፪፦ በውዳሴ ማርያም ትሰብከዋለች።
ካለፈው የቀጠለ . . .
፪፥፫፦ ነፃነትን ሰበከላቸው፤
አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን በግብርናተ ዲያብሎስ ተይዘው (የዲያብሎስ ባሮች ሆነው)፥ ለአምስት ሺህ
አምስት መቶ ዘመን፥ እስከ ልጅ ልጆቻቸው በሲኦል ኖረዋል። ኑሮውም የሥቃይና የፍዳ ነበር፥ ይህም ያን ዘመን፥ ዘመነ ፍዳ፣ ዘመነ ኲነኔ አሰኝቶታል። ጊዜው ሲደርስ (እግዚአብሔር፦ አምስት ቀን ተኲል ሲፈጸም፥ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ ብሎ ለአዳም የገባው ቃል የሚፈጸምበት ዘመን ሲደርስ)፥ ከሦስቱ አካላት አንዱ ወልድ፥ በተለየ አካሉ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከድንግል ማርያም ተወለደ። ቀስ በቀስ አድጎ በሠላሳ ዓመቱ ተጠመቀ፥ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ወንጌልን አስተማረ፥ ተአምራትንም አደረገ፥ በመጨረሻም በዕፀ መስቀል ተሰቅሎ (ሥጋውን በመቁረስ፥ ደሙን በማፍሰስ፥ ነፍሱንም በፈቃዱ አሳልፎ በመስጠት) የሰውን ልጅ አዳነ። በአካለ ሥጋ ወደ መቃብር ወርዶ ሙስን መቃብርን አጠፋ፥ በአካለ ነፍስ ደግሞ ወደ ሲኦል ወርዶ ነፍሳትን ማረከ፥ ሲኦልን ባዶ አስቀረ። ይኽንንም ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ፦ «ክርስቶስም ስለ ሰው ኃጢአት አንድ ጊዜ ሞቷልና፤ ጻድቅ እርሱ እኛን ወደ እግዚአብሔር (ወደ ባሕርይ አባቱ ወደ አብ፥ ወደ ራሱ እና ወደ ባሕርይ ሕይወቱ ወደ መንፈስ ቅዱስ) ያቀርበን ዘንድ ስለእኛ ስለ ኃጢአታችን በሥጋ ሞተ፤ (በተለየ አካሉ በተዋሕዶ ሰው ኹኖ ሞተ)፤ በመንፈስ ግን (በመለኰት) ሕያው ነው። በእርሱም (ሥጋን ተዋሕዶ በአካለ ሥጋ ወደ መቃብር እንደወረደ፥ ነፍስንም ተዋሕዶ በአካለ ነፍስም) በወኅኒ (በሲኦል) ወደአሉ ነፍሳት ሄዶ ነጻነትን ሰበከላቸው።» በማለት ገልጦታል። ፩ኛ ጴጥ ፫፥፲፰-፲፱። ይኽንን ታላቅ የነገረ ድኅነት ምሥጢር ይዘን ወደ ውዳሴ ማርያም ስንሄድ፦ «ፈቀደ እግዚህ ያግዕዞ ለአዳም ኅዙነ ወትኩዘ ልብ ወያግቦዖ ኀበ ዘትካት መንበሩ፤ ጌታ ልቡ ያዘነና የተከዘ አዳምን ነፃ ያወጣውና ወደ ቀድሞው ቦታው (ወደ ጥንተ ርስቱ ገነት) ይመልሰው ዘንድ ወደደ፤» ይለናል። (የሰኞ ቁ. ፩)። በተጨማሪም፦ «በዳዊት አገር የተወለደ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዳምንና ሔዋንን ነፃ አደረጋቸው፤» እያለ ይሰብከናል። (የሰኞ ቁ. ፱)
