስ በተንኮል የሰነቀው የተስፋ ዳቦ ሕፃናቱንም ወላጆችንም የሚያጠግብ መስሎ ስለቀረበ በቤተልሔም አንድ ሕፃን አልቀረም፡፡ ሄሮድስ የሚፈልገው የአይሁድ ንጉሥ የተባለው ሕፃን ክርስቶስ ግን ከ 144 000 ሕፃናት መካከል አልነበረም፡፡ ሄሮድስ በግብዝ አእመሮው ከ 144 000 ሕፃናት መካከል አንዱ የአይሁድ ንጉሥ የተባለው ሕፃን ሳይሆን አይቀርም ብሎ ሕፃናቱ እስኪገደሉ ይቸኩል ነበር፡፡ ሁሉንም ሕፃናት ግደሉ ብሎ ለወታደሮቹ ንጉሳዊ ትዕዛዙን አስተላለፈ፡፡ የሄሮድስ ወታደሮች በአንድ ቀን 144 000 ሕፃናትን አረዱ፡፡ በየሰፈሩ ለቅሶና ዋይታ ሆነ፡፡
የንጉሡ ወታደሮችም
በእርዳታ ስም የሰበሰብዋቸውን ሕፃናት እጅግ በሚዘገንን መልኩ የእናቶቻችውን ጡት እንኳ በአግባቡ ጠጥተው ሳይጨርሱ አንገት አንገታቸውን በሰይፍ ቆራርጠው ጨረስዋቸው፡፡ይሁን እንጂ ይህ የሕፃናት እልቂት በንጉሱ ትእዛዝ ምክንያት ከመፈጸሙ አስቀድሞ ንጉሡ ይህንን እኩይ ሐሳብ ሲያስብ በዮሴፍ ጠባቂነት፣ በእመቤታችን እናትነትና በቅድስት ሶሎሜ ረዳትነት ያድግ የነበረው ጌታችን ይህ አዋጅ ከመታወጁና እልቂቱም ከመፈጸሙ አስቀድሞ መልዓከ እግዚአብሔር በሌሊት ለቅዱስ ዮሴፍ ተገልጾ "ተንሥእ ወንሣእ ሕፃነ ወእሞ" ሄሮድስ ሕፃኑን
ሊገድለው፣ አለጊዜውም ደሙን ሊያፈሰው አጥብቆ ይፈልገዋልና እናቱንና ልጁን ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ (ማቴ 2፡1-23) ። በማለት ተናግረውና በዚያች ሌሊት ወደ ምድረ ግብፅ ጉዞ ጀመሩ፡፡ ታሪኩ በማቴዎስ ወንጌል እና ጥር ሦስት ቀን በሚነበበው በመጽሐፍ ስንክሳር ተመዝግቧል፡፡ ነቢዩ ኤርምያስ ስለዚህ ጽኑዕ ኀዘን ትንቢት ተናግሮ ነበር፡፡"ድምፅ በራማ ተሰማ ለቅሶና ብዙ ዋይታ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች መጽናናትንም አልወደደችም የሉምና"
የተባለው ተፈጸመ (ማቴ. 2፡18፣ ኤር. 31፡15 ) ። ራሔል የያዕቆብ ሚስት የዮሴፍና የብንያም እናት መሆንዋ ( በዘፍጥረት . 30፡22 እና 35፡16 ) ተጽፏል፡፡ የቤተልሔም
ሕፃናት በሄሮድስ ሰይፍ በታረዱ ጊዜ ራሔል አልነበረችም፡፡ ሆኖም ልጆቻቸው የታረዱባቸው እናቶችና የታረዱ ሕፃናት የራሔል የልጅ ልጆች ስለሆኑ በልጆቻቸው ሞት መጽናናት ያቃታቸውን እናቶች በራሔል ወክሎ ይናገራል፡፡ ኤርምያስ በልጆቻቸው ሞት የሚያነቡትን የእስራኤልን ሴቶች ራሔል ብሏቸዋል፡፡
ከእመቤታችን ስደት ጋር ታሪክ ያስተናገደው የዮሴፍ ልጅ ዮሳ
የዮሴፍ ልጅ ዮሳ ከእነ ዮሴፍ ጋር አልተሰደደም ከአባቱ ቤት ቀርቶ ነበር፡፡ ሄሮድስ እነ ዮሴፍን ለመያዝ ብዙ ጭፍራ ላከ፡፡ የሄሮድስን የተንኮል ምሥጢር የሚያውቁ ሰዎች ሄሮድስ ዘመዶችህን ሊያስገድል ብዙ ጭፍራ /ወታደር/ ላከ ብለው ለዮሳ ነገሩት፡፡ የዮሴፍ ልጅ ዮሳ እየሮጠ ወደ ዘመዶቹ ሲሄድ ሰይጣን ሰው መስሎ መንገድ ዳር ተቀምጦ የት ትሄዳለህ አለው፡፡ ወደ ዘመዶቼ አለ ዮሳ፡፡ የሄሮድስ ወታደሮች ለጥቂት ቀደሙህ እሰከአሁን ዘመዶችህን ገለዋቸው ይሆናል፡፡ ምን ያደክምሃል ተመለስ አለ ሰይጣን፡፡ ዮሳም ዘመዶቼ ሞተው ከሆነ እቀብራቸዋለሁ አልሞቱም ከሆነ ሄሮድስ
