Wednesday, February 6, 2013

የብሕትውና(የምንኩስና) ኑሮ - ክፍል 1


1.አጀማመር
1.1 በሕገ ልቡና

የብሕትውና ኑሮ የተጀመረው ከሰው ልጅ ወደዚህች ምድር መምጣት አንሥቶ ነው፡፡ ደቂቀ ሴት ከቃየል ልጆች ኑሮና ግብር ተለይተው በደብር ቅዱስ በንጽሕና በቅድስና ይኖሩ እንደነበር ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል( ዘፍ.6÷1-3 ሄኖክ 2÷1-2)
አባታችን ሄኖክም በዘመኑ ከነበሩት ግብረ ሰዶማውያን ርቆ፣ ሰዎችን ለጥፋት ውኃ ከዳረገው ኃጢአት ተለይቶ፣ ንጹሕ እግዚአብሔር ንጽሕናን ይሻል በማለት በሕገ ልቡና ተመርቶ በእግረ ገነት ለሰባት ዓመታት በብሕትውና ከኖረ በኋላ በልዑል እግዚአብሔር ፈቃድ ከአካለ ሥጋ ወደ ብሔረ ሕያዋን መነጠቁን መጽሐፈ ሄኖክ ያስረዳል፡፡ የመልከ ጼዴቅም የኑሮ ሥርዓት ይህንኑ የባሕታውያን ሕይወት የተከተለ ነበር( ዘፍ.14÷17-24)፡፡


1.2 በሕገ ኦሪት

ይህ የብሕትውና ኑሮ ከሕገ ልቡና ወደ ሕገ ኦሪት ተላልፎ አባታችን ኤልያስን የመሰለ መናኝ ለማስገኘት በቅቷል፡፡ የኤልያስንም ሕይወት ደቀ መዝሙሩ ኤልሳዕ ተረክቦታል፡፡
ኤልያስ ደቀመዝሙሩን ኤልሳዕን ተሰናብቶ በእሳት ሠረገላ ሲያርግ

1.3 በዘመነ ሐዲስ

መጥምቁ ዮሐንስ

ወደ ዘመነ ሐዲስም ስንመጣ የዮሐንስ መጥምቁ ሕይወት የዚህ ተከታይ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ 3 ዓመት ወጣት ሆኖ እስኪገለጥ ድረስ በጨው ባሕር አጠገብ በሚገኘው የቁምራን ገዳም የኖረ ሲሆን በኋላም የግመል ፀጉር ለብሶ የበረሃ አንበጣ እየበላ በሄኖም ሸለቆ በመኖር በዮርዳኖስ ወንዝ ሕዝቡን በንስሐ ጥምቀት ያጠምቃቸው ነበር (ማር.1÷1-11)፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሐዲስ ኪዳኑ ባሕታዊ ስለ መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ‹‹እርሱ የሚነድና የሚያበራ መብራት ነበረ›› በማለት መስክሮለታል ( ዮሐ.5÷35)፡፡

የቁምራን ገዳም

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገዳመ ቆሮንጦስ
መጥምቁ ዮሐንስ
ልዑለ ባሕርይ ኢየሱስ ክርስቶስም 3 ዘመኑ በፈለገ ዮርዳኖስ በዕደ ዮሐንስ ከተጠመቀ በኋላ ወደ ቆሮንቶስ ገዳም በመግባት የምናኔን እና የብሕትውናን ኑሮ አጽንቶ አስተምሮናል፡፡ ዛሬ አሠረ ፍኖቱን የተከተሉት አባቶቻችን እንደሚያደርጉት ሁሉ በነዚያ 4 ቀናት ወደ በረሃ ወርዶ ከአራዊት ጋር ኖረ ( ማር.1÷13)፡፡ ከዲያብሎስ ተፈትኖ ድል በማድረግም ድል የምናደርግበትን ኃይል ሰጠን፡፡ መድኃኒታችን ወዶ ፈቅዶ አርአያ ምሳሌ ይሆነን ዘንድ በገዳመ ቆሮንቶስ ዲያብሎስን ድል ባደረገው ጊዜ መላእክት አገለገሉት፡፡ በዚህም እኛ እሱን ብንመስለው ዲያብሎስንም ድል ብንነሣው ኑሮአችን ከመላእክት ጋር እንደሚሆን አስተማረን(ማር.1÷13 ማቴ 1÷11)፡፡

በአንድ ወቅት ደቀ መዛሙርቱ መድኃኒታችንን ‹‹መጋባት አይጠቅምምን›› ብለው በጠየቁት ጊዜ እንዲህ በሚል ቃል አስተምሯቸው ነበር፡፡ «ይህ ነገር ለተሰጣቸው ነው እንጂ ለሁሉ አይደለም፡፡ በእናት ማኅፀን ጃንደረቦች ሆነው የተወለዱ አሉ፡፡ ስለ መንግሥተ ሰማያትም ራሳቸውን የሰለቡ ጃንደረቦች አሉ፡፡ ሊቀበለው የሚችል ይቀበለው» (ማቴ.19÷10-10)፡፡
ስለ መንግሥተ ሰማያት ራሳቸውን የሰለቡ ጃንደረቦች የተባሉት ሁሉ እያላቸው፣ ሁሉን ማድረግ እየቻሉ ነገር ግን ይህንን ዓለም ንቀው መድኃኒታቸውን መስለው፣ ድምፀ አራዊትን ግርማ ሌሊትን ታግሠው፣ የእሾህ አክሊሉ ምሳሌ የሆነውን ቆብ ደፍተው፣ ምድረ በዳ ወርደው ከአራዊት ጋር እየኖሩ (ማር.1÷13) ከዲያብሎስ ጋር የሚጋደሉት የሃይማኖት አርበኞች ናቸው፡
ጃንደረብነት ሦስት ዓይነት መሆኑን ጌታችን ገልጦልናል፡፡ በተወለዱ ጊዜ በችግር ምክንያት ጃንደረቦች (ስልቦች) የሆኑ አሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በአገራችን አንዳንድ ቦታዎች፣ በመካከለኛውና ደቡባዊው አፍሪካ በአብዛኛው እንደሚታወቀው የማኮላሸት ተግባር የሚፈፀምባቸው አሉ፡፡ ሳይፈልጉ በሰዎች አስገዳጅነት የሚሰለቡ እንዳሉ ሁሉ ሥልጣን ሽተው ማዕረግ ፈልገው ጃንደረባ የሚሆኑም አሉ፡፡