፪፥፬፦ ጌትነቱ፥ አካላዊ ቃልነቱ፥ አምላክነቱ፥ ልጅነቱና ስሙ፤
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፦ ነገረ ክርስቶስ (ምሥጢረ ድኅነት) ከስብከት አልፎ ጸሎት፥ መዝሙር፥ ቅዳሴ፥ ማኅሌት ሆኗል። የሰባቱን ዕለታት ውዳሴ ማርያም በግዕዝም ሆነ በአማርኛ የምንደግም (የምንጸልይ) ሰዎች፥ እግዚአብሔር የሚለውን ስም ሠላሳ አምስት ጊዜ፥ ጌታ የሚለውን ሃያ አንድ ጊዜ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚለውን ሠላሳ ሰባት ጊዜ፥ መድኃኒት የሚለውን ሠላሳ ሰባት ጊዜ፥ አማኑኤል የሚለውን አምስት ጊዜ፥ መለኮት የሚለውን ዘጠኝ ጊዜ፥ ንጉሥ የሚለውን ዘጠኝ ጊዜ፥ ፈጣሪ የሚለውን አራት ጊዜ፥ ብርሃን የሚለውን አሥራ አራት ጊዜ፥ ሕይወት የሚለውን አምስት ጊዜ እንጠራለን። ኃይለ ቃሉ ትርጓሜው እና ምሥጢሩ በትክክል ነገረ ድኅነትን የሚሰብክ፥ ቀራንዮን የሚያሳይ ነው።
·
«ነቢዩ ኢሳይያስ
በመንፈስ ቅዱስ የዐማኑኤልን ምሥጢር አየ፤ ስለዚህ ሕፃን ተወለደልን፥ ወልድም ተሰጠልን፥ ብሎ አሰምቶ ተናገረ።» ኢሳ ፯፥፲፬፣ ፱፥፮፤ (የሰኞ ቁ. ፭)
·
ሰው ሆይ፥ ፈጽመህ ደስ ይበልህ፥ እግዚአብሔር ዓለሙን ወዶታልና፤ አንድ ልጁንም (ተቀዳሚና ተከታይ የሌለውን የባሕርይ ልጁን)፥ የሚያምንበት ሁሉ እስከ ዘለዓለም ፈጽሞ ይድን ዘንድ አሳልፎ ሰጥቷልና፥ ልዑል (አብ) ክንዱን (ልጁን) ሰደደልን።» ዮሐ ፫፥፲፭-፲፰። (የሰኞ ቁ. ፮)።
·
«የነበረው፥ የሚኖረው፥ የሚመጣው፥ ዳግመኛም የሚመጣውም ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ያለመለወጥ ፍጹም ሰው ሆነ።» ዮሐ ፩፥፲፬፣ ራእ ፩፥፲፪፣ (የሰኞ ቁ. ፯)
·
የቀድሞውን እርግማን (መርገመ ሥጋን መርገም ነፍስን) አጥፍቷልና፥ የጠላትን ምክሩን አፈረሰበት፥ ለአዳምና ለሔዋን የዕዳ ደብዳቤያቸውን ቀደደላቸው፥ በዳዊት ሀገር የተወለደ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዳምንና ሔዋንን ነፃ አደረጋቸው።» ገላ ፫፥፲፫። (የሰኞ ቊ. ፱)
·
«የዓለም የሰው
ሁሉ ደስታ የሆነ የመልአኩን ቃል ተቀብለሻልና ደስ ይበልሽ
፤ ዓለሙን ሁሉ የፈጠረ ጌታን የወለድሽው ሆይ ፥ደስ ይበልሽ ።» ሉቃ ፩፥፳፰፣ ዮሐ ፩፥፫ ( የማክሰኞ ቁ. ፮ )።