እያስፈለጋቸው መሆኑን አነግራቸዋለሁ ብሎ የሰይጣንን ምክር ሳይቀበል መንገዱን ቀጠለ፡፡ እግዚአብሔር ለዮሳ የአንበሳን ኃይል ሰጠው፡፡ እነዮሴፍ ሦስት ቀን የተጓዙትን መንገድ በአንድ ቀን ተጓዘና እነዮሴፍ ከደረሱበት ቦታ ደረሰ፡፡ እነዮሴፍ ሦሰት ቀን በተከታታይ ስለተጓዙ ደክሞቸአው አርፈው ነበር፡፡ ሰሎሜ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ስታጥበው አገኛቸው፡፡ዮሳ ሰላም ዋላችሁ ሰላም አደራችሁ ሳይል እንደደረሰ በጣም የሚያስደነግጥ ቃል ተናገረ፡፡ እንዲህም አላቸው በቤተልሔም እና በይሁዳ ሕፃን ያዘለች ሴት አትገኝም፡፡ ሁሉንም ሕፃናት ሄሮድስ በሰይፍ አሳርዷቸዋል፡፡ ይህን ሕፃን ኢየሱስ ክርስቶስን ልታስገድሉት ከዚህ ተቀምጣችኋል፡፡ እመቤታችን የዮሳን ቃል በሰማች ጊዜ ሕፃኑን ኢየሱስ ክርስቶስን ከሰሎሜ እጅ ተቀበለችና አቅፋ ይዛ በሌሊት ብርድ እና በፀሐይ ቃጠሎ መከራ የምቀበለው ከሞት ላላድንህ ነው ብላ ጽኑዕ ልቅሶን አለቀሰች፡፡
ሕፃኑ ኢየሱስ ክርሰቶስ ዮሳን እንዲህ አለው ድካምህ ዋጋ የሚያሰጥ ነው ነገር ግን እናቴን ስለአስደነገጥካት ይችን ድንጋይ ተንተርሰህ ተኛ አለው ፡፡ ወዲያውም ነፍሱ ከሥጋው
ተለየች፡፡ አባቱ ዮሴፍ ቀበረው፡፡ እንደእኛ እንደሰዎች አመለካከት ዮሳ የሚሸለም ሰው ነበር እንጂ የሚቀጣ ሰው አልነበረም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ዮሳ ባጠፋው ትንሽ ጥፋት በሥጋው ተቀጥቶ በነፍሱ ሕያው እንዲሆን አደረገው ፡፡ የአግዚአብሔር ወዳጆች ትንሽ ጥፋት ሲአጠፉ በሥጋቸው ይቀጣሉ፡፡ ለምሳሌ አሮን እና ሙሴ የእግዚአብሔር ወዳጆች ነበሩ፡፡ አንድ ቀን ባጠፉት ጥፋት ተቀጡ፡፡ ወደተስፋይቱ ምድር ሳይገቡ በመንገድ ሞቱ "እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን በእስራኤል ልጆች ፊት ትቀድሱኝ ዘንድ በእኔ አላመናችሁምና ስለዚህ ወደ ሰጠኋችሁ ምድር ይህን ጉባዔ ይዛችሁ አትገቡም" አላቸው ( ዘኁ. 20፡1-13 ) ። ጥበበኛው ሰሎምንም እንዲህ ይላል "ልጄ ሆይ የእግዚአብሔርን ተግሣጽ አትናቅ በገሠጸህም ጊዜ አትመረር እግዚአብሔር የወደደውን ይገሥጻልና አባት የሚወደውን ልጁን እንደሚገሥጽ"
( ምሳ. 3፡11 )
ዛሬስ በጌታ ላይ፣ በእመቤታችን ላይ፣ በቅዱሳን ላይ ያልተገባ የሰነፍ ንግግርንስ የሚናገሩ ምንኛ በነፍስ በሥጋ ይቀጡ ይሆን ?
ጥጦስና ዳክርስ ( ሁለቱ ወንበዴዎች )
ጥጦስ እና ዳክርስ ሁለት ወንበዴዎች መተዳደሪያቸው ቅሚያ ነበር፡፡ እነዮሴፍ ከገሊላ በወጡ ጊዜ ወንበዴዎቹ ተከተልዋቸው፡፡ በበረሃ ቢፈልጓቸውም እስከ ስድስት ቀን አላገኝዋቸውም፡፡ በሰባተኛው ቀን አገኝዋቸውና ዛሬስ እግዚአብሔር ከእጃችን ጣላችሁ ብለው እየሮጠ ሄዱባቸው፡፡ ሰሎሜ አስቀድማ ልብሷን ጥላላቸው ሸሸች፡፡ወንበዴዎቹ ከእነዮሴፍ እጅ የተገኘውን ቀምተው ከሄዱ በኋላ ጥጦስ ዳክርስን እንዲህ አለው፡፡ ይቺ ሴት የነገሥታት ወገን ትመስለኛለች፡፡ ሕፃኑም ከነቢያት አንዱ ይመስለኛል፡፡ የቀማናቸውን እንመልስላቸው? ዳክርስም ጥጦስን እንዲህ ያለውን ርኅራኄ ከየት አገኘኸው? ይህን ውንብድና ያስተማርከኝ አንተ ነህ፡፡ ሌላው ደግሞ ዛሬ የቀማነው የእኔ ድርሻ ነው የራስህን ድርሻ ወስደህ የእኔን ድረሻ እንመልስላቸው ትላለህ ? አለው፡፡እነዚህ ሁለት ቀማኞች አንድ ቀን የቀሙትን አንደኛው ሲወስድ በሌላ ቀን የቀሙትን ደግሞ ሁለተኛው ይወስድ ነበር፡፡ በዚህ ዕለት የቀሙት የዳክርስ ድርሻ ነበር፡፡ ጥጦስም ከገሊላ እስከዚህ የቀማነውን አንተ ውሰድ ይህን ለእኔ ስጠኝና ልመልስላቸው አለው፡፡ ዳክርስም በዚህ ሐሳብ ተስማማ፡፡ ዳክርስ ያልታደለ ሰው ነው፡፡ ጥሩ እድል ገጥሞት ነበር አልተጠቀመበትም፡፡ በትንሽ ርኅራኄ ብዙ በረከት አመለጠው፡፡ ወደ አርሱ ያንዣበበውን ፀጋ ለጓደኛው ሰጠው፡፡
