ቤተ ክርስቲያን አንዲት ናት፤ ምክንያቱም የአንድ የክርስቶስ አካል ናትና። ይህች የክርስቶስ አካል የሆነች ቤተ ክርስርስቲያን መሠረቷም ጉልላቷም ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ይህንንም ታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ፦ «እርሱም (ክርስቶስ)ከሁሉ በፊት ነው፤ (ለዘመኑ ጥንት የሌለው ቀዳማዊ ነው)፤. . . እርሱም የአካሉ ማለትም የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው፤. . . እርስዋም አካሉና ሁሉን በሁሉ የሚሞላ የእርሱ ሙላቱ ናት፤» ሲል ገልጦአታል። ኤፌ ፩፥፳፫፣ ቈላ ፩፥፲፰። በተጨማሪም በቆሮንቶስ መልእክቱ ላይ «የእግዚአብሔር ጸጋ እንደተሰጠኝ መጠን እንደ ብልሃተኛ የአናጺ አለቃ መሠረትን መሠረትሁ፥ ሌላውም በላዩ ያንጻል። እያንዳንዱ ግን በእርሱ ላይ እንዴት እንዲያንጽ ይጠንቀቅ። ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ ሊመሠርት አይችልምና፤ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።» ብሎአል። ፩ኛ ቆሮ ፫፥፲-፲፩።
በክርስቶስ ደም ላይ የተመሠረተችው ይህች ሐዋርያዊትና ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያዪቱ ቤተ ክርስቲያን ናት። የሐዋ ፳፥፳፰፣ ዕብ ፫፥፲፬። በመሆኑም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የምታስተምረው ትምህርት ሁሉ እውነት ነው። ምክንያቱም እውነት የባሕርይ ገንዘቡ ከሆነ ከእውነተኛው ምንጭ የተቀዳ ነውና። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «ለእናንተ ደግሞ አሳልፌ የሰጠሁትን እኔ ከጌታ ተቀብያለሁና፤» ሲለ እንደተናገረ ቤተ ክርስቲያንም ለእኛ ያስተላለፈችው ከጌታ የተቀበለችውን ንጹሕ ትምህርት ነው። ፩ኛ ቆሮ ፲፩፥፳፫። ይኸውም በዓይኖቿ ያየችውን፥ በጆሮዎቿ የሰማችውን ፥በእጆቿም የዳሰሰችውን ነው። ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ፦ «ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን፥ በዓይኖቻችን ያየነውን፥ የተመለከትነውንም፥ እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን፤ ሕይወትም ተገለጠ፤ አይተንማል፥ እንመሰክርማለን፥ ከአብ ዘንድ የነበረውንም (ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በቅድምና የነበረውን፥ ፈጥሮም የሚገዛውን) ለእኛም የተገለጠውን (በመለኰት ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ሳይለይ በተለየ አካሉ ከሰማየ ሰማያት በመውረድ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ በመወለድ ሰው ሆኖ የታየውን) የዘላለምን ሕይወት እናወራላችኋለን፤ » ያለው። ፩ኛ ዮሐ ፩፥፩-፫። ስለሆነም፥ የቅዱሳን ሐዋርያትን ትምህርት በመያዟ፥ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን የምትባለው ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፥ ክርስቶስን በቅዱሳን ሐዋርያት ዓይኖች አይታዋለች፥ በጆሮዎቻቸው ሰምታዋለች፥ በእጆቻቸውም ዳስሰዋለች። ይህም፦ ቤተ ክርስቲያንን ብፅዕት ያሰኛታል። ምክንያቱም ጌታ ደቀመዛሙርቱን፦ «የእናንተ ግን ዓይኖቻችሁ ስለሚያዩ፥ ጆሮዎቻችሁም ስለሚሰሙ ብፁዓን ናቸው፤» ብሎአቸዋልና። ማቴ ፲፫፥፲፮።