·
« ድንግል ሆይ፥ ቅድስት ሆይ፥ ጌታን የወለድሽ ሆይ፥ እኛን ለማዳን ድንቅ ምሥጢር (አምላክ የሆነበት
ምሥጢረ ተዋህዶ) በአንቺ ቢደረግ ንጉሥን ወልደሽልናልና፥ ፍጥረታትን በልዩ
ልዩ መልኩ የፈጠረ፥ የእርሱን የገናንነቱን ነገር ፈጽመን መናገር አይቻለንምና ዝም እንበል።» ዮሐ ፩፥፳፭፣ መዝ ፭፥፪፣ ፱፥፴፮፣ ፲፯፥፶፤ ኢሳ ፴፪፥፩፣ ፴፫፥፲፯፤ ኤር ፳፫፥፭፣ ፪ኛ ጴጥ ፩፥፲፩። ( የማክሰኞ ቁ.፰)
·
« የድንግል ገናንነትዋ ሊናገሩት አይቻልም፥ ጌታ መርጦአታልና፥ የሚቀርበው በሌለ ብርሃን ውስጥ የሚኖር እርሱ
መጥቶ አደረባት፤ ዘጠኝ ወር በማኅፀንዋ አደረ፤ የማይታይና የማይመረመር (ባህርየ መለኮቱ የማይታይ የማይመረመር) እርሱን በድንግልና ወለደችው።» ፩ኛ ጢሞ ፮፥፲፮። ( የማክሰኞ ፲፩ )።
·
« ነቢዩ ዳንኤል ያየው ያለ እጅ ( እጅ ሳይነካው)
ከረጅም ተራራ የተፈነቀለው ያ ደንጊያ ከአብ ዘንድ የወጣው ቃል ነውና፥ መጥቶ ያለ ወንድ ዘር ከድንግል ተወልዶ አዳነን።» ዳን ፪፥፴፬፣ መዝ ፩፻፲፯፥፳፪፣ ማቴ ፳፩፥፵፪፣ ኤፌ ፪፥፳፣ ፩ኛ ጴጥ ፪፥፭፣ ዮሐ ፩፥፩። (የማክሰኞ ቁ.፲፪ )
·
«እናትና ገረድ
ማርያም ሆይ፥ ደስ ይበልሽ፤ የታቀፍሽውን መላእክት ያመሰግኑታልና፥ ኪሩቤልም በፍርሃት ይሰግዱለታልና፥ ሱራፌልም ያለማቋረጥ ክንፋቸውን ዘርግተው የሚመሰገን ንጉሥ
ይህ ነው፥ በይቅርታው ብዛት የዓለምን ኃጢአት ያስተሠርይ ዘንድ የመጣው ይህ ነው፥ ይላሉ።» ኢሳ ፮፥፩-፬፣ ሉቃ ፪፥፲፫፣ ማቴ ፬፥፲፩፣ ዕብ ፩፥፮፣ ዘዳ ፴፪፥፵፫። (የማክሰኞ ቁ. ፲፮)
·
«ከአባቱ ያልተለየ
አንድ እርሱን የተሸከምሽ ሆይ፥ ደስ ይበልሽ፤ በክብር ጌጥ ሁሉ ያጌጠ እርሱ መጥቶ ሰው የሆነብሽ ንጽሕት የሠርግ ቤት ሆይ፥ ደስ ይበልሽ፤ የመለኮት እሳት ያላቃጠለሽ ዕፀ ጳጦስ ሆይ፥ ደስ ይበልሽ፤ በኪሩብል ላይ የሚቀመጠው ሰማያዊ መለኮትን በሥጋ የተሸከምሽ
ገረድና እናት፥ ድንግል እና ሰማይ ሆይ፥ ደስ ይበልሽ፤ ስለዚህ ንጹሓን ከሆኑ መላእክት ጋር በፍጹም ደስታ ደስ ተሰኝተን እናመስግን፥ በሰማይ
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፥ በምድርም ዕርቅ ይሁን፥ እንበል፤ ክብርና ምስጋና ጌትነት ያለው እርሱ አንቺን ወዷልና።» ዘጸ ፫፥፪፣ መዝ ፩፻፴፩፥፲፫፣ ኢሳ ፩፥፮፣ ሕዝ ፩፥፬፣ ዘጸ፲፫፥፳፩፣ ፲፱፥፲፰፤ ዘዳ ፬፥፳፬፤ (የረቡዕ ቁ.፮)
·
«ከቅዱሳን ክብር