የቁምራን ገዳም
ሦስተኛዎቹ ግን «ሁሉን ትተህ ተከተለኝ» ያለውን ቃል ሰምተው፣ ያላቸውን ሁሉ ለመንግሥተ ሰማያት ጌታ ለቅዱስ እግዚአብሔር ሲሉ ርግፍ አድርገው የተከተሉት፤ ከዚህ ዓለም ግብር ርቀው የዘወትር ሥራቸው ጸሎትና መዝሙር፤ ቅዳሴና ስግደት የሆነ ምድራውያን መላእክት ናቸው፡፡ ጌታችን ይህንን ጉዳይ ለሀብታሙ ጎልማሳ ጥያቄ በሰጠው መልስ ላይ አጠናክሮ አብራርቶ አስተምሮናል፡፡

ባለጸጋው ‹‹የዘላለምን ሕይወት እወርስ ዘንድ ምን ላድርግ?›› ብሎ በጠየቀው ጊዜ ጌታ «ትእዛዛትን ጠብቅ» በማለት የወጣንያንን ትምህርት አስተማረው፡፡ ጎልማሳው ግን ‹‹ይህን ሁሉማ ከሕፃንነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ ደግሞስ የሚጐድለኝ ምንድነው?›› በማለት ጠለቅ ብሎ ጠየቀ፡፡ በዚህ ጊዜ ‹‹ፍጹም ልትሆን ብትወድ ሂድና ያለህን ሽጠህ ለድኾች ስጥና ተከተለኝ›› ሲል አስተማረው፡፡ ጐልማሳው ግን ይህን መሸከም አቅቶት ለንብረቱ ሳስቶ እያዘነ ሄደ (ማቴ.1916-212)፡፡ ለዚህ ነበር ጌታችን ‹‹ሊቀበለው የሚችል ይቀበለው›› በማለት ያስተማረው፡፡

አባቶቻችን መነኮሳትና ባሕታውያን በረሃ የወረዱት፣ሁሉን ሽጠው፣ለድኾች መጽውተው የመነኑት ይህንን ጌታ ለፍፁማን የሰጠውን ትምህርት መሠረት አድርገው ነው፡፡

1.4 በመጀመርያዎቹ  ክርስቲያኖች

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገዳመ ቆሮንጦስ
ይህ ኑሮ በመጀመሪያው //ዘመን በነበሩ ክርስቲያኖች ዘንድ የተለመደ እንደነበር ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለዕብራውያን በላከው መልእክቱ ፍንጭ ሰጥቶናል፡፡ ‹‹ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፡፡ ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፣ በዋሻና በምድር ጉድጓድ (ግበበ ምድር) ተቅበዘበዙ›› ሲል (ዕብ 11÷37)፡፡ ዛሬም በየበረሃው የፍየል ሌጦ ለብሰው አበው የሚጋደሉት የእነዚህን ክርስቲያኖች አርአያ አንሥተው ነው፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የትዳርን ነገር በተናገረበት አንቀጹ «ሰው ሁሉ እንደ እኔ ሊሆን እወዳለሁ፡፡ ነገር ግን እያንዳንዱ ከእግዚአብሔር ለራሱ የጸጋ ስጦታ አለው፡፡ አንዱ እንደዚህ ሁለተኛውም እንደዚያ» በማለት የክርስቲያኖች የኑሮ ሥርዓት ሁለት ዓይነት መሆኑን አስተምሮናል (1ቆሮ.7÷7)፡፡ እነዚህም የትዳር እና የብሕትውና (ምንኩስና) ሕይወት ናቸው፡፡ የብሕትውና (ምንኩስና) ኑሮ ከጥንት ከዘመነ አበው ጀምሮ የመጣ፣ ጌታችን ያጸናው፣ ሐዋርያት የሰበኩት መጽሐፍ ቅዱስዊ ትምህርት እንጂ «ብዙ ተባዙ» ከሚለው አንቀጽ ጋር የሚጋጭ ሰው ሠራሽ ሥርዓት አይደለም፡፡
2. የሥርዓተ ምንኩስና ታሪክ
ይቀጥላል - ይቆየን

ወስብሐት ለእግዚአብሔር


ዋቢ
1.    ትንሣኤ .99/1978
2.    ገድለ አባ ሊባኖስ
3.    ገድለ አባ ዮሐንስ
4.    ዜና መንዝ
5.    የአንኰበር መሳፍንት የታሪክ መጽሐፍ
6.    ትንሣኤ .11/79
7.    ትንሣኤ .22/80
8.    Conti Rossini, steria PL.XLIV
9.    ሉሌ መላኩ፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ . 1986
10. አባ ጎርጎርዮስ፤ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ
11. አባ ጎርጎርዮስ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪ


ሐመር መጽሔት
ምንጭ: http://www.melakuezezew.info/

No comments:

Post a Comment