ብፅዕት፥ ንጽሕት እና ቅድስት የሆነችው ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካል በመሆኗ ሁለንተናዋ የሚሰብከው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ «መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ፥ እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤» ሲል እንደተናገረ፥ ቤተክርስቲያን ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ እየሰበከች ያለችው በደሙ የዋጃትን ኢየሱስ ክርስቶስን ነው። ፩ኛ ቆሮ ፩፥፳፪-፳፫፣ የሐዋ ፳፥፳፰።
ብዙ ሰዎች ስብከት ሲባል «ኢየሱስ ጌታ ነው፤» እያሉ እንደ ዓለማውያን መፈክር በባዶ ሕይወት ባዶ ጩኸት ማስተጋባት ይመስላቸዋል። ነገር ግን አይደለም፤ ምክንያቱም ጌታችን በወንጌል፦ «በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ ጌታ ሆይ፥ጌታ ሆይ፥ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም። በዚያን ቀን ብዙዎች፦ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፥ በስምህስ አጋንንት አላወጣንምን፥ በስምህስ ብዙ ተአምራት አላደረግንምን? ይሉኛል። የዚያን ጊዜም፦ ከቶ አላውቃችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ።» ብሎአልና። ማቴ ፯፥፳፩-፳፫።
በክርስትና ትምህርት ኢየሱስ ክርስቶስ የሚሰበከው በሕይወት(በኑሮ)ነው። በመሆኑም ጌታችን በወንጌል፦ «መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ፤» ሲል አስተምሮአል። ማቴ ፭፥፲፮። ለዚህም ነው ቤተ ክርስቲያን በኑሮዋ ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስን የምትሰብከው። ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ትምህርቷ በጆሮ የሚሰማ ብቻ ሳይሆን በዓይን የሚታይና በእጅም የሚዳሰስ ነው። ይኽንን በመሰለ የትምህርት አሰጣጥ ዘዴም ቤተ ክርስቲያን ሁል ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስን ትሰብከዋለች።
፩ኛ፦ በክቡር መስቀሉ ትሰብከዋለች፤
ጌታችን መርገመ ሥጋንና መርገመ ነፍስን አጥፍቶ ድኅነተ ምዕመናንን የፈጸመው በዕፀ መስቀል ላይ ነው። ገላ ፫፥፲፫፣ ኤፌ ፪፥፲፬-፲፯፣ ፊል ፪፥፰፣ ዕብ ፲፪፥፩-፪። ይኽም መስቀል የክርስቶስ ኃይሉ የተገለጠበትና በደሙም የከበረ ነው። ፩ኛ ቆ ፩፥፲፰። ጌታችን
በዚህ መስቀል ዲያቢሎስን ድል ካደረገው በኋላ እኛም ድል እያደረግነው እንድንኖር ኃይላችን የሆነውን መስቀል አስታጥቆናል። ኤፌ ፪፥፲፮። በመሆኑም እንደ ሐዋርያው እንደ ቅዱስ ጳውሎስ በመስቀሉ እንመካለን። ገላ ፮፥፲፬። መመካትም ብቻ ሳይሆን የጌታችን እግሮች ለድኅነተ ምዕመናን በችንካር ላይ ቆመው ለዋሉበት ለክቡር መስቀሉ እንሰግዳለን። ምክንያቱም ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት በትንቢት፦ «እግሮቹ በሚቆሙበት ሥፍራ እንሰግዳለን፤» ብሎአልና መዝ ፩፻፴፩፥፯። በዚህም መሰረት ቤተ ክርስቲያን ከፍ አድርጋ በጉልላቷ ላይ የተከለችውና ዕለት ዕለትም ካህናት በክርስቶስ ስም ምዕመናንን የሚባርኩበት ቅዱስ መስቀል የሚሰብከውና የሚናገረው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
፪ኛ፦ በቅዱሳት ሥዕላት ትሰብከዋለች፤
በዘመነ ብሉይ ሥዕለ ኪሩብን እንዲያዘጋጅ ለሙሴ የነገረው እግዚአብሔር ነው። ሙሴም የታዘዘውን ፈጽሟል፤ ዘጸ ፳፭፥፳፩-፳፪። እግዚአብሔርም አስቀድሞ እንደተናገረ በሥዕሉ እያደረ አነጋግሮታል። ዘኁ ፯፥፹፱። ንጉሡ ሰሎሞንም በዘመኑ የእግዚአብሔርን
ቤተ መቅደስ ሠርቶ
