በዚህ ዕለት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱሱ ክርስቶስ ስለ ሥልጣኑ ተጠይቋል፡፡
ጠያቂዎቹ የካህናት አለቆችና የሕዝብ አለቆች ናቸው፡፡ ጥያቄውም “በማን ሥልጣን እነዚህን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን የሰጠህ
ማነው?” የሚል ነበር፡፡ የካህናት አለቆች ያቀረቡት ጥያቄ ነበር፡፡ ጌታችን ሰኞ ዕለት ሁለት ነገሮችን ማድረጉን ተያይዞ የተነሣ
ጥያቄ ነው፡፡ ሰኞ ከቅጠል ብቻ በቀር ፍሬ ያላገኘባትን ዕፀ በለስ ረግሟል፤ በማስከተል ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ የሚሸጡትንና
የሚለውጡትን አስወጥቷል፡፡ ማቴ.21÷23-25፤ ማር.11÷27፣ ሉቃ.20÷1-8፡፡ ከላይ እንደ ተገለጸው ጌታችን ሲያደርጋቸው
የነበሩት ተአምራትና የኃይል ሥራዎች የካህናት አለቆችን ስላስቀናቸው ጌታችንን ከሮማ መንግሥት ባለ ሥልጣናት ጋር ለማጋጨት
የቀየሱት ስልት ነው፡፡
ጌታችን በቤተ መቅደስ የነበሩትን ነጋዴዎችን አባሯል፤ መደባቸውን ገለባብጧል፡፡ ነጋዴን ማባረርና መደብን ማስለቀቅ መንግሥታዊ ሥራ ነው፡፡ በአንድ አገር የንግድ ቦታን የሚያጸድቅ መንግሥት መሆኑ እሙን ነው፡፡ ጌታችን ፈሪሳውያን ላቀረቡት ጥያቄ ቀጥተኛ መልስ አልመለሰም፡፡ ምክንያቱም ጥያቄው ለከሳሾቹ አመቺ ሁኔታን ስለሚፈጥር ጥያቄውን በጥያቄ መልሷል፡፡ “በመባሕተ መኑ ትገብር ዘንተ፤ በማን ሥልጣን ነው ይህን የምታደርገው?” ነበር ያሉት፡፡ በራሴ ሥልጣን ቢላቸው ፀረ መንግሥት አቋም አለው በማለት ከሮማ መንግሥት ዘንድ ለማሳጣት ነበር ዕቅዳቸው፡፡
ጌታችን እኩይ የሆነውን የፈሪሳውያንን አሳብ በመረዳት “የዮሐንስ ጥምቀት ከየት ነው ከሰማይ ነው ወይስ ከምድር ሲል”
ጠይቋቸዋል፡፡ ከሰማይ ያልነው እንደ ሆነ ለምን አላመናችሁበትም ይለናል÷ ከሰው ያልነው ከሆነ ሕዝቡ ይጣላናል፡፡ ምክንያቱም
ሕዝቡ ዮሐንስን እንደ አባት ይፈሩት እንደ መምህር ያከብሩት ነበርና ከዚህ የተነሣ ያቀረቡት የፈተና ጥያቄ ግቡን ሳይመታ
ከሽፎባቸዋል፡፡ ማቴ.21÷25፤ ማር.11÷27-30፤ ሉቃ.20÷1-8፡፡
ዛሬም ቢሆን መልካም ሥራን
በሠራን ጊዜ ከልዩ ልዩ ወገኖች የሚመጡ ፈተናዎች ለመልካም ሥራችን እንቅፋት ሊሆን እንደሚችሉ መገንዘብ አለብን፡፡ ብዙ ወገኖች
ለቅን አሳባችን ለምን ሰዎች ክፉ ነገር ይመልሱልናል በማለት ሲጠይቁ ይሰማል፡፡ ለቅን ዐሳባችን ከዓለም ዘንድ የተገላቢጦሽ ነገር
እንደ ሚጠብቀን “ዓለም የሚወደው የገዛ ወገኑን ነው” የሚለውን የጌታችንን ትምህርት ልብ ይሏል፡፡ ይህ በመሆኑ በዘመናችን
አሳልፈው ሊሰጡን የሚፈልጉ ሰዎች ፈታኝ ጥያቄ እንደሚያቀርቡልን ከወዲሁ ልንገነዘብ ይገባል፡፡ምንጭ የማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ ነው::
No comments:
Post a Comment