እመቤታችን ሁለቱ ወንበዴዎች ቁመው በዚህ ሐሳብ ሲወያዩ አይታ ፈራች፡፡ ወንበዴ የቀማውን ይዞ ይሄዳል እንጂ ለምን ቁሞ ይማከራል? ምን አልባት ልጆቻቸው የሞቱባቸው ሰዎች ይሆናሉ፡፡ በዚህ ሕፃን ምክንያት ልጆቻችን ሞቱብን ብለው ልጄን ሊገሉብኝ ይሆናል ብላ ጽኑዕ ለቅሶን አለቀሰች፡፡ ሕፃኑ ኢየሱስ ክርስቶስም እናቱም ድንግል ማርያምን እንዲህ አላት፡፡ አይዞሽ እናቴ አታልቅሺ አይገሉኝም እንመልስላቸው እያሉ ነው፡፡ እኔ በቀራንዮ ስሰቀል እነሱም በቀኜ እና በግራዬ ይሰቀላሉ አንዱ አምላክነቴን አምኖ ይድናል ሁለተኛው ግን አይድንም፡፡ ከዚህ በኋላ ጥጦስ የተባለው ወንበዴ ገንዘባቸውን መለሰላቸውና ጌታን አቅፎ ይዞ ሲሄድ ሰይፉ ወድቆ ተሰበረበት፡፡ በጣም አዘነ፡፡ ጌታ የሰይፍህን ስብርባሪ ሰብስብ አለው፡፡ ጥጦስ የሰይፉን ስብርባሪ ሰበሰበ፡፡ ጌታም እንደቀድሞው ይሁንልህ አለው፡፡ ሰይፉም እንዳልተሰበረ ሆነ፡፡ ጥጦስ ሕፃኑ ከነቢያት ወገን ይመስለኛል ብሎ የገመተው ግምት እውን ሆነለት፡፡ ተአምራቱን አየና አደነቀ፡፡ ጌታ ጥጦስን እንዲህ አለው፡፡ አዳምን ቀድመኸው ገነት ትገባለህ፡፡ ጥጦስም ሄዶ ጌታ የነገረውን ሁሉ እና ያደረገለትን ተአምራት ለጓደኛው ነገረው፡፡ ጓደኛው ግን አላመነም፡፡ ጥጦስ የተባለው ወንበዴም ጌታ በተሰቀለ ጊዜ በጌታ ቀኝ ተሰቅሎ ፀሐይ ስትጨልም አይቶ የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት አምኖ "ጌታ ሆይ በመንግስትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ አለው፡፡ ኢየሱስም እውነት እልሃለሁ ዛሬ ከኔ ጋር በገነት ትሆናለህ" ( ሉቃ. 23፡42 ) ። ጌታ አዳምን
ቀድመኸው ገነት ትገባለህ ብሎ በጫካ የሰጠውን ተስፋ በመስቀል ላይ ፈጸመለት፡፡
እመቤታችን ከልጇ ጋር በስደት ከተጓዘችባቸው ሀገራት መካከል ፦
የድንግል ማርያም የስደትዋ ምስጢር ጸጋው የበዛላቸው ሊቁ ቅዱስ አባት አባ ጽጌ ድንግል "በሰቆቃወ ድንግል" በስፋት እንደገለጹት በዚህ ዓለም ላይ የኖረና ለወደፊትም የሚኖር ፍጡር እንደ ድንግል ማርያም አለመኖሩ አበክረው ያሰምሩበታል፡፡ ሊቁ ይህንን ድርሰታቸው ሲጀምሩም፡-ማኅሌተ ጽጌ፡-በስመ እግዚአብሔር ሥሉስ ሕጸተ ግጻዌ ዘአልቦ ሰቆቃወ ድንግል እጽሕፍ በቀለመ አንብዕ ወአንጠብጥቦ ወይሌ ወላህ ለይበል ለዘአንበቦ ከማሃ ሀዘን ወተሰዶ ሶበ በኩለሄ ረከቦ ርእዮ ለይብኪ ዓይነ ልብ ዘቦ.... ብለው ነው፡፡ ይኸውም እንኳንስ በዓይነ ሕሊና ወደ ምድረ ግብፅ ወርዶ ያየውና የሰማው አይደለም እንዲሁ ለይኩን ብሎ ያዳመጠው እንኳ ሳይቀር ከብዝሐ መከራዋ ተነስቶ እንደሚያለቅስ ይገልጽልናል፡፡ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ስደት መንፈሳዊ ዓላማና በምሥጢረ ድኅነት ዉስጥ የራሱ የሆነ ድርሻ ያለው እንጂ በአጋጣሚ የተገኘ እንዳልሆነ እንዲሁም የተነገረው ቃለ ትንቢት ለመፈጸም እንደሆነ ከላይ ተመልክተናል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ሲያትቱ ከተነገሩት ትንቢቶች መካከል፡-"ወፍኖቶሂ ዘእም ዓለም ርኢኩ አዕፃዳተ ኢትዮጵያ ይደነግፃ" ከጥንት የታሰበ መንገዱን አየሁ የኢትዮጵያ አውራጃዎችም ይደነግጣሉ (እንባቆም 3፡6-7) የሚለው ትንቢት በማራቀቅ እመቤታችን በመዋዕለ ስደቷ ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ በመምጣት ሃገራችንን ጎብኝታ ሕዝባችንን በአሥራት ተሰጥታ (ከልጇ ተቀብላ) እንደሄደች በመተረክ ሊቃውንት መምህራኑ ያራቅቃሉ፡፡ እመቤታችን ስትሰደድ ያልደረሰበት መከራ፣ ያልተፈራረቀባት ችግር ... አልነበረም፡፡ ይህም ሆኖ ግን ስለሚደርስባት ነገር ፈጽሞ አታስብም ነበር፡፡ የምታስበው ልጇ እንዳይሞትባት ብቻ ነው፡፡"ይእቲ ትበኪ ወትቤ ቀቲሎትየ ይቅድሙ፣ እም ይርአይ ለወልድየ ዘይትከአው ደሙ " ትርጉም እርሷም ይህንን ሰምታ አለቀሰች የልጄ ደሙ ሲፈስ ከምመለከትስ እኔን ያስቀደሙ፣(ሰቆቃወ ድንግል) እንደለ ደራሲ፡፡
ሀ . ገዳመ ጌራራል /ጌራራል ከተባለ ጫካ /፡ - መልአክ ለዮሴፍ ሕፃኑን እና እናቱን ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ ካለው በኋላ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአመቤታችን ጠባቂ ዮሴፍ የእመቤታችን አክስት ወይም የሐና እህት ሰሎሜ አራቱ ጉዞአቸውን ጀምረዋል፡፡ ወደ ግብፅ እንዲሰደዱ የተነገራቸው ቢሆንም ወደ ግብፅ ከመሄዳቸው በፊት ብዙ አገሮችን ዙረዋል፡፡ ከቤታቸው እንደወጡ ጌራራል ወደተባለ ጫካ ነበር የሄዱት
(ማቴ. 2፡13 ) ። እነዮሴፍን በገዳመ ጌራራል መላዕክት እየመጡ እያጽናኑዋቸው አርባ ቀን
ተቀምጠዋል፡፡ ከአርባ ቀን በኋላ አንድ አውሬ አዳኝ አያቸው፡፡ እርሱም በፍጥነት ሄዶ ማርያምንና ዮሴፍን ሰሎሜንም በጌራራል ጫካ ትላንትና አየኋቸው ብሎ ለሄሮድስ ነገረው፡፡ ሄሮድስም በጌራራ ጫካ መኖራቸውን በሰማ ጊዜ ደስ ተሰኘ፡፡ ይህንን ወሬ ላመጣለት አውሬ አዳኝ እነዮሴፍን ካሳየህኝ የመንግስቴን እኩሌታ እሰጥሃለው ብሎ በጣኦቱ ማለለት፡፡ ሄሮድስ በሀገሩ ሁሉ አዋጅ ነጋሪ /መልእክተኛ/ ላከ፡፡ አዋጅ ነጋሪው በሀገሩ እየዞረ ሁላችሁም የሄሮድስ ወታደሮች ነገ በሄሮድስ ቤተመንግስት እንድትገኙ በማለት አስጠነቀቀ፡፡ ወታደሮቹም የሄሮድስን ቤተመንግስት አጥለቀለቁት፡፡ ሄሮድስም ወደ ጌራራል ጫካ ላካቸው፡፡ የሄሮድስ ወታደሮች የጌራራልን ጫካ ከበቧት፡፡ ነገር ግን እነዮሴፍን አላገኙዋቸውም፡፡ ወታደሮቹ እርስ በራሳቸው እንዲህ ተባባሉ፡፡ እነዮሴፍ የትሄዱ ምድር ዋጠቻቸውን ? ይሉ ነበር
። እነዮሴፍን ግን የእግዚአብሔር መልአክ ወርዶ የሄሮድስ ሰራዊት በማያውቁት መንገድ ወሰዳቸው፡፡
ለ . ጥብርያዶስ ፦ ከዚህ በኋላ
የእመቤታችን ዘመድ የኬፋዝ ንጉሥ ወደ አለበት ወደ ጥብርያዶስ ሄዱ፡፡ እመቤታችንም ሄሮድስ እንደሚያሳድዳት ዘመዷ ለሆነው ንጉሥ ነገረችው፡፡ ንጉሡም ሄሮድስ የሚያሳድድሽ በምን ምክንያት ነው ብሎ ጠየቃት፡፡ ይህን ሕፃን ለመግደል ስለሚፈልግ ነው አለችው፡፡ ንጉሡም እመቤታችነን ከዚህ ከእኔ ቤት ተቀመጪ አላት፡፡ ቤተሰቦቼንም ማርያም ከእርሱ ቤት መኖርዋን ለማንም እንዳይነግሩ አስጠነቀቃቸው፡፡ ሄሮድስ ግን በብዙ ሀገሮች እየዞረ ቢፈልጋት ሊአገኛት አልቻለም፡፡ ሄሮድስ እንዲህ ይል ነበር፡፡ ማርያምን ምድር ዋጠቻትን? ሄሮድስ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመግደል ያደረገው ጥረት የደከመው ድካም እጅግ ብዙ ነው ያለውን ኃይል አሟጦ ተጠቅሞአል የሚፈልገውን አለማግኘቱ ደግሞ ድካሙን ውጤት አልባ አድርጎታል፡፡ ከብዙ ቀናት በኋላ ሄሮድስ ጥብርያዶስ በሚባል ሀገር እመቤታችን መኖርዋን ሰማ፡፡ እመቤታችን