ከጨረሰ በኋላ በግምቡ ዙሪያ ሥዕለ ኪሩብን በማሠራቱ እግዚአብሔር ሥራውን ወዶለታል። ፩ኛ ነገ ፮፥፳፫-፳፱፣ ፪ኛ ዜና ፯፥፲፩-፲፪። ከዚህም የምንማረው ቅዱሳት ሥዕላትን መሥራት የተጀመረው በእግዚአብሔር ትእዛዝ መሆኑን ነው። ይህ ትእዛዝ በአዲስ ኪዳንም አልተሻረም። ምክንያቱም ተሽሮ ቢሆን ኖሮ ጌታችን የገንዘብ ለዋጮችን ገበታዎችና የርግብ ሻጮችን ወንበር ገልብጦ ከቤተ መቅደስ ባስወጣ ጊዜ ሥዕሉንም ባስወጣ ነበርና ነው። ማቴ ፳፩፥፩-፲፫። ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን በእግዚአብሔር ትእዛዝ መሠረት በመቅደሷ በቅድስቷና በቅኔ ማኅሌቷ ዙሪያ የጌታችንን ብሥራቱን፥ ልደቱን፥ ስደቱን፥ ጥምቀቱን፥ ተአምራቱን፥ መከራ መስቀሉን፥ ርደተ መቃብሩን፥ ትንሣኤውን፥ ዕርገቱንና ዳግም ምጽአቱን የሚያመለክቱ ቅዱሳት ሥዕላትን በመሣል ክርስቶስን በሥዕል ትሰብከዋለች። በቤተ ክርስቲያን ቅዱሳት ሥዕላት ማስተማሪያ ብቻ አይደሉም። ልክ እንደ በትረ ሙሴ፥ እንደ ኤልያስ መጐናጸፊያ፥ እንደ ኤልሳዕ ቅርፊትና ጨው፥ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ የልብስ ቁራጭ፥ እንደ ቅዱስ ጴትሮስም ጥላ ያኃይለ እግዚአብሔር መገለጫዎችና የበረከት መገኛዎች ናቸው። ዘጸ ፬፥፲፪፣ ፪ኛ ነገ ፪፥፰፣ ፪ኛ ነገ ፪፥፳፩፣ ፮፥፮፤ የሐ ፭፥፲፭፣ ፲፱፥፳፪። በመሆኑም ለቅዱሳት ሥዕላት ይሰገዳል።
፫ኛ፦ በጽላቷ ትሰብከዋለች፤
ሕጉና ትእዛዙ የተቀረጸበትን ፅላት አስቀድሞ ለሙሴ የሰጠ እግዚአብሔር ነው። ዘጸ ፴፩፥፲፰። በኋላም በተሰበሩት ምትክ ሙሴ እንዲያዘጋጅ የፈቀደ እግዚአብሔር ነው። ዘጸ ፴፬፥፩። የጽላቱ ማደሪያ ታቦትን የደፈረ ኦዛንም የቀሰፈ እግዚአብሔር ነው። ታቦቱን ላከበረ ለአቢዳራም በረከቱን ያትረፈረፈ እግዚአብሔር ነው። ፪ኛ ሳሙ ፮፥፮-፲፪። በአዲስ ኪዳንም፦ «እኔ ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም።» ያለ ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ማቴ ፭፥፲፯። ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ደግሞ፦ «በሰማይም ያለው የእግዚአብሔር መቅደስ ተከፈተ፥ የኪዳኑም ታቦት በመቅደሱ ታየ፥ መብረቅና ድምፅም ነጐድጓድም የምድርም መናወጥ ታላቅም በረዶ ሆነ፤» ብሎአል። ራእ ፲፩፥፲፱፤ በመሆኑም ቤተ ክርስቲያን ጽላትን አክብራ ይዛለች። በእነዚህም ጽላት ላይ ከስም ሁሉ በላይ የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተቀርጾባቸዋል። ከዚህም ጋር «በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ ለኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይንበርከኩ።» የሚለው የሐዋርያው የቅዱስ ጳውሎስ ቃል ተቀርጾባቸዋል። ፊል ፪፥፲። በመሆኑም በጽላቱ ፊት የሚሰገደው ለኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው። ለዚህም ነው ቤተ ክርስቲያን ኢየሱስ ክርስቶስን በጽላቷ ትሰብከዋለች ያልነው።
፬ኛ፦ በንዋየ ቅዱሳት ትሰብከዋለች፤
የቤተ መቅደስ መገልገያዎች በዘይት (በሜሮን) እንዲከብሩ ያደረገ፥ ተቀብተው ቅድስተ ቅዱሳን ይሆናሉ፥ የነካቸውም ቅዱስ ይሆናል ያለ እግዚአብሔር ነው ። ዘጸ ፴፥፳፪-፴፫። በመሆኑም እግዚአብሔር የሚገለገልባቸው የቤተ መቅደስ መገልገያዎች ሁሉ በሜሮን የከበሩ ናቸው። እነዚህም የከበሩ ንዋየ ቅዱሳት ከአገልግሎታቸው በተጨማሪ እያንዳንዳቸው ራሱን የቻለ መንፈሳዊ መልእክት ያስተላልፋሉ። ስለሆነም፦ መቋሚያው፥ ከበሮው፥ ጸናጽሉ፥ ካባው፥ ጥምጥሙ፥ አክሊሉ፥ ቆቡ፥ ቀሚሱ፥ ጻሕሉ፥ እርፈ መስቀሉ፥ ጽንሐው ወዘተ. . . የሚሰብከው ኢየሱስ ክርስቶስን ነው። (ኆኅተ ሰማይ የሚለውን የቀሲስ ያሬድ ገብረ መድኅንን ድንቅ መጽሐፍ ያንብቡ)።
፭ኛ፦ በቅዱስ ቁርባን ትሰብከዋለች፤
የአዲስ ኪዳን ቁርባን የኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋና ደም ነው። በመሆኑም በቤተ ክርስቲያን ኅብስቱ ተለውጦ ሥጋ መለኰት፥ ወይኑም ተለውጦ ደመ መለኰት ይሆናል። ይኽንንም፦ «እንካችሁ ብሉ፤ ይህ ሥጋዬ ነው፤ ጽዋንም አንሥቶ . . .
ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው።» ብሎ የሰጠ ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ማቴ ፳፮፥፳፮-፳፯። በተጨማሪም፦ «እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የወልደ ዕጓለ እመሕያው ክርስቶስን ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም። ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው። እኔ በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ። ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ
ነውና። ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል፤ እኔም በእርሱ እኖራለሁ፤» ብሎአል። ዮሐ ፮፥፶፫-፶፮። ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «ስለዚህ ሳይገባው ይህን እንጀራ የበላ ወይም የጌታን ጽዋ የጠጣ ሁሉ የጌታ ሥጋና ደም ዕዳ አለበት። ሰው ግን ራሱን ይፈትን፥ እንዲሁም ከእንጀራው ይብላ ከጽዋውም ይጠጣ፤ ሳይገባው የሚበላና የሚጠጣ የጌታን ሥጋ ስለማይለይ ለራሱ ፍርድ ይበላልና፥ ይጠጣልምና።» በማለት ቅዱስ ቁርባንን ማክበር በንጽሕናም ሆኖ መቀበል እንደሚገባ የተናገረው። ፩ኛ ቆሮ ፲፩፥፳፯-፳፱። ስለሆነም ቤተ ክርስቲያን ይኽንን መሠረት በማድረግ በቅዱስ ቁርባን የክርስቶስን ሕይወትነት ትሰብካለች።
፮ኛ፦ በምስጋናዋ ትሰብከዋለች፤
ቤተ ክርስቲያን ከዓመት እስከ ዓመት የማይቋረጥ ምስጋና በመዓልትም በሌሊትም ለእግዚአብሔር ታቀርባለች። በኪዳን፥ በመዝሙር፥ በቅዳሴና በማኅሌት እግዚአብሔርን ታመሰግነዋለች። ይህም ምስጋና ከብሉይ ኪዳንና ከሐዲስ ኪዳን ከመጽሐፍተ ሊቃውንትም የተውጣጣ ነው። ለምሳሌ በመጽሐፈ ግጻዌው መሠረት በየዕለቱ በሚቀደሰው ቅዳሴ ላይ ከቅዱስ ወንጌልና ከቅዱሳት ሐዋርያት መልእክታት የሁለቱ ይነበባል። በመጨረሻም (ከቅዳሴው በኋላ) ይተረጐማል ፥ ይመሰጠራል ወደ
ህይወት ተለውጦ ይሰበካል። በመሆኑም ንባቡም ሆነ ትርጉሙ እንዲሁም ምሥጢሩ የሚሰብከው ኢየሱስ ክርስቶስን ነው።
፯ኛ፦ በአጽዋማት ትሰብከዋለች፤
በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ሰባት አጽዋማት አሉ። እነዚህም የሚሰብኩት ኢየሱስ ክርስቶስን ነው። ፩ኛ፦ ዐቢይ ጾምን የምንጾመው ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ፦ እጸድቅ አይል ጻድቅ፥ እከብር አይል ክቡር ሲሆን በገዳመ ቆሮንቶስ አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት በመጾም ባርኮና ቀድሶ ስለሰጠን ነው። በመጨረሻም ዲያቢሎስን ድል ነሥቶታል። ይሀም ብትጾሙ ጥንተ ጠላታችሁን ዲያቢሎስን ድል ትነሡታላችሁ ብሎ አብነት ሲሆነን ነው። ፪ኛ፦ ዓርብና ረቡዕን (ጾመ ድኅነትን) የምንጾመው ጌታችን በዕለተ ረቡዕ በአይሁድ ሸንጐ ሞት ስለተፈረደበትና በዕለተ ዓርብ ደግሞ ድኅነታችንን በመስቀል ላይ የፈጸመበት ዕለት ስለሆነ ነው። ፫ኛ፦ ጾመ ነቢያትን የምንጾመው ቅዱሳን ነቢያት ጌታ ይወርዳል ይወለዳል ብለው በተስፋ በደጅ ጥናት በእርሱ ስም የጾሙት ጾም በመሆኑ ነው። እኛም ይኽንኑ በማሰብና ከቅዱሳኑም በረከት ለመሳተፍ ከበዓለ ልደት በፊት በስሙ እንጾማለን። ምክንያቱም ጌታ በወንጌል፦ «እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፥ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል። ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል፥ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል፤» ብሎአልና። ማቴ ፲፥፵-፵፩። ፬ኛ፦ ጾመ ሐዋርያትን የምንጾመው ቅዱሳን ሐዋርያት የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ተቀብለው «የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ስሙ ሕይወት መድኃኒት ነው፤» ብለው ለመስበክ ከመሰማራታቸው በፊት በስሙ የጾሙት ጾም በመሆኑ ነው።
፭ኛ፦ የገሃድን ጾም የምንጾመው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥምቀት ዓርብ ወይም ረቡዕ በሚውልበት ጊዜ ለውጠን በዋዜማው ማክሰኞ ወይም ሐሙስ ነው። ይኸውም፦ ትንቢተ ነቢያት የተፈጸመበትን፥ ምሥጢረ ሥላሴ የተገለጠበትን፥ የጸጋ ልጅነታችን የተመለሰበትን፥ በዮርዳኖስ ተጥሎ የነበረው የዕዳ ደብዳቤያችን የተፋቀበትን ሰማያት ተከፍተው ምሥጢር የታየበትን፥ ጥምቀታችን የተባረከበትንና የተቀደሰበትን በዓለ ጥምቀት በታላቅ ደስታ ለማክበር ነው። ፮ኛ፦ ጾመ ፍልሰታን የምንጾመው ቅዱሳን ሐዋርያት እመቤታችን ካረፈች በኋላ ቅዱሳን መላእክት አሳርገዋት ስለነበር ሥጋዋን ለማግኘት እርሱን ተማጽነው በእርሱ ፈቃድ የእናቱን ሥጋ ያገኙበት
ጾም ስለሆነ ነው። ፯ኛ፦ ጾመ ነነዌን የምንጾመው ሰብአ ነነዌ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት ጾመው ምሕረትን ከጌታ ያገኙበት፥ እርሱም የወደደው ጾም ስለሆነ ነው። በመሆኑም ይኽንን የምሕረትና የይቅርታ ጾም ብንጾም ጌታ ይምረናል ብለን በማመን ነው የምንጾመው።
፰ኛ፦ በበዓላት ትሰብከዋለች፤
በዓላትን ባርኰና ቀድሶ እንዲያከብሩት ለሰው ልጆች የሰጠ እግዚአብሔር ነው። ይኸውም ገና ከመጀመሪያው ቀዳሚት ሰንበትን በማክበሩና በመቀደሱ ታውቋል። ዘጸ ፳፥፲፩። በዚህም ምክንያት ሰንበትን አለማክበር ከባድ ቅጣትን ያስከትል ነበር። ዘኁ ፲፭፥፴፪-፴፮። እስራኤል ዘሥጋ ዕለቱን በሚገባ ባለማክበራቸው በነቢያት ተወቅሰዋል። ሕዝ ፳፥፲፪-፲፮፣ አሞ ፰፥፮። በአዲስ ኪዳንም ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዕለተ ሰንበትን አክብሮአል። ሉቃ ፬፥፲፮። ጌታ የተቃወመው የፈሪሳውያንን የሰንበት አከባበር ሥርዓት እንጂ የሰንበትን ክብር አይደለም። ማቴ ፲፪፥፩-፬። ከሰንበትም ሌላ አይሁድ በእግዚአብሔር ትእዛዝ የፋሲካን፥ የመከርን፥ የዳስን፥ መለከቶች የሚነፉበትን፥ የማስተስረያን፥ የፉሪምን፥ የመቅደስ መታደስ መታሰቢያን በዓል በመንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ያከብሩ ነበር።
በአዲስ ኪዳን ደግሞ ቤተ ክርስቲያን በማኅሌት እና በቅዳሴ የምታከብራቸው ዘጠኝ ዓበይት በዓላት እና ዘጠኝ ንዑሳን በዓላት አሉ። እነዚህም ብሥራት፥ ልደት፥ ጥምቀት፥ ደብረ ታቦር፥ ሆሳዕና፥ ስቅለት፥ ትንሣኤ፥ ዕርገት፥ ጰራቅሊጦስ እና የመስከረም መስቀል፥ ስብከት፥ ብርሃን፥ ኖላዊ፥ ግዝረት፥ ልደተ ስምዖን፥ቃና ዘገሊላ፥ ደብረ ዘይት፥ የመጋቢት መስቀል ናቸው። ሌሎችም የጌታ በዓላት አሉ። በእነዚህም የተከበሩና የተቀደሱ ዕለታት በሁሉ ማለትም በቅዳሴውም፥ በማኅሌቱም፥ በትምህርቱም የሚሰበከው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ከዚህም ጋር ቤተ ክርስቲያን የእመቤታችንን እና የቅዱሳንን በዓላት በታላቅ መንፈሳዊ ሥርዓት ታከብራለች። ይኽንንም የምታደርገው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው። ምክንያቱም