Monday, July 16, 2012

ቤተክርስቲያን እንዴት ተመሠረተች ? ክፍል ፩


 ስለ ክርስትና ሃይማኖት ስለ ቤተክርስቲያን በምንናገርበት ጊዜ ሁሉ ትዝ የሚለንና የምናስተውለው የመጀመሪያው ሰው የአዳም ሁኔታ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን እግዚአብሔር ሁላችንን አባት አዳምን በአርአያውና በመልኩ ከፈጠረው በኋላ ባረከው፡፡ ኹሉንም እንዲገዛ ሥልጣን ሰጠው፡፡ በረከቱን ሥልጣኑንና ሲሳዩን ከሰጠው በኋላ ፈጣሪውን የሚያስታውስበት ትእዛዝ አዘዘው፡፡ እሱ ግን በተሳሳተ ምክር ተመርቶ ከፈጣሪው ትእዛዝ ወጣ፡፡ በዚህ ጊዜ የሞት ፍርድ ተፈረደበት፡፡ ይህም የሞት ቅጣት ለርሱ ዐቅም ቀላል አልነበረም፡፡ በሱም ብቻ አልቀረም የልጅ ልጆቹ ይህን የሞት ቅጣት በውርስ ተካፈሉት፡፡ የዚህ የሞት ጽዋ ተካፋዮች ሆኑ፡፡ የአዳም ሕግን መተላለፍ የልጆቹም ተባባሪነት በእግዚአብሔርና በነሱ መካከል ያለውን ልዩነት እያሰፋው ሔደ፡፡ የፈጠራቸው እግዚአብሔርን ዘንግተው የሰማይና የምድርን ሠራዊት ማምለክ ጀመሩ፡፡ በጨረቃ፣ በፀሐይና በከዋክብት፣ በእሳት፣ በውኃ፣ በእንስሳትና በአራዊት፣ በዛፍና በተራራ፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር የሰውን ዘር ጨርሶ ለመደምሰስ ስላልፈለገ ይህን የሰው ልጅ መራራና አሰቃቂ ታሪክ ከመጀመሪያው ጀምረው ሲከታተሉ የነበሩ በአንድ አምላክ በማመን የታወቁ ጥቂት ሰዎችን አተረፈ፡፡ እነሱም ከአበው ሄኖክን፣ ኖህን፣ አብርሃምንና ሎጥን ሌሎችንም የመሳሰሉትን ነው፡፡ 



ከአብርሃም ይስሐቅ፣ ከይስሐቅ ያዕቆብ ተወለደ፡፡ ከያዕቆብም አሥራ ሁለት ልጆች ተወለዱ፡፡ አሥራ ኹለቱን የእሥራኤል ነገድ መሠረቱ፡፡ ለነሱም አንዳንድ ጊዜ ራሱ እግዚአብሔር እየተገለጠ አንዳንድ ጊዜም በነቢያትና በካህናት አማካይነት ሕጉንና ትእዛዙን ይሰጣቸው ነበር፡፡ መላልሶ ተአምራት ያደርግላቸው ነበር፡፡ ነገር ግን በአካባቢያቸው በነበረው የአረማውያን ተጽዕኖ ምክንያት እነዚህ ሰዎች አልፎ አልፎ በየጊዜው ወደ አምልኮ ባዕድ ይወድቁ ነበር፡፡ በአንድ ወገን ይህ ሲሆን በሌላው ወገን ሲታይ ደግሞ ከእውነተኛው የአንድ አምላክ እምነት ያላፈነገጡ፤ በአምልኮ ባዕድ ያልተለወጡ ብዙ እሥራኤላውያን ነበሩ፡፡ እነዚህ አምልኮታቸው የጸና ነበር የሚባሉት እሥራኤላውያን ከኃጢአት ለመንጻትና የእግዚአብሔርን ምሕረትና ይቅርታ ለመጠየቅ ብዙ ወይፈኖችንና ጊደሮችን ይሠዉ ነበር፡፡ እግዚብሔርን ደስ ቢለው በማለት በወርቅ የተለበጠ በሐር የተጨመጨመ ቤተ መቅደስ በሰሎሞን ተሠርቶ ነበር፡፡እግዚአብሔር በነቢያት እያደረ የሚመልሰው መልስ ይህን ሁሉ ደስ ብሎት የተቀበለው አለመሆኑን የሚገልጽ ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ የሰው ልጅ የታሪክ ጉዞ በኋላ እግዚአብሔር በራሱ ፈቃድ የሰውን ልጅ ለማዳን የቀጠረው ቀን ሲደርስ ልጁን ሰው ይሆን ዘንድ ላከው፡፡ በልጁ በክርስቶስ ሞት ቤተክርስቲያን ተመሠረተች፡፡ 