ወደ አለችበት ንጉሥ ደብዳቤ ጽፎ መልእክተኛ ላከ፡፡ ሄሮድስ የጻፈው ደብዳቤ እንዲህ ይላል፡፡ ንጉሥ ሆይ ሰላምታ ይገባሃል፡፡ ማርያምን ከነልጅዋ ያዝልኝ ብዙ ወርቅ እና ብር እሰጥሃለሁ በእኔ እና በአንተ መካከል ጽኑዕ ፍቅር ይሆናል፡፡ ንጉሡም የሄሮድስን ደብዳቤ አንብቦ በጣም ተገረመ፡፡ እንዲህም አለ፡፡ ማርያም በእኔ ቤት መኖርዋን ለሄሮድስ ማን ነገረው? መቼም ሰው አልነገረውም ሰይጣን ነግሮታል እንጂ፡፡ የእመቤታችን ዘመድ የሆነው ንጉሡም ሄሮድስ የላከውን መልዕክት ለእመቤታችን ነገራት፡፡ እመቤታችንም በጣም ደነገጠች፡፡ ንጉሡም እኔ ከሞትኩ ትሞቻለሽ እኔ ከዳንኩ ትድኛለሽ አትፍሪ፣ ለሄሮድስ አሳልፌ አልሰጥሽም አላት፡፡ ‘’ ወትቤ ማርያም ዘፈቀደ አምላከ እስራኤል ለይኩን /ማርያምም የእስራኤል አምላክ የፈቀደው ይሁን ‘’ አለች/፡፡ በዚያች ሌሊት የእግዚአብሔር መልአክ መጥቶ ሲነጋ
ይህን ሀገር ለቀሽ ወደ አድባረ ሊባኖስ ሂጂ አላት፡፡ በዚያም እኔ መጥቼ ተነሺ እስክልሽ ድረስ ተቀመጪ አላት፡፡ በነጋ ጊዜ መልአኩ የነገራትን ለንጉሡ ነገረችው፡፡ ንጉሡም ደስ ብሎት የሦስት ቀን መንገድ እሰከ ዛብሎን እና እስከንፍታሌም ድረስ ሸኛቷት ወደ ሀገሩ
ተመለሰ፡፡
ሐ . አድባረ ሊባኖስ ፦ እመቤታችን ከዮሴፍ እና ከሰሎሜ ጋር በደብረ ታቦር ጥግ አልፋ ወደ ተወለደችበት ወደ ደብረ ሊባኖስ ወጣች፡፡ ኰኵህ ከሚባለ ዛፍ ስር ተቀምጣ አለቀሰች፡፡ እንዲህም አለች፡፡ አቤቱ እሰከመቼ ድረስ ካንዱ ሀገረ ወደ ሌላው ሀገር ስዞር እኖራለሁ ነፍሴስ ምን ያህል ጸናች፡፡ ከዚህ በኋላ ያለችበትን ቦታ ሰው እንዳያውቅ ወደ ጫካው ገባች ለአሥር ቀናት ያህል ሰው ሳያያት ተቀመጠች፡፡ከዚህ በኋላ አንድ አውሬ አዳኝ ከሩቅ ሆኖ አያት፡፡ አውሬ አዳኙ ውሾች ነበሩት፡፡ ውሾቹ ጌታቸውን ትተው እየሮጡ ሄዱና ከእመቤታችን እግር በታች ሰገዱ፡፡ እመቤታችንም በእግርዋ የረገጠችውን መሬትም ይልሱ ነበር፡፡ አውሬ አዳኙ ከሩቅ ሆኖ ውሾቹን ጠራቸው፡፡ ውሾቹ ግን ወደ አንተ አንመጣም አንተ ምን ትሰጠናለህ ከአንድ ጉራሽ በቀር የዕለት ምግባችን ዕንኳ አትሰጠንም አሁንስ ፈጣሪያችንን አግኝተናል ይሉት ነበር፡፡ ድንግል ማርያም ውሾቹ የተናገሩትን ሰምታ አደነቀች፡፡ ፍጥረት ሁሉ ለሚፈሩህ ፈጣሪ ምስጋና ይገባሃል ብላ አመሰገነች፡፡ ውሾቹም ከእመቤታችን እግር ስር ተኙ የሰው ልቡና በተንኮል ሲሞላ እና ከሰው ቅንነት ሲጠፋ ለሰዎች መገለጥ የሚገባው ምሥጢር ለእንስሳት ይገለጣል፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ ለበለአም ሳይገለጥ ለተቀመጠባት አህያ እንደተገለጠ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል ( ዘኁ. 22፡23-30 ) ። የበለአም
ታሪክ በዚህ አውሬ አዳኝ ላይ ተደግሞአል፡፡ ሄሮድስ ፈጣሪውን
ወደ በረሃ አሳደደው፡፡ ውሾቹ ግን ወደ በረሃ ለተሰደደው ፈጣሪያቸው እና ለእናቱ ሰገዱ፡፡ ይህ ትልቅ ትምህርት ነው፡፡ ሰዎች በገንዘብ ፍቅር እና በሥልጣን ጥማት ሲቃጠሉ ከውሾቹ ያንሳሉ ማለት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ አውሬ አዳኙ ውሾቹን እየፈለገ መጣ፡፡ እመቤታችን ቅድስት ማርያም ከልጅዋ ጋር ጫካውን ስታበራ አያትና እጅግ አደነቀ፡፡ መንፈስ /ምትሐት/ እየታየው መሰለው፡፡ እመቤታችን ምን ትፈልጋለህ አለችው፡፡ አውሬ አዳኙ ውሾቼን እፈልጋለሁ አላት፡፡ እመቤታችንም