እመቤታችን ከፍጥረታት ሁሉ በላይ የሆነችበትን ጸጋና ክብር ያገኘችው ለጌታ እናትነት በመመረጧ ነውና። ለዚህም ነው እግዚአብሔር የላከው ቅዱስ ገብርኤል፦ «ደስ ይበልሽ፥ ጸጋን የሞላብሽ ሆይ፥ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺም ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ። . . . ማርያም ሆይ በእግዚአብሔር ዘንድ ጸጋን አግኝተሻልና፤» ሲለ ያመሰገናት። ሉቃ ፩፥፳፰፣፴። መንፈስ ቅዱስ ያደረባት ኤልሳቤጥም፦ «አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፥ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው። የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይደረግልኛል? እነሆ የሰላምታሽ ድምፅ በጆሮዬ በመጣ ጊዜ ፅንሱ በማኅፀኔ በደስታ ዘሎአልና። ከጌታ የተነገረላት ይፈጸማልና ያመነች ብፅዕት ናት።» በማለት አመስግናታለች። ሉቃ ፩፥፵፫-፵፭። እርሷም፦ «እነሆ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል፤» ብላለች። ሉቃ ፩፥፵፰። ቅዱሳን መላእክትም ለመዳን የተመረጡትን የሚረዱት በእርሱ ስም ነውና። ይኽንን በተመለከተ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት፦ «የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩ ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማል፤» ብሏል። መዝ ፴፫፥፯። ዕብ ፩፥፲፬። ቅዱሳን ነቢያትም ትንቢት የተናገሩት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና። ለዚህም ነው፥ ፊልጶስ፦ «ሙሴ በሕግ ነቢያትም ስለ እርሱ የጻፉትን. . . ኢየሱስን አግኝተነዋል፤» ያለው። ዮሐ ፩፥፵፮። ጌታም ከትንሣኤው በኋላ በኤማሁስ ጐዳና ያገኛቸውን ሉቃስንና ቀለዮጳን፦ «እናንተ የማታስተውሉ፥ ነቢያትም የተናገሩትን ሁሉ ልባችሁ ከማመን የዘገየ፤ ክርስቶስ ይህን መከራ ይቀበል ዘንድና ወደ ክብሩ ይገባ ዘንድ ይገባው የለምን?» ካላቸው በኋላ ስለ እርሱ ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ በመጻሕፍት የተጻፉትን ተርጉሞላቸዋል። ሉቃ ፳፬፥፳፭-፳፯። ለደቀመዛሙርቱም ተርጉሞላቸዋል። ሉቃ ፳፬፥፵፬-፵፯። ቅዱሳን ሐዋርያትም መከራውን ሁሉ ሳይሰቀቁ እስከ አጽናፈ ዓለም የሰበኩት ኢየሱስ ክርስቶስን ነው። የሐዋ ፪፥፴፮፣ ፰፥፴፭፣ ፱፥፳፯፣ ፲፮፥፴፩። ጌታም አስቀድሞ «ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ፤» ብሎአቸዋል። የሐዋ ፩፥፰። ቅዱሳን ጻድቃንም ከዓለም ተለይተው፥ በገዳም ተወስነው፥ ግርማ ሌሊትን፥ ደምፀ አራዊትን፥ ጸብአ አጋንንትን ሳይሰቀቁ በገድል ሲቀጠቀጡ የኖሩት በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው። ቅዱሳን ሰማዕታትም በመጋዝ የተተረተሩት፥ በሰይፍ የተመተሩት፥ በእሳት የተቃጠሉት በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው። አያሌ ተአምራትን ያደረጉትም በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው። የሐዋ ፫፥፮።
በመሆኑም ቅዱሳን በገድል የተቀጠቀጡት፥ ተአምራት ያደረጉትና የሚያማልዱትም በእርሱ ስም ስለሆነ ይህ ሁሉ የሚነገርበት በዓላቸው የሚሰብከው ኢየሱስ ክርስቶስን ነው። በአጠቃላይ የቅዱሳን ሕይወታቸው የሚሰብከው ኢየሱስ ክርስቶስን ነው። ምክንያቱም ቅዱሳን እርሱን መስለው ተገኝተዋልና። ፩ኛ ቆሮ ፲፩፥፩።