ቤተክርስቲያን የተወለደችው ወይም የተመሠረተችው በፍልስጥዔም ምድር ነው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ከላይ እንደተገለጠው የሰውን ልጅ ትክክለኛ ታሪክና ሃይማኖት የያዙ የእግዚአብሔርንም የምሕረት ቀን በተስፋ ሲጠባበቁ የነበሩ በትዕግሥታቸው የተመሰገኑ ብዙ ደጋግና ቅዱሳን ሰዎች ስለነበሩባት ነው፡፡ የእግዚአብሔርንም የማዳን ሥራው ድንገተኛ ሳይሆን ለብዙ ዘመናት በተስፋ ሲጠበቅ የቆየ መሆኑን ለመግለጥ ነው፡፡ የክርስትና ሃይማኖት የታሪክ ሃይማኖት ነው መባሉም በዚህ ነው፡፡ ክርስትና በተወለደበት ጊዜ የነበረውን የፍልስጥኤም ሁኔታ ለማጤን የሚቻለው ቀደም ካለው ሁኔታ የጀመርን እንደሆነ ነው፡፡ ፍልስጥዔም የአብርሃም የቃልኪዳን አገር ከነዐን ናት፡፡ በሌላም አነጋገር ምድረ ርስት ትባላለች፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን የያዕቆብ ልጆች በሙሉ ከዚች አገር ተሰደው በግብጽ በባርነት ይኖሩ ነበር፡፡ ዘመኑም 17ዐዐ-13ዐዐ ከጌታ ልደት በፊት መሆኑ ነው፡፡ ከጌታ ልደት በፊት 13ዐዐ ዓመት ገደማ በሙሴ መሪነት ወደዚች አገር ተመልሰዋል፡፡ 1922 ዓመት ከጌታ ልደት በፊት አሥራ ኹለቱ ነገድ ባገዛዝ ተጣልተው ለሁለት ተከፈሉ፡፡ አሥሩ ነገድ በሰሜን ፍልስጥኤም በሰማርያ ተቀመጡ፡፡ 


ከተማቸው ሴኬም ነበረች፡፡ ኹለቱ ነገድ ደግሞ በደቡብ ፍልስጥኤም ሰፈሩ፡፡ ከተማቸውም ኢየሩሳሌም ነበረች፡፡ 792 ዓመት ከጌታ ልደት በፊት ሰሜኑን ክፍል እስራኤላውያን በስልምናሶር መሪነት መጥተው አጠፏት፡፡ ሕዝቡም ተማረኩ፡፡ ይህ ሲሆን በደቡብ ክፍል የነበሩት የተማረኩትን አሥሩን ነገድ እንደ ጠላት ይቆጥሯቸው ስለነበር ሳይደሰቱ አልቀሩም፡፡ ነገር ግን 586 ከጌታ ልደት በፊት የሴኬም ፅዋ በኢየሩሳሌምም ደረሰ፡፡ በናቡከደነፆር መሪነት ባቢሎናውያን መጥተው ኢየሩሳሌምን አጠፉ ሕዝቡንም ማርከው ወሰዱ፡፡ ሰባ ዓመት በምርኮ ቆይተው ከተመለሱ በኋላ ጥቂት እንደቆዩ በፋርስ ተወረሩ፡፡ 
አሁንም እንደገና 33 ከጌታ ልደት በፊት ግሪኮች በዚች ምድር ላይ ቅኝ ገዢዎች ሆኑ፡፡ በመጨረሻም 63 ዓመት ከጌታ ልደት በፊት ሮማውያን ተረከቧት፡፡ እንግዲህ በዚህ ረጅም የተፋልሶ ጊዜ ሕዝቡ ብዙ የባህልና የሃይማኖት ቀውስ ደርሶበታል፤ እስራኤላዊ ያልሆኑ ጠባዮችንም ሳያውቀው ሸምቷል፡፡ ክርስትና በፍልስጥኤም ሲመሠረት የነበረውን ሁኔታ ለማወቅ የሚቻለው ይህ ሲታይ ነው፡፡ ክርስትና ሲወለድ ምድረ ፍልስጥኤም እንደ ሌሎቹ የመካከለኛው ምሥራቅ የሰሜን አፍሪካና የታናሽ እሲያ አገሮች በሮም ቅኝ ግዛት ሥር ነበረች፡፡ በውስጥም የነበሩ ሕዝቦችም የተከፋፈለ የሃይማኖትና የፖለቲካ ቡድን ነበራቸው፡፡ ከነዚህም ዋናዎቹ የፈሪሳውያንና የሰዱቃውያን ቡድኑች ነበሩ፡፡ የሰዱቃውያን ቡድን የሀብታሞችና የካህናት ቡድን ነው፡፡ ይህ ቡድን ለባሕል፣ ለሥነ ሥርዓትና ለሃይማኖት ግድ የሌለው ከቅኝ ገዢዎች ጋር ተስማምቶ በነሱ ሥልጣኔ መጠቀምን ብቻ እንጂ የነቢያትን ትንቢትና ሌሎችንም የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት አይቀበሉም ነበር፡፡ የሙታንን ትንሣኤና የመሲሕንም መምጣት አያምኑም ነበር፡፡ ሌላው ቡድን የፈሪሳውያን ቡድን ነው፡፡ 