ውሾች ምን ያደርጉልሃል አለችው፡፡ አውሬ አዳኙ ውሾች አውሬዎችን ይገሉልኛል፡፡ የአውሬዎችን ሥጋ እበላለሁ ቆዳቸውንም እሸጣለሁ አላት፡፡ እመቤታችንም ዛሬ ከምታድናቸው አውሬዎች የበለጠ ነገር አግኝተዋል የእግዚአብሔርን መሲሕ አይተሃልና ወደ ሀገርህ ግባ እኔ በዚህ ጫካ መኖሬን ለማንም አትንገር አለችው፡፡ ውሾቹንም ወደ ጌታችሁ ሂዱ አለቻቸው፡፡ ውሾቹም ለፈጣሪያቸው እና ለእመቤታችን ከሰገዱ በኋላ ወደ ጌታቸው ሄዱ፡፡ አውሬ አዳኙም እያደነቀ ሄደ፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ግን በጫካው ውስጥ ነበረች፡፡ በኤልያስ ዘመን ጣዖት አምላኪዋ ኤልዛቤል ነቢያትን ካህናትን ባስገደለቻቸው ጊዜ እግዚአብሔርን ከኤልዛቤል ዓይን የሠወራቸው በጫካ የሚኖሩ ጻድቃን እየመጡ ከእመቤታችን ይባረኩ ነበር፡፡
እመቤታችንና ንጉስ ደማትያኖስ
አውሬ አዳኙ ከሰባት ቀን በኋላ ደማትያኖስ ለተባለው ንጉሥ ያየውን ሁሉ ነገረው፡፡ ደማትያኖስም አውሬ አዳኙ የነገረው እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ አሥር የቤተመንግስት ሰዎችን ከአውሬ አዳኙ ጋር ላከ፡፡ የተላኩት ሰዎች በደረሱ ጊዜ እመቤታችንን ከልጅዋ ጋር አገኝዋት፡፡ እመቤታችን ግን ለማንም አትንገር ያለችውን ስለተናገረ አውሬ አዳኙን በቁጣ ተመለከተችው፡፡ አውሬ አዳኙም የጨው ድንጋይ ሆነ ( ማቴ. 8፡4 ) ። የሎጥ ሚስት ታሪክ በአውሬ አዳኙ ተደግሞአል፡፡ እግዚአብሔር ሎጥን በእሳት ከምትጋየው ከሰዶም ባወጣው ጊዜ ወደኋላህ አትመልከት ብሎት ነበር፡፡ የሎጥ ሚስት ግን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በመተላለፍ ወደ ኋላዋ ወደ ሰዶም ተመለከተችና የጨው ሐውልት ሆነች ( ዘፍ. 19፡26 ) ። ከቤተ መንግስት
የተላኩት ሰዎችም እመቤታችን ያደረገችውን ተአምር አይተው በጣም ደነገጡ፡፡ እመቤታችን እኔም እንደ እናንተ ሰው ነኝና አትፈሩ ብላ አረጋጋቻቸው፡፡ መልእክተኞችም ንጉሡ ደማትያኖስ እንደላካቸው ነገርዋት፡፡ ከዚህ በኋላ ወደ ቤታቸው ተመልሰው እመቤታችንን ከልጅዋ ጋር እንደአገኝዋት እና አውሬ አዳኙ የጨው ድንጋይ እንደሆነ ለደማትያኖስ ነገሩት፡፡ በማግስቱ ደማትያኖስ ብዙ ሠራዊት አስከትሎ ወደ እመቤታችን ሄደ፡፡ ብዙ ሠራዊቱን ከተራራው ስር ትቶ ከሰባቱ ጋር እመቤታችን ወደ አለችበት ጫካ ገባ፡፡ እመቤታችን እንደ አጥቢያ ኮከብ ስታበራ አገኛት፡፡ ንጉሡ ደማትያኖስ ለእመቤታችን ከሰገደ በኋላ አንቺ ከማን ወገን ነሽ ከየት ሀገርስ የመጣሽ ነሽ ብሎ ጠየቃት፡፡ እመቤታችንም እኔ እስራኤላዊት ነኝ፡፡ የይሁዳ ክፍል ከምትሆን ከቤተልሔም ነው የመጣሁት አለችው፡፡ እመቤታችንም ሄሮድስን ፈርቼ ነው አለችው፡፡ ንጉሡም ሄሮድስ ለምን ይጠላሻል አላት፡፡ እመቤታችንም እንዲህ አለችው፡፡ ሁለንተናው እሳት የሆነ ግሩም መልአክ ገብርኤል መጥቶ ፀጋን የተመላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ እነሆ ወንድ ልጅ ትወልጃለሽና ስሙንም አማኑኤል ትይዋለሽ አለኝ፡፡ እንደነገረኝ