፱ኛ፦ በባህል ትሰብካዋለች፤
ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ትርጉም ባለው ባህሏም የምትሰብከው ኢየሱስ ክርሰቶስን ነው። ለዚህም የምዕመናንን ሕይወት መመልከት ብቻ ይበቃል። ለምሳሌ ምዕመናን እንደ ባህል አድርገው በግንባራቸውና በእጃቸው ላይ የሚነቀሱት የመስቀል ቅርጽ የሚሰብከው የኢየሱስ ክርስቶስን ቤዛነት ነው። በተለይም እናቶቻችን በቀሚሶቻቸውና በነጠላዎቻቸው ላይ የሚጠልፉት በሐረግ የተንቆጠቆጠ የመስቀል ቅርጽ የሚሰብከው የመስቀሉን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ነው። በየክብረ በዓሉ የምንለብሰው ነጩ ልብሳችንም የሚሰብከው የክርስቶስን ብርሃንነት ነው። ይህንን ልብስ ቅዱሳን መላእክት በጌታ ትንሣኤና ዕርገት ጊዜ ለብሰውት ታይተዋል። ዮሐ ፳፥፲፪፣ የሐዋ ፩፥፲። በአጸደ ነፍስ ያሉ ቅዱሳንም ልብሳቸው ነጭ ነው። ራእ ፮፥፲፩። የጌታም ልብስ በደብረ ታቦር እንደ ብርሃን ነጭ ሆኗል። ማቴ ፲፯፥፪። ለዘመን መለወጫ፥ ለመስቀል፥ ለደብረ ታቦር በዓላት የሚበራውም ችቦ የሚሰብከው የኢየሱስ ክርስቶስን ብርሃንነት ነው። ሌሎችም ይኽንን የመሰሉ የተቀደሱ ባህሎች አሉ።
፲ኛ፦ በሥርዓት ትሰብከዋለች፤
ቤተ ክርስቲያን ለቅዳሴዋ፥ ለማኅሌቷ፥ ለመዝሙሯ፥ ለጾሟ፥ ለጸሎቷ ሁሉ ሥርዓት አላት። ምክንያቱሞ እግዚአ ብሔር የሚመለከው በዘፈቀደ ሳይሆን በሥርዓት ነውና። ጥንት በኦሪቱ ቤተ መቅደስ፥ እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠው ሥርዓት ነበር። በዚህም ምክንያት ለመብራቱ፥ ለዕጣኑ፥ ለመሥዋዕቱ፥ ለታቦቱ ወዘተ. . . ሥርዓት ነበረው። ይህንንም ሥርዓት «በምን አለበት?» የተላለፉትን ሰዎች እግዚአብሔር ቀጥቷቸዋል። ዘኁ ፲፮፥፩-፶፣ ኢያ ፮፥፲፰፣ ዘሌ ፲፥፩፣ ፩ኛ ሳሙ ፬፥፩-፳፪፣ ፪ኛ ዜና ፳፮፥፲፯፣ ፩ኛ ሳሙ ፮፥፲፱፣ ፪ኛ ሳሙ ፮፥፲፩፣ ፩ኛ ሳሙ ፲፥፭፣ ፩ኛ ሳሙ ፲፫፥፰፣ ዳን ፭፥፩-፴፩፣ የሐዋ ፭፥፩-፴፩፣ ፰፥፬-፳፬፣ ፲፱፥፲፩-፲፯። በአዲስ ኪዳንም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ በስምንተኛው ቀን ሥርዓተ ግዝረትን ለመፈጸም ወደ ቤተ ግዝረት ሄዷል። ይህንንም ሉቃስ ወንጌላዊ፦ «ሊገርዙት ስምንት ቀን በሞላ ጊዜ በማኅፀን ሳይረገዝ በመልአኩ እንደተባለ ስሙ ኢየሱስ ተብሎ ተጠራ።» ሲል ገልጦታል። ሉቃ ፪፥፳፩። አርባ ቀን በሞላውም ጊዜ ሥርዓት ለመፈጸም ወደ ኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ወስደውታል። ሉቃ ፪፥፳፪-፳፬። ዘጸ ፲፫፥፪፤ ዘሌ ፲፪፥፩። የአሥራ ሁለት ዓመት በሆነውም ጊዜ የፋሲካን በዓል ለማክበር እንደ በዓሉ ሥርዓት ወደ ኢየሩሳሌም ሄዷል። ሉቃ ፪፥፵፩። ሥርዓተ ጾምን ሲፈጽምም እንደነ ሙሴ እንደነ ኤልያስ አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት ጾሟል። ማቴ ፬፥፪፣ ዘጸ ፴፬፥፳፰፤ ፩ኛ ነገ ፲፱፥፰። ሥርዓተ ጥምቀትንም በዮርዳኖስ ፈጽሟል። ማቴ ፫፥፲፫-፲፯። በቃና ዘገሊላ ሠርግ ቤትም በመገኘት ሥርዓተ ተክሊልን ባርኳል። ዮሐ ፪፥፩-፲፩። ሥርዓተ ጸሎትንም ፈጽሟል። ሉቃ ፳፪፥፴፱-፵፮፣ የሐ ፲፩፥፵፭። ይኽንንም ያደረገው ምሳሌውን ትቶልን ለመሄድ ለአብነት ነው። ለዚህም ነው ጌታችን «ከእኔ ተማሩ፤» ያለው። ማቴ ፲፩፥፳፱። በተጨማሪም የደቀመዛሙርቱን እግር በማጠብ ሥርዓተ ትህትናን በፈጸመ ጊዜ «እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና፤» ብሎአል። ዮሐ ፲፫፥፲፭። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም «የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና። ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና።» ሲል ምዕመናንን አስተምሯል። ፩ኛ ጴጥ ፪፥፳፩።
