ምንኵስና በኢትዮጵያ
ከ4ኛው መ/ክ/ዘ በፊት
ሥርዓተ ምንኵስና ወደ ሀገራችን የገባው በኢትዮጵያ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ በአባ ጳኩሚስ ዘመን ቢሆንም የብሕትውና ኑሮ ግን በሀገራችን ከዚያም ቀድሞ እንደነበረ የሚጠቁሙ አንዳንድ መረጃዎች አሉ፡፡
አባ አሞንዮስ፡- ሥርዓተ ምንኵስና ወደ ኢትዮጵያ ከመግባቱ በፊት አሞንዮስ የተባሉ ባሕታዊ በተንቤን ቆላ ደብረ አንሣ በተባለው በረሃ በጾም በጸሎት ተወስነው ይኖሩ ነበር፡፡
አባ ዮሐኒ፡- በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መግቢያ ላይ በትግራይ ተንቤን አውራጃ በሀገረ ሰላም ቀበሌ ተወለዱ፡፡ በዚያን ዘመን ሥርዓተ ምንኵስና ወደ ኢትዮጵያ ባይገባም አበው በምናኔ በበረሃ ይኖሩ ነበር፡፡ የአባ ዮሐኒ ቤተሰቦች ድሆች ስለነበሩ አባ አሞንዮስ ወስደው አሳደጓቸው፡፡ ካደጉ በኋላም ከአባ አሞንዮስ ተለይተው ወደ በረሃ ለብቻቸው በመውረድ በተጋድሎ ሲኖሩ ከቆዩ በኋላ በተወለዱ በ3ዐ ዓመታቸው ኀዳር 5 ቀን እግዚአብሔር ወደ ብሔረ ሕያዋን በመላእክት እጅ እንደወሰዳቸው ገድለ አባ ዮሐኒ ይገልጣል፡፡