ይህን ሕፃን በድንግልና ጸንሼ በድንግልና ወለድኩት፡፡ ከተወለደ በኋላ ሰብአሰገል የተወለደው የእስራኤል ንጉሥ የት ነው እያሉ መጡ፡፡ ይህን ነገር ሄሮድስ ሰማ፡፡ ስለዚህ እኔን እና ሕፃኑን ሊገድለን ይፈልጋል፡፡ ከዚህ በፊት በዚህ ቦታ አባቴና እናቴ ነበሩ እኔም የተወለድኩት በዚህ በደብረ ሊባኖስ /በሊባኖስ ተራራ/ ነው አለችው፡፡ ደማትያኖስም የአባትሽ እና የእናትሽ ስም ማን ይባላል ? አላት፡፡ እመቤታችንም አባቴ ኢያቄም እናቴ ሐና ይባላሉ አለችው፡፡ ደማትያኖስም እነዚህን ሰዎች አውቃቸዋለሁ አላት፡፡ ደማትያኖስ ብዙ ሠራዊት ያለው ኃያል ንጉሥ ስለሆነ ከዚህ በኋላ አሥር ነገሥታት እንኳ ቢገቡ አንቺን ማግኘት አይቻላቸውም አትፍሪ አላት፡፡ ወደ ኃላውም በተመለሰ ጊዜ የጨው ድንጋይ የሆነውን ሰው አየውና ይህ ሰው ለምን የጨው ድንጋይ ሆነ አላት፡፡ እመቤታችንም በኃጢአት ነው አለችው፡፡ ከዚህ በኋላ እመቤታችን ወደ እግዚአብሔር ጸለየች፡፡ የጨው ድንጋይ የሆነውን ሰው አስነሳችውና ለማንም አትንገር ብዬህ ነበር ለምን ነገርህ አለችው፡፡ የጨው ድንጋይ የሆነው ሰው ኃጢአቱን አምኖ ይቅርታ ጠየቀ፡፡ የተነገረንን ምስጢር እንጠብቅ፡፡ ብዙ ጊዜ ኃጢአት የሚፈትነን በንግግራችን ነው፡፡ ንጉሡ ግን ይህን ተአምር ባየ ጊዜ እጅግ ደነገጠ፡፡ እመቤታችን በቀኝ እጅዋ ይዛ አትፍራ አለችው፡፡ እመቤታችን ስትይዘው ድንጋጤውና ፍርሃቱ ለቀ ቀው፡፡ ከዚህ በኋላ ንጉሡ ለእመቤታችን ሰገደላትና አባቴና እናቴ ስማቸውን ሲጠርዋቸው በልጅነቴ የምሰማቸው ሚካኤልና ገብርኤል ሩፋኤል ከሚባሉት አንዱ አንቺ ነሽ አላት ከማድነቁ የተነሣ፡፡ እመቤታችንም እኔ የእነሱ የጌታቸው ባሪያ ነኝ አለችው፡፡ ንጉሡም ብዙ ገጸ በረከት ገንዘብ ይዞ እመቤታችንን ተቀበይኝ አላት፡፡ እመቤታችን ግን ምንም ስደተኛ ብትሆንም አልተቀበለችውም፡፡ ለድሆች ስጣቸው በሰማይ መዝገብ ታገኛለህ አለችው፡፡ ከዚህ በኋላ ንጉሡ ወደ ቤቱ ተመለሰ፡፡ እመቤታችንም በደብረ ሊባኖስ ሦስት ወር ያህል ተቀመጠች፡፡ ከዚህ በኋላ ሄሮድስ ሊባኖስ በተባለው ተራራ እነዮሴፍ መኖራቸውን ሰምቶ በሠራዊት አስከብቦ ሊይዛቸው ሞከረ፡፡
ጊጋር የሶርያ ገዥ /ጊጋር መስፍነ ሶርያ/
አንድ የሶርያ
ገዥ /መስፍነ ሶርያ/ ጊጋር የተባለ ሰው የሄሮድስን እኩይ ምክር ሰለሰማ ወደ እመቤታችን መልእክተኞችን ላከ፡፡ ጊጋር የላካቸው ሰዎች በፈረስ እየጋለቡ በፍጥነት ደርሰው የሊባኖስን ተራራ ሄሮድስ በሠራዊት ሊያስከብበው ነውና ሊባኖስን ለቃችሁ ሽሹ አሏቸው፡፡ መልአኩም መጥቶ ከሊባኖስ ውጡ አላቸው፡፡ እመቤታችን ጌታችን ዮሴፍና ሰሎሜ ደብረ ሊባኖስን ለቀው ሄዱ፡፡ ከዚህ በኋላ ጊጋር መልእክተኞችን ልኮ እነ ዮሴፍን ከደብረ ሊባኖስ እንዳስወጣቸው ሄሮድስ ሰማ፡፡ የምንፈልጋቸውን ሰዎች ያሸሽህብኝ አንተ ነህ በማለት ጊጋርን ተጣላው፡፡ ሄሮድስ ወታደሮቹን ልኮ የሶርያ ገዢ ጊጋርን አስያዘና በሰይፍ አስቆረጠው፡፡ ጊጋርም በሰማዕትነት ሞተ ። ነሐሴ 16 ቀን በሚነበበው ስንክሳር ይህን የጊጋርን ታሪክ እናገኛለን፡፡
መ . ደብረ
ቶና ፦ ከዚህ በኋላ እመቤታችን ዮሴፍና ሰሎሜ ወደ ደብረ ቶና ሄዱ፡፡ በደብረ ቶና የይሁዳ አገሮች ይታያሉ፡፡ እመቤታችን ብዙ መንገድ በመሄድ ደክማ ነበርና አልሲስ ከተባለ ዛፍ ስር ተቀመጠች፡፡ በጣም ስለደከማት ከዛፉ ስር ተኛች፡፡ መላእክት ነፍሷን በራዕይ ወደ ጽርሐ አርያም ወሰዷት፡፡ የእሳት መጋረጃዎች በቀኝና በግራ በግራ ተከፈቱ፡፡ ልጅዋ ኢየሱስ ክርሰቶስ የሰው ዓይን ያላየውን የሰው ጆሮ ያልሰማውን በሰው ልቡና ያልታሰበውን በመንግሥተ ሰማያት የሚገኘውን ብዙ ምሥጢር ነገራት፡፡ የሰው ልጆች ለዘለዓለም የሚወርሱትን እጅግ ደስ የሚያሰኘውን ዓለም አየች፡፡ ከዚህ በኋላ ነፍሷ ወደ ሥጋዋ ተመለሰች፡፡ ከእንቅልፏ በነቃች ጊዜ ልጅዋን ለምን ወደዚህ የመከራ ዓለም መለስኸኝ አለችው፡፡ ሕፃን ልጇን ኢየሱስ ክርስቶስም እንዲህ አላት ያለመከራ ፀጋ አይገኝም፡፡ በዚህ ዓለም በእኔ ስም መከራ የተቀበሉ ሁሉ በወዲያኛው ዓለም ደስ ይላቸዋል፡፡ አንቺም በወዲያኛው ዓለም ደስ ይልሽ ዘንድ በዚህ ዓለም በመከራ ውስጥ ማለፍ ይኖርብሻል፡፡ ከዚህ በኋላ ከደብረ ቶና ወጥተው ወደ ሲዶና ሄዱ፡፡ ከሲዶናም ወጥተው ወደ ደብረ ዘይት ሄዱ፡፡