እንግዲህ ኢየሱስ ክርስቶስን አብነት አድርጋ ለሁሉ ነገሯ ሥርዓት ያላት ቤተ ክርስቲያን፥ በሥርዓቷ የምትሰብከው ኢየሱስ ክርስቶስን ነው። ለምሳሌ ለሕፃናት ሥርዓተ ጥምቀትን ከፈጸመችላቸው በኋላ ስመ ክርስትና ትሰጣቸዋለች። ገብረ ወልድ፥ ተክለ ወልድ፤ ወለተ ወልድ፤ ገብረ ኢየሱስ፤ ወልደ ኢየሱስ፥ ኃይለ ኢየሱስ፥ አምኃ ኢየሱስ፤ ወለተ ኢየሱስ፥ አመተ ኢየሱስ፥ ፍቅርተ ኢየሱስ፥ ገብረ ክርስቶስ፤ ወለተ ክርስቶስ ወዘተ. . . ብላ ትሰይማቸዋለች። በዚህም የሚሰበከው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በምዕመናን አንገት ላይ የሚታሰረው ክርና መስቀሉም የሚሰብከው ኢየሱስ ክርስቶስን ነው። በጸሎት ጊዜ ገጽን በትእምርተ መስቀል በማማተብና ነጠላን አመሳቅሎ በመልበስም የሚሰበከው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እንዲሁም ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት፦ «በቀን ሰባት ጊዜ አመሰግንሃለሁ፤» መዝ ፩፻፲፰፥ ፩፻፷፬ ሲል በተናገረው መሠረት ሰባቱ የጸሎት ጊዜያትም የሚናገሩት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ፩ኛ፦ ነግህ (ማለዳ)፦ ጌታችን በዚህ
ሰዓት በጲላጦስ ፊት ቆሞ ተወቅሶበታል። ማቴ ፳፯፥፩። ፪ኛ፦ ሠለስት(ሦስት ሰዓት)፦ ጌታችን የተገረፈበት ሰዓት ነው፤ ዮሐ ፲፱፥፩። ፫ኛ፦ ቀትር (ስድስት ሰዓት)፦ ጌታችን የተሰቀለበት፥ መራራ ሐሞት የጠጣበት፥ልብሱን የተገፈፈበት ሰዓት ነው፤ ማር ፲፭፥፳፭። ፬ኛ ተሰዓት (ዘጠኝ ሰዓት)፦ ጌታችን ሰባቱን አጽርሐ መስቀል የተናገረበትና ቅድስት ነፍሱን ከክቡር ሥጋው በፈቃዱ የለየበት ሰዓት ነው። ማቴ ፳፯፥፶፣ ማር ፲፭፥፴፬። ፭ኛ ሠርክ (አሥራ አንድ ሰዓት)፦ ጌታችን ወደ ከርሠ መቃብር የወረደበት ሰዓት ነው፤ ማቴ ፳፯፥፷። ፮ኛ፦ ንዋም (የመኝታ ሰዓት)፦ ጌታችን ሥርዓተ ጸሎትን ያስተማረበት ሰዓት ነው፤ ማቴ ፳፮፥፴፰-፵፫። ፯ኛ፦ መንፈቀ ሌሊት፦ ጌታችን የተወለደባት፥ ሞትን ድል አድርጐ የተነሣባትና ዳግም የሚመጣባት ሰዓት ነው። ሉቃ ፪፥፰፣ ማቴ ፳፰፥፩፣ የሐዋ ፩፥፲፩።
፲፩ኛ፦ በፊደሎች ትሰብከዋለች፤
ቤተ ክርስቲያን ቀርጻ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያበረከተቻቸው ከሀ - ፐ ያሉት ፊደሎች
የሚሰብኩት ኢየሱስ ክርስቶስን ነው። ለምሳሌ «ሀ» ብሂል፦ ሀልዎቱ ለአብ እምቅድመ ዓለም፤ የአብ አኗኗሩ ከዓለም በፊት ነው፤ «ለ» ብሂል፦ ለብሰ ሥጋ እምድንግል፤ ክርስቶስ ከድንግል ሥጋ ለበሰ፤ «ሐ» ብሂል፦ ሐመ ወሞተ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ አሥራ ሦስቱን ሕማማት በመስቀል ላይ ተቀብሎ ሞተ፤ «መ» ብሂል፦ መንክር ግብሩ ለእግዚአብሔር፤ የእግዚአብሔር ሥራው ድንቅ ነው፤ «ሠ» ብሂል ሠረቀ በሥጋ፤ በሥጋ ተገለጠ፤ «ረ» ብሂል፦ ረግዓት ምድር በቃሉ፤ ምድር በቃሉ ረጋች፤ «ሰ» ብሂል፦ ሰብአ ኮነ እግዚእነ፤ ጌታችን ሰው ሆነ፤ «ቀ» ብሂል፦ ቀዳሚሁ ቃል፤ ቃል በመጀመሪያ ነበረ፤ «በ» ብሂል፦ በትኅትናሁ ወረደ፤ ጌታችን በትህትና ከሰማየ ሰማያት ወረደ፤ ማለት ነው። ወዘተ . . .
ከቤተ ደጀኔ የተወሰደ
No comments:
Post a Comment