የማርያም ክብር ይበልጣል፥ የአብን ቃል ለመቀበል በተገባ ተገኝታለችና፤ መላእክት የሚፈሩትን፥ ትጉሆች በሰማያት የሚያመሰግኑትን ድንግል ማርያም በማኅፀንዋ ተሸከመችው። ይህች ከኪሩቤል ትበልጣለች፥ ከሱራፌልም ትበልጣለች፥ ከሦስቱ አካል ለአንዱ (ለወልድ) ማደሪያ ሆናለችና። (ኪሩቤል ቢሸከሙ የእሳቱን ዙፋን ነው፥ ሱራፌል ቢያጥኑ የእሳቱን ዙፋን ነው፥ እርሷ ግን እርሱን ባለቤቱን ተሸከመችው)። የነቢያት ሀገራቸው ኢየሩሳሌም ይህቺ ናት፥ ለቅዱሳን ሁሉ የደስታቸው ማደሪያ ናት፤ በጨለማና በሞት ጥላ ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች
ታላቅ ብርሃን ወጣላቸው፤ በቅዱሳን ላይ (በረድኤት) የሚያድር እግዚአብሔር እኛን ለማዳን ልዩ ከሆነች ድንግል ሰው ሆኗልና፥ ኑ ይህን ድንቅ እዩ፥ ስለተገለጠልን ምሥጢር ምስጋና አቅርቡ፤ ሰው የማይሆን ሰው ሆኗልና፥ ቃል ተዋሕዷልና፤ ጥንት የሌለው ሥጋ ጥንታዊ ቀዳማዊ ሆነ፥ ዘመን የማይቆጠርለት መለኮት ዘመን ተቆጠረለት፤ የማይታወቅ ተገለጠ፥ የማይታይ ታየ፤ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ በርግጥ ሰው ሆነ። ትላንት የነበረው፥ ዛሬም ያለው፥ መቼም የሚኖረው፥ ኢየሱስ ክርስ ቶስ እንሰግድለትና እናመሰግነው ዘንድ አንድ
ባሕርይ ነው።» ኢሳ ፮፥፪፣ መዝ ፩፻፵፯፥፩፣ ኢሳ ፱፥፩-፪፣ ማቴ ፬፥፲፮፣ ዕብ ፲፫፥፰፣ ራእ ፩፥፰። (የረቡዕ ቁ. ፯)
·
« ሰለ ሔዋን
የገነት ደጅ ተዘጋ፥ ዳግመኛም ስለድንግል
ማርያም ተከፈተልን፥ ከዕፀ ሕይወት እንበላ ዘንድ አደለን፥ ይኸውም እኛን ስለመውደድ መጥቶ ያዳነን የክርስቶስ ክቡር ሥጋው ክቡር ደሙ ነው።» ዮሐ ፮፥፶፫ ( የሐሙስ ቁ.፫)።
·
«መልአኩ ልጅ
ትወልጃለሽ፥ ስሙም ዐማኑኤል ይባላል፥ አላት። ትርጓሜውም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ሆነ
ማለት ነው። ዳግመኛም ወገኖቹን ከኃጢአታቸው የሚያድናቸው
ኢየሱስ ይባላል። በችሎታው (በኃይሉ) ያድነን ዘንድ፥ ኃጢአታችንንም ያስተሠርይልን ዘንድ፥ ለዘለዓለም ክብር ይግባውና ሰው የሆነ እርሱን አምላክ እንደሆነ በተረዳ ነገር አውቀነዋልና። ልዩ ከሆነች ድንግል ማርያም
