ሠ-በማን ስም ልንጠመቅ ይገባል
ሐዋርያዊትና ኦርቶዶክሳዊት
ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰዎች የእግዚአብሔርን ልጆች ይሆኑ ዘንድ በሥላሴ ስም ታጠምቃለች፡፡ ይህም ጌታ ራሱ ለሐዋርያቱ ‹‹ሂዱና
አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም ያጠመቃችኋቸው፡፡›› (ማቴ. 28÷19) ብሎ የሰጠውን አምላካዊ ቃል
መሠረት በማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ ቤተክርስቲያን በክርስቶስ ደም ከተመሠረተችበት ዘመን አንስቶ በሥላሴ (በአብ፣ በወልድ፣
በመንፈስ ቅዱስ) ስም መጠመቅ የድኀነት በር ቁልፍ መሆኑን ስታስተምርና ተግባራዊ ስታደርግም ኖራለች፡፡
ይህንን
የወንጌል ቃል የሚያጣምሙ መናፍቃን በኢየሱስ ስም ብቻ መጠመቅ አለብን እንጂ በአብ፣ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም መጠመቅ
የለብንም ይላሉ፡፡ ለዚህም ማስረጃ አድርገው ለማቅረብ የሚሞክሩት የሐዋርያው የቅዱስ ጴጥሮስን አነጋገር ነው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ
በበዓለ ሃምሳ ከየሃገሩ ለተሰበሰቡት አይሁድ የምሥራቹን ቃል ድምጹን ከፍ አድርጐ ባሰማቸው ጊዜ ልባቸው ተነካ፡፡ ስለዚህም
‹‹ምን እናድርግ›› ብለው ሊያደርጉት የሚገባቸውን እንዲነግራቸው ጠየቁት፡፡ እርሱም ‹‹ንስሐ ግቡ፣ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ
ክርስቶስ ስም ተጠመቁ አላቸው›› (የሐዋ ሥራ 2÷38)፡፡
2006 ዓ.ም የጥምቀት በዓል አከባበር በጎንደር |
ሊያጠምቁ
የሚገባቸው ሥልጣነ ክህነት ያላቸው ሰዎች ማለትም ቄስ ወይም ጳጳስ መሆን እንዳለባቸው የቤተክርስቲያን ቀኖና ያዛል፡፡ ግን
‹‹በክርስቶስ ያመነ ሁሉ ካህን ነውና ሊያጠምቅ ሥልጣን አለው›› የሚለው አመለካከት የተሳሳተ ነው፡፡ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን
መፈጸም የሚገባቸው ሥልጣነ ክህነት የተሰጣቸው ብቻ እንጂ ሥልጣነ ክህነት የሌላቸው ምእመናን ሊሆኑ አይገባም፡፡
አይሆኑምም፡፡
ሥልጣነ
ክህነት በሌለው ሰው የተደረገ ጥምቀት አማናዊ ጥምቀት አይደለም፡፡ ከሥላሴም ልጅነትን
አያሰጥም፡፡
ምክንያቱም ጌታ ‹‹አጥምቁ›› ብሎ የላካቸው ከሌላው ሁሉ መርጦ የሾማቸውን ሐዋርያቱን እንጂ ያመኑትን ሁሉ አይደለም
(ማቴ.28÷19፤ ማር.16 ÷16)፡፡
ሐዋርያት
ሥልጣነ ክህነትን ከጌታ መቀበላቸው በወንጌል ተመዝግቧል፡፡ #ይህንንም ብሎ እፍ አለባቸውና መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ$ ይላል
(ዮሐ. 2ዐ÷22)፡፡ ይህም ሥልጣነ ክህነት ለመሆኑ ማረጋገጫችን ‹‹ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፡፡
የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል አላቸው›› (ዮሐ.20÷23) በማለት ልጅነትን ሳይሆን ሥልጣነ ክህነትን እንደሰጣቸው ቅዱስ ወንጌል
ያስተምረናል፡፡ ምክንያቱም ልጅነት ኃጢአት ሊያስተሠርይ፣ ከኃጢአት ሊፈታ፣ ሊያስር፣ አይችልምና ነው፡፡ ሥልጣነ ክህነት ግን
ኃጢአትን ሊያስተሠርይ፣ ከኃጢአት ሊፈታና ሊያስር ይችላል፡፡
ስለዚህ
ለማጥመቅም ሆነ ሌሎችንም ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን ለመፈጸም ሥልጣኑ ያላቸው ካህናት እንጂ ሁሉም ምእመን አይደለም፡፡ በዚህም
