በስመ አብ ወወልድ
ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡ አሜን!
“ካለውና ከነበረው ከሚመጣውም በዙፋኑም ፊት ካሉት ከሰባቱ
መናፍስት ከታመነውም ምስክር ከሙታንም በኩር የምድርም ነገሥታት ገዥ ከሆነ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን አሜን!””
“እስከ ሞት ድረስ የታመንህ ሁን “ ራዕየ ዮሐንስ ምእራፍ ፪ ፥ ፲
በዘላለማዊ የኪዳን ደም ሊታደገንና ለነፍሳችን ፍጹም እረፍትን ሊሰጠን፡ ወደ ክብሩ ዙፋን ሊያደርሰንና ወደ ቅዱሳን ሕብረት
ሊደምረን በቀራንዮ ለቤዛነታችን መስዋዕት የሆነው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ሞት ድረስ ለታመነው ሐዋርያ በፍጥሞ ደሴት በግዞት ሳለ ወደፊት በቤተክርቲያን ላይ ሊደርስ ስላለው መከራ፦ ስደትና
ፈተና እንዲሁም ለቤተክርስቲያን መሪዎችና ለማህበረ ምእመናን ፦ ከእነርሱ
ስለሚጠበቀው ኃላፊነትና ክርስቲያናዊ ግዴታ ምን እንደሆነ በአጽንኦት የሚያመላክት፤ አማናዊ ቃሉን ለሚጠብቁ እና እንደ ፈቃዱም ጸንተው
ለሚኖሩት ያዘጋጀላቸው ፍጹም የሆነ ሰማያዊ ክብር እና ጸጋ በማስረገጥ በራዕይ የገለጠለት ምስጢራዊ የትንቢት ቃል ነው።
በራዕየ ዮሐንስ ምዕራፍ ሁለት እና ሦስት የተጻፉት ትንቢታዊ መልዕክቶች በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን በእስያ (በዛሬዋ
የቱርክ ክፍለ ግዛት) አካባቢ በቅዱሳን ሐዋርያት ትምህርት የተመሰረቱ እና ታላቅ መንፈሳዊ አገልግሎት ይሰጥባቸው የነበሩ ሰባት
አብያተ ክርስቲያናት ፦ የአገልግሎት ጥንካሬ እና ድክመት ምን እንደሆኑ በዝርዝር ከማስረዳታቸውም ባሻገር የእነዚያ አብያተ ክርስቲያናት
መሪዎች እና ምእመናን በተለያዩ ምክንያቶች በወቅቱ ከደረሱባቸው ወደ
ፊትም ሊመጡባቸው ከሚችሉ ፈተናዎች እና መከራዎች እንዴት ማምለጥ እንደሚችሉ ከእግዚአብሔር የተላከላቸውን መልዕክት ሰምተው፦ በእምነትም
ጸንተው፦ በመንፈሳዊ ተጋድሎ በርትተው በእግዚአንሔር ኃይል እና መንፈስ በመታገዝ በአሸናፊነት መጓዝ የሚችሉባቸውን መንገዶች የሚያሳዩ
መልዕክቶች ናቸው። ለዚህም ነው በእያንዳንዷ መልዕክት መዝጊያ ላይ “ መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ።” በማለት ያሳሰበው።
ከሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከልም ከወቀሳው ቃል የዳኑት ሰምርኔስ እና ፊላዴልፊያ ሲሆኑ የአምስቱ አብያተ ክርስቲያናት አለቆች እና ምዕመናን ወቀሳ እና ተግሳጽ ደርሶባቸዋል። “እስከሞት ድረስ የታመንህ ሁን.....”
የሚለው ቃል በወቅቱ የተነገረውም በሰምርኔስ ቤተ ክርስቲያን ተሹሞ ለነበረው ለቅዱስ ሄሬኔዎስ ነው። በእርሱ እና በምእመናን ላይ
እስራት እና ጽኑ የሆነ መከራ እንደሚደርስባቸው እያሳሰበ በዚህ ሁሉ
ግን ሊደርስባቸው በሚችለው ነገር ሳይሳቀቁ ፍርሃትን በእምነት አስወግደው እስከ ሞት ድረስ እግዚአብሔርን በመታመን እንዲጸኑ፦ ይህንን
ቢያደርጉ የሕይወትን አክሊል እንደሚቀዳጁ በማስረገጥ ነው መልዕክቱን ያጠቃለለው።