ይህ የአምላክ መወለድ ምን ይደንቅ፥ ቃልን ወሰነችው። ልደቱንም ዘር አልቀደመውም፥ በመወለዱም ድንግልናዋን አልለወ ጠውም። ቃል ከአብ ያለድካም ወጣ፥ ከድንግልም ያለሕማም ተወለደ። ሰብአ ሰገል ሰገዱለት፤ አምላክ ነውና፥ ዕጣን አመጡለት፥ ንጉሥም ነውና፥ ወርቅ አመጡለት፤ ስለኛ በፈቃዱ ለተቀበለው መዳኛችን ለሆነ ሞቱም ከርቤ አመጡለት፤ ቸርና ሰውን ወዳጅ የሆነ አንድ እርሱ ብቻ ነው።» ማቴ ፩፥፳፩-፳፫፣ ኢሳ ፯፥፲፬፣ ሕዝ ፵፬፥፩-፬፣ ማቴ ፪፥፲፩። (የሐሙስ ቁ.፬)
·
«በኪሩቤልና በሱራፌል
ላይ አድሮ የሚኖር ጌታ መጥቶ በማኅፀንሽ አድሯልና፥ ሰውን የሚወድ ወደ እርሱ አቀረበን፥ ክብር ምስጋና ያለው እርሱ የእኛን ሞት ተቀብሎ የእርሱን ሕይወት ለእኛ
ሰጠን።» ኢሳ ፶፫፥፬፣ ሮሜ ፮፥፬፣ ገላ ፪፥፳ (የዓርብ ቁ.፫)
·
«የባሕርያችን መዳን
በማኅፀንሽ ፍሬ ተገኝቷልና፥ ወደአባቱ ወደ እግዚአብሔር አቀረበን።» ፩ኛጴጥ ፫፥፲፰-፲፱።
·
«ከተለዩ የተለየች
የተባልሽ፥ የኪዳን ጽላት ያለበሽ፥
የተሰወረ መና ያለበሽ፥ የወርቅ መሶብ ያለብሽ፥ ደብተራ ድንኳን አንቺ ነሽ። ይኸውም መና የተባለው መጥቶ በድንግል ማርያም ማኅፀን ያደረው የእግዚአብሔር
ልጅ ነው፤ የአብ ቃል በእርሷ ሰው ሆነ፥ መጥቶ ያዳነን የባሕርይ ንጉሥን በዓለም ውስጥ ወለደችው። የሚናገር በግ የክርስቶስ እናቱ ገነት ደስ ይላታል፥ ለዘለዓለም የሚኖር የአብ ልጅ እርሱ መጥቶ ከኃጢአት
አድኖናልና።» ዘጸ ፲፮፥፲፫፣ ፳፭፥፩-፳፪፣ ፵፥፳፤ (የቅዳሜ ቁ. ፯)።
·
«ያለመለወጥ ካንቺ ሰው የሆነ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደገኛ ስሙን አስቀድሞ በየውጣ ነገረን፥ ለአዲስ ኪዳንም አስታራቂ ሆነ። በከበረ ደሙ ፈሳሽነት ወይም መፍሰስ ያመኑትንና ንፁሓን የሆኑትን ወገኖች አነፃ ቸው።» (የእሑድ ቁ. ፩)
እንግዲህ በመጠን አነስተኛ የሆነችው ውዳሴ ማርያም የምትሰብክልን ነገረ ድኅነት፥
ከሰማይ የራቀ፥ ከውቅያኖስም የጠለቀ መሆኑን ማስተዋል ይገባል። ውዳሴ ማርያም፦ ነገረ ማርያም ብቻ ሳትሆን ነገረ መለኰትም ጭምር መሆኗን መገንዘብም ከሃይማኖት ሰዎች ይጠበቃል። በቀጥታ አነጋገርም ነገረ ማርያም ነገረ መለኰት ነው፥ ማለት ይቻላል። ምክንያቱም፦ መለኰት ከሰማይ ወርዶ በማኅፀኗ ባያድር፥ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ ሰው ኹኖ ባይወለድ ኖሮ ነገረ ማርያም አይኖርም ነበር። ነገረ ማርያም ማለት ማኅደረ መለኰት መሆኗን መናገር ነውና። የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን፤ አሜን።
ይቀጥላል . . .
No comments:
Post a Comment