የተነሣ ቤተክርስቲያን በምእመናን የሚፈጸመውን ጥምቀት እውነተኛ ጥምቀት አድርጋ
አትቀበለውም፡፡
ሰ-ጥምቀት
አንዲት ናት
ጥምቀት
የማትደገም፣ የማትከለስ አንዲት ናት፡፡ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ልጅነትን የምናገኝባት ጥምቀት የማትደገምና የማትከለስ አንዲት
ብቻ መሆንዋን ሲያስተምር ‹‹አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት…አለ›› ብሏል (ኤፌ.4÷5)፡፡ ሃይማኖታቸው የቀና
318ቱ ሊቃውንትም ‹‹ኃጢአትን በምታስተሠርይ በአንዲት ጥምቀት እናምናለን፡፡››
ብለው
አስተምረዋል፡፡ በዚህ የተነሣ ኣርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አንድ ጊዜ ያጠመቀችውን ድጋሚ አታጠምቅም፡፡
ነገር ግን አማናዊቷን ጥምቀት ቀድሞም አልፈጸሙምና ከቤተ ክርስቲያናችን ውጪ በሌላ
በማናቸውም ሁኔታ ‹‹ተጠምቀን ነበር›› የሚሉትን ወደ ቤተ ክርስቲያናችን ሲቀርቡ በሥርዓቷ መሠረት አስተምራ አሳምና
ታጠምቃቸዋለች፡፡
በሌላ
መልኩ ደግሞ ቀድሞ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ተጠምቆ ኋላ ግን ወደ ሌላ እምነት ቢገባ ተናዞ (ንስሐ ገብቶ)
በማየ ጸሎት (መጽሐፈ ቄደር ተደግሞለት) ይረጫል እንጂ ድጋሚ አይጠመቅም፡፡ ቄደር የንስሐ እጽበት
ነው፡፡ ያደፈ ልብስ እንደሚታጠብ ሁሉ ይህም ሰው ንጽሕት እምነቱን አሳድፏልና ከኃጢአቱ ለመታጠቡ ምልክት ይሆን
ዘንድ በማየ ጸሎት ይታጠባል፡፡
ጥምቀት የማይደገምበት
ምክንያት
ሀ.
ጥምቀት ከእግዚአብሔር ዳግም የምንወለድበት ምሥጢር ነው፡፡
የሥጋን
ልደት ስንመለከት ሰው ከእናቱ ማኀፀን የሚወጣው (የሚወለደው) አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ እንዲሁም እግዚአብሔርም በእውነት አንድ
ጊዜ ወልዶናል፡፡ ስለዚህ አንድ ጊዜ ብቻ እንጠመቃለን፡፡
ለ.
ጥምቀት ከጌታ ሞትና ትንሣኤ ተሳታፊ የምንሆንበት ምሥጢር ነው፡፡
‹‹በጥምቀትም
ከእርሱ ጋር ተቀብራችሁ በጥምቀትም ደግሞ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አሠራር በማመናችሁ ከእርሱ ጋር ተነሣችሁ››
(ቈላ.2÷12)፡፡ ጌታ የሞተውና የተነሣው አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ እንዲሁም እኛ ከእርሱ ጋር የምንቀበረውና የምነሣው አንድ ጊዜ
ብቻ ነው፡፡
1. ጌታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀው በውኃ ነው እኛም እርሱን አብነት በማድረግ በውኃ
ልንጠመቅ ይገባናል (ማቴ.3÷13-16)፡፡
ልንጠመቅ ይገባናል (ማቴ.3÷13-16)፡፡
2. ጌታችን
ለኒቆዲሞስ ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት
ሊገባ አይችልም›› ስላለ እኛም የጌታን ትእዛዝ ለመፈጸም በውኃ እንጠመቃለን
(ዮሐ.3÷5)፡፡
3. ሐዋርያት
ከጌታ በተማሩት መሠረት ያጠመቁት በውኃ ነው፡፡ ጴጥሮስም መልሶ ‹‹እነዚህ እንደ እኛ ደግሞ መንፈስ ቅዱስን
የተቀበሉ እንዳይጠመቁ ውኃን ይከለክላቸው ዘንድ የሚችል ማን ነው? አለ›› (የሐዋ.10÷46ና 47)፡፡
ፊልጶስና ጃንደረባው ሁለቱም ወደ ውኃ
ወረዱ አጠመቃቸውም (የሐዋ.8÷28)፡፡
ወረዱ አጠመቃቸውም (የሐዋ.8÷28)፡፡
4. ውኃ
የሰውነትን እድፍ እንደሚያጠራ ሁሉ እንዲሁም ጥምቀት የነፍስን እድፍ ያስወግዳል