ፈሪሳዊፖርሽከሚለው የዕብራይስጥ ቃል የወጣ ነው፤ ትርጉሙምየተለየማለት ነው፡፡ እነዚህ ፈሪሳውያን ምንም የቅኝ አገዛዝ ቀንበር መላልሶ ቢያደቃቸውም ባህልና ልምዳችን አይነካ በሃይማኖትም የሙሴን ሕግና የነቢያትን መጻሕፍት የምንጠብቅ እኛ ብቻ ነን ባዮች ነበሩ፡፡ ስለዚህ ከአይሁድ ዘር ውጭ ከሆነ ከማንኛውም ጎሳና ዘር ጋር በባህልና በሥልጣኔ መቀራረቡን እንደ መርከስና ሕግን እንደመተላለፍ ይቆጥሩ ነበር፡፡ የመሲሕንም መምጣት ነቅተውና ተግተው ይጠባበቁ ነበር፡፡ ለዚህም ዋናው ምክንያታቸው ሀገራቸው ፍልስጥኤምን ከሮም ግዛት ነጻ ለማውጣት የቆየ ጉጉት ስላላቸው ነው፡፡ እንደነሱ አስተሳሰብ መሲሕ ሲመጣ የጦር ኃይል አቋቁሞ ራሱ የጦር መሪ በመሆን የሮማን የቅኝ ግዛት ቀንበር አውልቆ ጥሎ የዳዊትን ቤተ መንግሥት የሚያድስ መሲሕ ይጠባበቁ ነበር ማለት ነው፡፡ ምንም እንኳ ከትንሣኤ በኋላ ሥጋዊ ኑሮ አለ ብለው ቢያምኑም ትንሣኤ ሙታን መኖሩን ያውቁ ነበር፡፡ ፈሪሳውያን በዕለታዊ ኑሮአቸው ብዙ ሀብት ፍልስጥኤምን ነጻ ያወጣል የሚለውን የፈሪሳውያን እምነትና ተስፋ በመቃወም ሌላ ንኡስ ቡድን ከፈሪሳውያን ተከፍለው በሙት ባሕር አካባቢ ገዳም መሥርተው ይኖሩ ነበር፡፡ የእነሱም ዓላማቸው እንደ ፈሪሳውያን መሲሕን መጠባበቅ ነው፡፡ ኤሤይ በመባል የታወቁት እነዚሁ ክፍሎች ከፈሪሳውያን የሚለዩት ፈሪሳውያን በጦር ኃይል ነጻ እንወጣለን ሲሉ ኤሤይ የሚባሉት ደግሞ በተአምራት በእግዚአብሔር ኃይል ፍልስጥዔም ነፃ ትወጣለች ብለው ያምኑ ነበር፡፡ በቤተልሔም በስተደቡብ ልዩ ስሙ ኩምራን በሚባል ቦታ የሚኖሩ እነዚህ ሰዎች መጻሕፍትን በመጻፍ ጸሎትን በማድረስ ብዙ ጊዜ ቆይተዋል፡፡ ኤሤዎችና ፈሪሳውያን ባንድ አንድ አስተሳሰብ ቢለያዩም መሲሕ መምጣቱንና የተወሰኑ ምርጥ ጎሳዎችን ነጻ እንደሚያወጣ ዓለም አቀፋዊ መሲሐዊ መንግሥት እንደሚያቋቁምና እነሱም የመንግሥት ባለሟሎች እንደሚሆኑ ሁለቱም ቡድኖች ያምኑ ነበር፡፡ በእስራኤል የሃይማኖትና የነገድ ቤተሰብ ውስጥ ይህ ልዩነት ተፈጥሮ መከራቸውን ሲያዩ በፍልስጥኤምና ከፍልስጥኤም ውጭ የነበረው የሮማ መንግሥት ፖለቲካ ደግሞ ከቅኝ ግዛቱ የተነሣ ያነገንግ ነበር፤ የነጻ አውጭ ግንባሮች በየጊዜው የሕዝብ ቆጠራ እንዲደረግ ታዞ ነበር፡፡
Source: http://www.melakuezezew.info/ 

No comments:

Post a Comment