ሠ . ቤተልሔም ፦ ከደብረ ዘይትም ወጥተው ወደ ቤተልሔም ሄዱ፡፡ በቤተልሔም ሳሉ ከሄሮድስ ሠራዊት አንዱ አያቸው፡፡ በፈረስ እየጋለበ በፍጥነት ከሄሮድስ ቤተመንግሥት ደርሶ ማርያም እና ዮሴፍ ሰሎሜም በቤተልሔም አሉ ብሎ ለሄሮድስ ነገረው፡፡ ሄሮድስ ይህን ዜና ያመጣለትን ሰው እንዲህ አለው የነገረኸኝ ነገር እውነት ቢሆን
የመንግሥቴን እኩሌታ እስጥሃለሁ እውነት ባይሆን ግን አንተን እገልሃለሁ፡፡ ብዙ ጊዜ እነ ዮሴፍ በዚህ ቦታ አሉ እየተባለ ተራራውን ሸለቆውን ዋሻውን በሠራዊት እያስከበበ ቢፈልግ ሳያገኛቸው ቀርቷል፡፡ ፈልጎ አለማግኘቱ በብስጭት ላይ ብስጭት ስለጨመረበት አሁን ግን ፈልጎ ባያገኛቸው የጠቆመውን ሰው ለመግደል ቆርጦ ተነሣ፡፡ በዚያች ሌሊት ገብርኤል ወርዶ ዮሴፍን እንዲህ አለው፡፡ በነቢይ ልጄን ከግብፅ ጠራሁት የተባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ይፈጸም ዘንድ ወደ ግብፅ ሽሽ (ት.ሆሴዕ . 11.1 ) ፡፡ እነ ዮሴፍም በዚች ሌሊት ቤተልሔምን ለቀው ወጡ፡፡ በነጋ ጊዜ ሄሮድስ ቤተልሔምን አስከበባት፡፡ እመቤታችን በታየችበት አካባቢ የተገኙትን ሰዎች ወንዶችንም ሴቶችንም አስገደለ፡፡ ሰዎችን ጨርሶ ከዶሮ እስከ ውሻ ያሉ እንስሳትን ሁሉ አስገደለ፡፡ ሰማዩም እንደደም ቀይ ሆነ ደም መሰለ፡፡
ሄሮድስ ላስገደላቸው ሰዎች ከሰማይ አክሊል ወረደላቸው፡፡ የአክሊሉን መውረድ የተመለከቱ የሄሮድስ ሠራዊትም በማርያም ልጅ በሕጻኑ በኢየሱስ ክርስቶስ
እናምናለን
አሉ፡፡ የሥልጣን ፍቅር ውስጡን ያጨለመው ሄሮድስ ግን በድንግል ማርያም ልጅ ያመኑትን ወታደሮች በሰይፍ አስቆራረጣቸው፡፡ ማርያምን በቤተልሔም አየኋት ብሎ የነገረውን ወታደርም በሰይፍ አስቆራረጠው፡፡ የሰዎችን ደም በማፍሰስ የሚረካ እየመሰለው የደም ማፍሰስ ሱስ ያዘው፡፡ ዛሬም ምድራችን የምስኪኖቹን ደም በማፍሠስ ወንበር በሚያደላድሉት የስልጣን ዘመን በሚያራዝሙ ግፈኞች ተሞልታለች፡፡ ይቆይ ይሆናል እንጂ ሁሉም
የዘራውን እንደሚያጭድ ይህ ታሪክ ያስረዳልና፡፡ ከዚህ በኋላ ሄሮድስ በፈረስ ላይ ሆኖ ሲሄድ የእግዚአብሔር መልአክ ወርዶ የፈረሱን አፍንጫ መታው፡፡ ፈረሱ
ወደ ላይ ሲዘል በላይ የነበረ ሄሮድስ በታች ሆነ በታች የነበረ ፈረስም በላይ ሆነ፡፡ ሄሮድስ ተንኮታኮተ፡፡ አጥንቱ ተሰባበረ ሥጋው ተቆራረጠ፡፡ የብዙዎችን ደም ባፈሰሰበት መሬት ላይ የእርሱም ደም ፈሰሰ፡፡ ሠራዊቱ ተሸክመው ከቤቱ አደረሱት፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለመ ዓለም አሜን ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡አነሳስቶ ያስጀመረኝ አስጀምሮ ያስጨረሰኝ የቅዱሳን አባቶቻችን አምላክ ይክበር ይመስገን ፡፡አሜን !!!!!!
ክፍል ሦስት ይቀጥላል … … … … … … ይቆየን::
ጥቅምት
09 /2005 ዓ/ም
source: http://dhkidusraguel.org/
No comments:
Post a Comment