ያነጻል፡፡
5. ውኃ
መልክን ያሳያል እኛም በውኃ በመጠመቅ የሥላሴን ምሥጢር በዓይነ ኅሊናችን እናያለን፡፡
6. በጥንተ
ፍጥረት መንፈስ እግዚአብሔር በውኃ ላይ ረብቦ እንደነብር መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል ይገልጻል፡- ‹‹የእግዚአብሔርም
መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር›› (ዘፍ.1÷2)፡፡ እንዲሁም በውኃ፣ በሕይወትና በመንፈስ ያለውን ግንኚነት ማስተዋል ይገባል፡፡
ልዑለ ባሕርይ ጌታ በነቢዩ በኤርምያስ አንደበት እንዲህ ሲል ተናግራል ‹‹ሕዝቤ ሁለቱን ክፉ ነገሮች አድርገዋልና እኔን የሕያውን
ውኃ ምንጭ ትተውኛል…›› (ኤር.7÷13)፡፡
ጌታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ትምህርቱ በእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል ብሎ አስተምሯል
(ዮሐ.7÷39)፡፡ ለሳምራዊቷ ሴትም ‹‹እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘላለም አይጠማም፡፡ እኔ የምሰጠው ውኃ በእርሱ
ውስጥ ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል እንጂ አላት›› (ዮሐ.4÷14)፡፡
ከላይ
በተገለጸው መሠረት ውኃ የሕይወት ምልክት ነው፡፡ በተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እንደምናነበው ውኃ ለሰማያዊው መንግሥት፣
ለዘላለም ሕይወት ምሳሌ ሆኖ ተገልጿል፡፡ ‹‹እርሱም በውኃ ፈሳሾች ዳር አንደተተከለች ፍሬዋን በየጊዜው እንደምትሰጥ ቅጠልዋም
እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል›› (መዝ. 1÷3) እና የመሳሰሉትን ሁሉ እናገኛለን (ራእይ.2÷16፣ 22÷1፣
22÷17)፡፡
እንግዲህ
ውኃ ከክፉ ኀሊና ለመንጻታችንና ለመቀደሳችን ማረጋገጫ መሆኑን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ሲል አስተምሯል፡- ‹‹ከክፉ ሕሊና
ለመነጻት ልባችንን ተረጭተን፣ ሰውነታችንንም በጥሩ ውኃ ታጥበን፣ በተረዳንበት እምነት በቅን ልብ እንቅረብ››
(ዕብ.10÷22)፡፡
7.
ለንጊኖስ የተባለው ሐራዊ (ወታደር) የጌታን ቀኝ ጎን በጦር በወጋው ጊዜ ትኩስ ደምና ውኃ ባንድነት ፈሷል (ዮሐ.
19÷34)፡፡ደሙ ለመጠጣችን፣ ውኃው ለጥምቀታችን መሆኑን ሲያጠይቅ ነው፡፡ ይህንንም ፍቁረ እግዚእ ዮሐንስ እንዲህ ሲል ገልጾታል
‹‹በውኃና በደም የመጣ ይህ ነው፡፡ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ በውኃና በደሙ እንጂ በውኃው ብቻ አይደለም፡፡… የሚመሰክሩት
መንፈሱና ውኃው ደሙም እንጂ በውኃው ብቻ አይደለም፡፡… የሚመሰክሩተ መንፈሱና ውኃው ደሙም ሦስት ናቸውና፡፡ ሦስቱም በአንድ
ይስማማሉ›› (1ዮሐ.5÷6-8)፡፡
8.
ውኃ በሁሉም ቤት ይገኛል፡፡ በሀብታሙም በድኃውም ጥምቀትም ላመነ ሁሉ የተፈቀደ መሆኑን ለማጠየቅ በውኃ ሆኗል፡፡ ስለዚህም በውኃ
ብቻ እንጠመቃለን፡፡ ሥርዓተ ጥምቀቱን የሚፈጽመው ካህን አሐዱ አብ ቅዱስ፣ አሐዱ ወልድ ቅዱስ፣ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ ብሎ
በእግዚአብሔር ቃል ሲባርከው ውኃው ተለውጦ በዕለተ ዓርብ ከጌታችን ቀኝ ጐን የፈሰሰውን ውኃ ይሆናል፡፡
No comments:
Post a Comment